Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ የሚገኘው የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ከሥልጣናቸው ተሻሩ

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ የሚገኘው የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ከሥልጣናቸው ተሻሩ

ቀን:

በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት ከአቅም በላይ በመሆኑ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት በቀጥታ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር የሚገኘው የአማራ ክልል ምክር ቤት፣ በጤና እክል ምክንያት መልቀቂያ ማስገባታቸው የተገለጸው የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)ን ከሥልጣን በመሻር ተተኪ ፕሬዚዳንት ሾመ፡፡

በፀጥታ ችግር እየታመሰ የሚገኘውን ክልል ለሁለት ዓመታት ያክል ሲያስተዳድሩ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ተክተው የተሾሙት አቶ አረጋ ከበደ የሚባሉ ሲሆኑ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እስከተሾሙበት ዕለት ድረስ የአማራ ክልል የሥራ ፈጠራና ሥልጠና ቢሮ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ነበር፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የክልሉ ሚሊሺያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊም ነበሩ፡፡

አቶ አረጋ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሀመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለአማራ ክልል ከተሾሙ ፕሬዚዳንቶች ስድስተኛው ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ከእሳቸው በፊት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አቶ አገኘሁ ተሻገርና ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በሥልጣን ተፈራርቀዋል፡፡

ምክር ቤቱ በአዲሱ ርዕሰ መስተዳድር በዕጩነት የቀረቡትን የተለያዩ ሹመቶችም ያፀደቀ ሲሆን፣ በዚህም አቶ አብዱ ሁሴን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ብርሃኑ ጎሽም ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ መንገሻ ፈንታው ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊና ሌሎችንም ጨምረሮ 12 አዳዲስ የቢሮ ኃላፊዎችን አዲስ ሹመት ሰጥቷል፡፡

በክልሉ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲደረጉ የነበሩ ግጭቶች በከተሞች እንደቀነሱ ቢነገርም፣ በአንዳንድ ገጠራማ አካባቢዎች መቀጠላቸው ከተለያዩ ቦታዎች የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዱ በመድረኩ እንደተናገሩት ሕዝቡ ችግሮች እንዲፈቱለት ቢጠይቅ ቢጠይቅ ምንም መፍትሔ ሊመጣ ባለመቻሉ አሁን ከደረስንበት የፖለቲካ ቀውስ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህንን እውነታ መቀበል ይገባናል፣ መፍትሔ ይሆናል ብዬ የማስበውና የማስቀምጠው ጉዳይ ሕዝቡ ተበድሏል ብለን ከተግባባን ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅና ችግሮች እንዳይደገሙ ቃል መግባት ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በምክር ቤቱ ውሎ ሌላኛው አባል የዚህን ሕዝብ ሕመምና ቁስል በግልጽ በመረዳት ችግሩ በአጭር ጊዜ መፍታት ያለበትን ቶሎ መፍትሔ በመስጠትና የረዥም ጊዜ መፍትሔ የሚፈልጉትን ደግሞ በጊዜ ሒደት የሚፈቱበትን መንገድ መረጃ በመስጠት ሕዝቡ እንዲታገስ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህ መፍትሔ ካልተሰጠ ሕዝቡን እንዴት መምራትና መግባባት ይቻላል ብለዋል፡፡ አክለውም በየጊዜው ቃል መግባት ትክክለኛ ሕክምና አይሆንም መንግሥት ራሱን ይፈትሽ ብለዋል፡፡ ሌላኛው አባል እንደሚሉት ደግሞ በፖለቲከኞች ልፊያ ደሃው የአማራ ሕዝብ እየተጎዳና በሽኩቻ ደሃ የአማራ እናት እንድታለቅስና ገበሬው አምርቶ ሕይወቱን እንዳያሻሽል ሆኗል በማለት ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...