Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለተሽከርካሪዎች የሚያስከፍሉት ዝቅተኛ የዓረቦን ወለል ተመን የሚተገበርበት አስገዳጅ መመርያ ወጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለተሽከርካሪዎች የኢንሹራንስ ሽፋን ዝቅተኛ የዓረቦን ወለል በመተመን ተግባራዊ የሚደረግበትን መመርያ አወጣ፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ተፈርሞ የወጣው መመርያ ከነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀን ጀምሮ የሚተገበር መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ በኋላ ማንኛውም የኢንሹራንስ ኩባንያ፣ ብሔራዊ ባንክ በዚህ መመርያ ካስቀመጠው ዝቅተኛ የዓረቦን ወለል በታች ዓረቦን ማውጣት አይችሉም፡፡ የዓረቦን ምጣኔያቸው ይህንኑ ዝቅተኛ ዋጋ መሠረት አድርገው የማይሠሩና በመመርያው ከተቀመጠው ዝቅተኛ ዋጋ በታች በጠየቁበት በእያንዳንዱ ተሽከርካሪ 25 ሺሕ ብር እንደሚቀጡም ተጠቅሷል፡፡

የመመርያው ዋነኛ ዓላማ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪው ውስጥ ለሞተር ኢንሹራንስ ሲሰጥ የቆየውን ያልተገባ ዋጋ ለማስቀረትና ገበያን መሠረት ያላደረጉ የዓረቦን ክፍያዎችን ለማስቀረት እንዲያስችል ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተሽከርከሪ ኢንሹራንስ ሽፋን እየደረሰባቸው ያለውን ከኪሳራ ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ መመርያ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዓረቦን ወለል ተመን ባለመኖሩ ኢንዱስትሪው ላይ ችግር እየፈጠረ ነው በሚል፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በማኅበራቸው ዝቅተኛ የዓረቦን ወለል ይውጣ በማለት ሲጠይቁ እንደነበር ይታወሳል፡፡  

በተለይ ከአንድ ዓመት በፊት ችግሩ ጎልቶ የታየበት የሞተር ኢንሹራንስ ዝቅተኛው የዓረቦን ወለል ሊሆን ይገባዋል ያሉትን ተመን፣ በውጭ ኩባንያ አስጠንተው ለብሔራዊ ባንክ አቅርበው ነበር፡፡

ከትናንት በስቲያ የወጣውም መመርያም በእዚሁ ጥናት ላይ መሠረት አድርጎ የወጣ ሲሆን፣ እንደ የተሽከርካሪው ዓይነት መከፈል የሚገባው ዝቅተኛ የዓረቦን ምጣኔ ሥሌት በዝርዝር የቀረበበት ነው፡፡

በመመርያው ላይ እንደተቀመጠው እንደ ተሽከርካሪው ዓይነት ከተሽከርካሪው ዋጋ ከ0.58 በመቶ እስከ 2.86 በመቶ ዝቅተኛው የዓረቦን ወለል የሚታሰብ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ለቤት ተሽከርካሪዎች የዓረቦን ክፍያ ከተሽከርካሪው ዋጋ 1.01 በመቶው የሚሆነው እንደ ዝቅተኛ ዋጋ ተሠልቶ የሚሠራበት እንደሚሆን በመመርያው ተጠቅሷል፡፡

የሞተር ሳይክሎች ደግሞ ከዋጋቸው 1.14 በመቶው ዝቅተኛው የዓረቦን ምጣኔ እንደሚሆን መመርያው ያመለክታል፡፡

ዝቅተኛ የዓረቦን መጠን የወጣላቸው የተሽከርካሪዎች ለግብርና አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ሲሆኑ፣ ዝቅተኛ የዓረቦን ምጣኔያቸው የሚሠላውም ከተሽከርካሪው ዋጋ 0.58 በመቶ የሚሆነው ነው፡፡

እስከ 16 ሰዎች የሚጭኑ የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ለተሽከርካሪዎቻቸው ለሚገቡት ዋስትና ዝቅተኛ የዓረቦን ምጣኔያቸው የተሽከርካዎቻቸውን ዋጋ 2.8 በመቶ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ በዚህ መመርያ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎች፣ ብሔራዊ ባንክ ለመጀመርያ ጊዜ በመድን ሽፋን ላይ ዝቅተኛ የዓረቦን ተመን በማውጣት ተግባራዊ እንዲሆን ያደረገበት መመርያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ይህ የብሔራዊ ባንክ ዝቅተኛ የተሽከርካሪዎች የዓረቦን ምጣኔ የመድን ሰጪዎች ማኅበር አስጠንቶ ዝቅተኛ ዋጋ መሆን አለበት ብለው ካስቀመጡት ዋጋ ጋር በእጅጉ ይራራቃል፡፡

በጥናቱ ከተቀመጠው ዋጋ ከ35 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ ተደርጎበት የወጣ መመርያ ነው የሚሉት እኚሁ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎች፣ ይህም በሞተር ኢንሹራንስ ላይ እየደረሰ ያለውን ኪሳራ ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ብለው አያምኑም፡፡

ሆኖም ኢንዱስትሪውን ለመታደግ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ደረጃ ያወጣው መመርያ የመጀመርያው በመሆኑ ሊመሠገን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ አሁን የተጠቀሰው ዝቅተኛ የዋጋ ተመን ግን ኩባንያዎቹ ድጋሚ ጥያቄ የሚያቀርቡበት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም አስረድተዋል፡፡

ምክንያቱም አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ከሞተር ኢንሹራንስ ጋር በተያያዘ እየታዩ ያሉ በርካታ ችግሮች በመሆናቸውና በተለይ የመለዋወጫ ዕቃዎች የዋጋ ንረት የመድን ሽፋኑን እየሰጡበት ካለው የዓረቦን መጠን ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ በመሆኑ፣ አሁን በተቀመጠው ዝቅተኛ የዓረቦን ዋጋ ተመን ከችግራቸው ይወጣሉ ብለው እንደማያስቡም አመልክተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተለይ በዚህ ዓመት ሞተር ኢንሹራንስ ኪሳራ ውስጥ እንደከተታቸው የገለጹ ሲሆን፣ አሁን ዝቅተኛ የዓረቦን ዋጋ ወለል መውጣቱ ቢያስደስታቸውም የተቀመጠው ዋጋ አሁንም እንደሚስተካከል እምነት አላቸው፡፡  

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን ከ22.6 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ከጠቅላላ የዓረቦን ገቢያቸው ውስጥ ከ60 በመቶ የሚሆነውን የሚሰበስቡት ከሞተር ኢንሹራንስ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች