Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ኢትዮጵያ ብሪክስን የመቀላቀሏ ዜና ጎራን የመደገፍ ጉዳይ አይደለም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

‹‹ኢትዮጵያ ብሪክስን የመቀላቀሏ ዜና ጎራን የመደገፍ ጉዳይ አይደለም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ቀን:

ኢትዮጵያ ብሪክስ የተሰኘውን ስብስብ ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርባ ተቀባይነት ማግኘቷ፣ ከአገራዊ ጥቅም አንፃር እንጂ ጎራን የመለየት ጉዳይ አይደለም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ አባል የሆኑበትን ይህን ስብስብ ለመቀላቀል ኢትዮጵያ ጥያቄ ማቅረቧን ይፋ ያደረገችው በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡  

ከ15 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ብሪክስ የተሰኘውና አምስት አገሮች የዓለም የኃይል ሚዛንን ለማመጣጠን በሚል የመሠረቱት ጥምረት ስለመሆኑ በብዙዎች ዘንድ የሚነገርለት ስብስብ፣ ነሐሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ 15ኛ የመሪዎች ጉባዔውን አካሂዷል፡፡

በጉባዔው ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ አርጀንቲና፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኢራንና ሳዑዲ ዓረቢያ ከመጪው ጥር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ብሪክስን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያን የብሪክስ አባልነትን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያ ያላትን አገራዊ አቅምና በአኅጉሩ ያላትን አስተዋጽኦ መሠረት በማድረግ ብዙ ሥራ መሥራት እንዳለባት ስለታመነበት እንጂ፣ ይህንን ጎራ ወይም ያንን ጎራ የመደገፍ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አክለውም፣ ‹‹የጎራ ጉዳይ ነው፣ የጎራ ጉዳይ አይደለም የሚሉ ተንታኞች አሉ፡፡ እሱ ግን የሙግት ጉዳይ ነው፡፡ ሙግቱን የምንወስደው ከተቀመጥንበት ወንበር አንፃር ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መጪው ዓመት አጋር የማብዛት ሥራ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥና ኢትዮጵያ ቀድሞ ወደ ነበረችበት የዲፕሎማሲ ቁመና የምትመለስበት ጊዜ ይሆናል  ያሉት  መለስ (አምባሳደር)፣ የዲፕሎማሲ ሥራው ከመከላከል ይልቅ ነገሮችን ቀድሞ መሥራት ላይ ያተኩራል ብለዋል፡፡ በዚህ ላይ የሚያተኩረው የ2016 ዓ.ም. የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ዕቅድ ቀጣይ ዝርዝር አፈጻጸሞች እንደሚገለጹ አስረድተዋል፡፡

የዲፕሎማሲ የመጨረሻው ግብ ወዳጅ የማብዛትና ጠላት የመቀነስ ጉዳይ በመሆኑ፣ በዚሁ የወዳጅ ማብዛት ሒደትም የዲፕሎማሲ፣ የገንዘብና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚገኝበት አክለዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያን የቢዝነስ መዳረሻዎችና  ምርቶች ለማስተዋወቅ፣ ከኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ያልተናነሰ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኤምባሲዎች መካከል ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር በ2016 ዓ.ም. በትኩረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከባህረ ሰላጤው አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት ከዚህ ቀደም እንደነበረው ታሪካዊ ግንኙነት ሳይሆን፣ ካለፉት አምስት ዓመታት በፊት የነበረውን ግንኙነት የሚለውጡ ብዙ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም አዲስ ምዕራፍና ገጽታን የሚቀይሩ ሥራዎች በመሠራታቸው ከመጠራጠር ወደ ትብብር የሚወስድ ግንኙነት ላይ ተደርሷል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...