Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ልምዶች የሚያሳዩት የተሃድሶ ሥራው በሁለት ዓመታት ሊጠናቀቅ እንደማይችል ነው›› ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፣ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር

ትግራይን ማከል ያደረገው የሰሜ ኢትዮጵያ ጦርነት ከሁለት መታት አስከፊ የእርስ በርስ ልቂት በኋላ በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተጠናቀቀ ር ወራት ሊሞላ ጥቂት ቀናት ይቀሩታል። ስምምነቱን የተፈራረሙት የትና የፌራል መንግት ለጦርነቱ የተሰባሰቡትን ታጣቂዎች ትጥቅ በማስፈታትና የተሃድሶ ልጠና በመስጠት ተመልሰው ወደ ማበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚያስገድድ አንቀጽ በስምምነቱ ማካተታቸውም አይዘነጋም። በዚህም መረት ነበር የሚስትሮች ምክር ቤት ስምምነቱ በተካሄደ በጥቂት ቀናት ውስጥ የብራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንን ማቋቋሚያ ደንብ አርቅቆ ያደቀው። ሁለት መት ጊዜ እንዲኖረው ተደርጎ የተቋቋመው ኮሚሽንም በዚሁ መት በታሳስ ወር ነበር ‹‹የቀድሞ ታጣቂዎች›› በማለት በጦርነቱ ተሳትፎ ያደረጉትንና ትጥቅ የፈቱትን መደበኛ የማበረሰብ ክፍሎች ለመለየትና ድጋፉን ለመስጠት የዝግጅት ምዕራፉን የጀመረው። ትኩረቱን በትግራይ ክልል በሚገኙት ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በስምንት ክልሎች በሚገኙ ታጣቂዎች ላይ በማድረግትጥቅ ከፈቱ በኋላ ሚያልፉበት የተሃድሶ መር ግብር ላይ እየራ የሚገኘው ኮሚሽኑ፣ ‹‹የቀድሞ ታጣቂዎች›› በሚለው ማቀፍ ውስጥ የሚገቡትን ዜጎች የመለየትና ለነሱ ድጋፍ የሚያደርግበትን ብት ማሰባሰብ ላይ ሲራ ቆይቷል። ኮሚሽነር ሆነው ተቋሙን እንዲመሩ ባለፈው ሳስ ወር መጨረሻ ላይ የተሾሙት ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)ዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባነትን ጨምሮ በአገር ውስጥ ፖለቲካና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለበርካታ መታት በተለያዩ ቦታዎች ያገለገሉ ናቸው። የተሃድሶ ኮሚሽ እያከናወነ ስላላቸው ተግባራት፣ ስየሚያጋጥሙት ተግዳቶች፣ በኢትዮጵያ ስላለው ነባራዊ ሁኔታና የተሃድሶው ራ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንር የመሳካት ድሉ አጠያያቂነትን በሚመለከት ሳሙኤል ቦጋለ ከኮሚሽነሩ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል። 

ሪፖርተርለረመታት በገር ውስጥ ፖለቲካና በዲፕሎማሲው ዘርፍ  ማገልገልዎ ይታወቃል፡፡ አሁን ያሉበትን ላፊነት እንዴት ያዩታል?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- በሦስት አኅጉሮች በሚገኙ በስድስት አገሮች በዲፕሎማሲው ዘርፍ አገልግያለሁ፡፡ በተጨማሪም በአገር ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የካቢኔ አባልነትን ጨምሮ በብዙ ኃላፊነቶች ሠርቼ ነበር፡፡ የሕዝብ ተመራጭ ሆኜም አገልግያለሁ፣አሁንም በማገልገል ላይ ነኝ፡፡ በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የተሰጠኝ ኃላፊነት በዋናነት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተፈጠረው ጦርነት በርካታ ዜጎች ለጦርነት ተሰባስበው ስለነበር፣ የጦርነት ማቆሙ ስምምነት ከተደረገ በኋላ እነዚህን ዜጎች መልሶ ወደ ነበሩበት ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ በማስፈለጉ ነው፡፡ ኃላፊነቱ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ስንመለከተው የዲፕሎማሲ ሥራ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ የሚሠሩትን ሥራ ያካትታል፡፡ከዚያ አኳያ እኔ ከነበረኝ የፖለቲካም ሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ ብዙም የላቀ አይደለም፡፡ትልቁ ነገር ግን ሥራው ለአገር ያለው ፋይዳ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የቀድሞ ተዋጊዎች መልሶ ማቋቋም፣ የሰላም ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ፣ምርታማ እንዲሆኑና ካሁን በኋላ የሚኖራቸውን ሕይወት ያለ ጦርነት እንዲመሩ የማድረግ ሥራ በአገር ደረጃ ስናሰላው በጣም ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ሥራ ነው፡፡

ሪፖርተርበፖለቲካው ብዙ እንደ መቆየትዎ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለውን የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚ መዳከምስ እንዴት ይመለከቱታል? ዘላቂና አፋጣኙ መፍትሔስ ምንድነው ብለው ያስባሉ?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- የአገራችንን  ሁኔታ በሁለት መልክ ማየት እንችላለን፡፡አንደኛው በአዎንታዊ መልክ የምናያቸው ከኢኮኖሚ ጀምሮ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች አሉ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት ዋነኛ ችግሮች ውስጥ እያለፍን ነው ያለነው፡፡ ዋነኛው የሰሜኑ ጦርነት ነው፣ ሌላኛው ደግሞ ሁሉንም አገሮች የጎዳው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አለ፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ያለው ሁኔታ፣ በተለይም የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት በሁሉም አገሮች ላይ ያስከተለው ተፅዕኖ አለ፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባል እስከሆንን የዚህ ተፅዕኖ ተሸካሚ ነን፡፡ እነዚህን ችግሮች ከራሳችን አቅምና ከሌሎች አጋሮቻችን ጋር በመተባበር ለመፍታት ጥረት እያደረግንነው ያለነው፡፡ የኮቪድ፟-19 ወረርሽኝ አሁን ታሪክ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ያሳደረው ተፅዕኖ አሁንም አለ፡፡ ያንን ተፅዕኖ እንዴት አድርገን መሻገር እንችላለን? ለሚለው እየሠራን ነው ያለነው፡፡ የሰሜኑ ግጭት ከፍተኛ ጉዳት በአገሪቱ ላይ አሳድሯል፡፡ ይህንንም በተመለከተ የመጀመርያውና ትልቁ ነገር ካሁን በኋላ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግና የጦርነት አማራጭን ዝግ ማድረግ ነው፡፡ ሕዝቡ በብዙ ጦርነት ውስጥ አልፏል፡፡ በጦርነት ብዙ ተጎድተናል፣ስለዚህ ያንን ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ነው ብዙ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጦች እየተደረጉ ያሉት፡፡ በጎ ውጤቶችም እየተመዘገቡ ነው፡፡ ከፖለቲካ አኳያ ብዙ መግባባት ያልደረስንባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ከሕገ መንግሥቱ፣ ከታሪካችንና ከአስተዳደር ሥርዓታችን ጀምሮ ብዙ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ላይ መስማማት ባንችልም፣ ግን ለዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ፈጥረን የተቀሩትን በሕዝብ ምርጫና በሕዝብ ውሳኔ እያስኬድን መሄድ ይኖርብናል፡፡ የምክክር ኮሚሽኑም ትልቁ ፋይዳ እዚህ ላይ ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነት የሚቀር አይደለም፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ልዩነቶቻችንን የምናስተናግድበት መንገድ ላይ የጋራ መግባባት ሊኖረን ይገባል፡፡ ችግሮችን በውይይት የምንፈታበት ዘመን ነው እንጂ ለማንኛውም ዓይነት ችግር ጠመንጃ እያነሳን፣ ራሳችንን ወደኋላ እየወሰድን፣ ኢኮኖሚያችንን እየጎዳንና በዓለም ላይ ገጽታችንን እያበላሸን መቀጠል ያለብን አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከተቋቋመ ወዲህ በዋናነት ያከናወናቸው ተግባራት፣ ዕድሎችና ያጋጠሙት ተግዳሮቶች ላይ ትንሽ ገለጻ ቢያደርጉልን?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ከተፈረመው ስምምነት የተወለደ ተቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡ምክንያቱም በስምምነት ውስጥ ከተካተቱት ጉዳዮች አንዱ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ነው፡፡ ሥራው በሌላ ተቋም ተደርቦ እንዲሠራ አልተፈለገም፣ ምክንያቱም የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ካስፈታህ በኋላ መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይህን ሥራ በኃላፊነት እንዲሸከምና እንዲወጣ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንን አቋቁሟል፡፡ በመጀመርያ ሥራችን ተቋሙን የማቋቋምና የማደራጀት ተግባር ላይ ነበርን፡፡ እሱም ጊዜ ወስዶብናል፡፡ መጀመርያ ኮሚቴ በማቋቋም፣ ቀጥሎ ሠራተኞችን ከተለያዩ ተቋማት በዝውውር በማምጣት ሥራ ጀምረናል፡፡ አሁን እስከ 50 በመቶ ድረስ መዋቅሩን በማዘጋጀት ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ ተቋም፣ የሰው ኃይልና በጀት ሳይኖር ሥራ መሥራት ስለማይቻል ቅድሚያ ሰጥተን የተረባረብነው ተቋም መገንባት ላይ ነበር፡፡ አሁንም በቂ ባይሆንም ሥራውን ማንቀሳቀስ የሚያስችል ተቋማዊ አቅም አለን ብለን እናስባለን፡፡

የእኛ ሥራ በዋናነት የማቀናጀትና የማስተባበር ነው፡፡ አብዛኛውን ሥራ በዘርፍ መሥሪያ ቤቶችና በክልል ተቋማት፣ እንደዚሁም ደግሞ በግልና በሌሎች ዘርፍ የሚሠሩ ሥራዎችን በተቻለ መጠን የማስተባበርና የማቀናጀት ተግባር ነው የያዝነው፡፡ሥራ የሚመራበት የሥራ መርሐ ግብር መንደፍ ያስፈልግ ነበር፡፡ እሱን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ጋር በተመባበር የሌሎች አገሮችንና የእኛን አገር ልምድ በመቀመር አዘጋጅተናል፡፡ በዚህ ዙሪያ ላይም በርካታ የባለድርሻ አካላትን አወያይተናል፡፡ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ሊሳካ የሚችለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሲረባረቡ ነው፡፡ ይህ ሥራ በስምንት ክልሎች ነው ይሠራል ተብሎ የሚጠበቀው፣ ስለዚህ ከስምንቱም ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ ሌላኛው የፕሮጀክት ሰነድ መቅረፅ ነበረብን፣ እሱን ቀርፀናል፡፡ ከዚህ ጋርም ተያይዞ የፕሮጀክት ሰነዱ ላይ የእኛ ባለሙያዎችና የዩኤንዲፒ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ አድርገናል፡፡ እዚህ ላይ አንዱና ትልቁ የሚያስፈልገው ገንዘብ ነው፣ ምክንያቱም ሥራው ከፍተኛ የሆነ ሀብት ይፈልጋል፡፡በአገራችን ብዙ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ከመኖራቸው አኳያ ለዚህም ሥራ የሚያስፈልገውን ሀብት ማሰባሰብም ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም ጋር ያደረግነው ውይይት በምን ዓይነት መንገድ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው፡፡ የክልል መንግሥታትን ጨምሮ ሁሉም ቁርጠኝነት አላቸው፡፡ኢትዮጵያን የተረጋጋች አገር ከማድረግ አኳያ የዚህ ፋይዳ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የትጥቅ ማስፈታቱ ሥራ ሌላኛው እየተሠራ ያለው ሥራ ነው፡፡ የእኛ ሥራ ለጦርነት የተሰባሰቡ ሰዎችን አሁን ለሰላምና ለልማት ሥራ ማሰማራት ነው፡፡ ይህንንም ስናደርግ ማለፍ ያለባቸው ሒደቶች አሉ፡፡ አንዱ ማዕከል ላይ አሰባስበን በተቻለ መጠን የሥነ ልቦና ተሃድሶ፣ የፖለቲካ ተሃድሶ፣ እንዲሁም ሙያዊ ሥልጠና እናካሂዳለን፡፡ የተወሰነ ጊዜ ካምፕ ውስጥ ማቆየት አለብን፣ ይህንንም ለማድረግ ካምፖችም መዘጋጀት አለባቸው፡፡ በካምፕ ውስጥ የሚካሄዱ ሥራዎችን በተመለከተ የሥልጠና ዝግጅቶች እያደረግን ነው ያለነው ከሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር፡፡ ካምፖችንም እንዴት መጠገን አለብን? የሚለውንም እያየን ነው ያለነው፡፡ ካምፕ ውስጥ ደግሞ የሚቀርቡ ነገሮች አሉ፡፡ የምግብና መጠጥ፣ የደኅንነት፣ የጤናና የመሳሰሉ በካምፕ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ የሚቀርብላቸው ነገር አለ፡፡ ይህንን እንዴት ነው ማቅረብ የሚቻለው? የእኛ ድርሻና የክልሎች ድርሻ ምንድነው የሚለውን እየተወያየን ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻም ትግራይ ነበርኩ፣ በዚህ ላይ እየተነጋገርን፡፡

ሪፖርተር– በብሔርና በፖለቲካ ልዩነት ተደራጅተው ውጊያ ውስጥ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች ላይ ሚከሰቱ የአካል፣ የሥነ ልቦናና የኢኮኖሚ ችግሮችን በመቅረፍ በኩል  የኮሚሽኑ ዝግጁነት እንዴት ነው?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- ታጣቂዎቹ በጦርነት ውስጥ እንደማለፋቸው አጠገባቸው ሰው ሲሞት አይተዋል፣ በቤተሰቦቻቸውና በአካባቢዎቻቸው ላይ የደረሰ ጉዳት ሊኖር ይችላል፡፡ በብዙ የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ እንዳለፉና አንዳንዶቹም ከዚያ እንዳልወጡ እናውቃለን፡፡ ለዚህም ነው እነዚህን ሰዎች ወደ ማኅበረሰብ ውስጥ ከማስገባታችን በፊት ካምፕ ውስጥ መጀመርያ የሥነ ልቦና ተሃድሶ መሰጠት ያለበት፡፡ በሌሎች አገሮችም በልምድ የሚደረገው ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም የሥነ ልቦና ዝግጅት ሳያደርጉ ወደ ሥራ ማስገባት ችግር አለው፡፡ በተጨማሪም ካሁን በኋላ ጦርነትን እንቢ ብለው ለሰላም እሺ እንዲሉ ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እኛ በራሳችን አቅም ብቻ ሳይሆን በዚህ ላይ የተሻለ ልምድና ብቃት ያላቸውን ተቋማት እየለየን ነው ያለነው፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከአንዳንድ በዚህ ሥራ ላይ ልምድ ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አብረን ነው ሥልጠና እንዲሰጥ የምናደርገው፡፡ አንዳንዶች በራሳቸው ወደ አካባቢያቸው የሄዱ አሉ፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር ሲነጋገሩ የተወሰነ ሸክምን እያቀለለም ይሄዳል፡፡ የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው አሉ፡፡ ሁሉም የቀድሞ ተዋጊዎች አንድ ዓይነት አይደሉም፡፡ ሊገጠን የማይችል የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰው አለ፣ መካከለኛና ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰውም አለ፡፡ እንደ ፍላጎታቸው ለእያንዳንዱ ድጋፍ ለማድረግ እየሠራን ነው ያለ ነው፡፡ በእኛ ግምገማ የዝግጅት ሥራው ጥሩ እየሄደ ነው ያለው፡፡ ለዕርዳታም ዝግጁ ነን የሚሉ አካላት አሉ፡፡ ነገር ግን መጀመርያ መጠቀም የምንፈልገው የአገር ውስጥ አቅምን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዜጎችን በቡድን አደራጅቶ ወደ ጦርነት የከተተው የፖለቲካ ልዩነትና አለመስማማት አሁንም አለ እኮ? ይህን ልዩነት ማጥበብ ነው ወይስ ወደ ተዋጊዎች መሄድ መቅደም የነበረበት? የፖለቲካውን ልዩነት መፍታት ቅድሚያ ሊሰጠው አይገባም ነበር?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- የፖለቲካ ልዩነቱ የሚደረገው በፖለቲካ አመራሮች ነው፣ አሁን እየተደረገም ነው ያለው። ስምምነቱ ብዙ ክፍሎች ነው ያሉት፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሟል፣ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንም በትግራይ ተመልሶ እንዲተከል ሆኗል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ አለ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ወደ ቀዬአቸው የመውሰድ ጉዳይ አለ፣ እንዲሁም የእኛ የተሃድሶ ሥራ አለ፡፡ በአጠቃላይ መሠረተ ልማትና ኢኮኖሚን መልሶ የመጠገን ሥራዎችም በገንዘብ ሚኒስቴር አማካይነት እየተከናወኑ ነው ያሉት፡፡ የፖለቲካ ሥራ ሲባል መታየት ያለበት የሰላም ስምምነቱን በተሟላ መንገድ የመፈጸም ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከአቅም ጋር ተያይዞ የሚዘገዩ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም የሰላም ስምምነቱ አንቀጾች እየተተገበሩ ነው ያሉት፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶች በውይይት የሚፈቱ ናቸው፡፡ የፖለቲካና የፖሊሲ አቋም ልዩነት ስላለን ተብሎ የቆመ የሰላም ስምምነቱ አካል የለም፡፡ ሁሉም እየተተገበረ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተርኮሚሽኑ ለሁለት ዓመታት እንዲቆይ ሆኖ ከተቋቋመ ዘጠኝ ወራት ተቆጠሩ፡፡ በቀሩት አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሥራው ሙሉ ለሙሉ ይሳካል? እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎችን ውጤት እንዴት ነው የሚገመግሙት?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- ለኮሚሽኑ የተሰጠው የሥራ ዘመን ሁለት ዓመት ነው በደንቡ መሠረት፡፡ እዚያው ደንቡ ላይ ደግሞ ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልገው ከሆነ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊራዘም እንደሚችልም ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተሠሩ ሁለት ትልልቅና መለስተኛ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች አሉ፡፡ የእነዚህ ልምድም ሆነ የሌሎች አገሮች ልምዶች የሚያሳዩት ሥራው በሁለት ዓመታት ሊጠናቀቅ እንደማይችል ነው፡፡ እኛ ግን እየሠራን ያለነው በተሰጠን የጊዜ ገደብ መሄድ የምንችለውን ያህል እንድንሄድ እየሠራን ነው፡፡ እንደ ተመድ ዓይነት የልማት አጋሮቻችን በሚሰጡን አስተያየት መሠረት እስካሁን ሒደታችን ጥሩ እንደሆነ ቢነግሩንም፣ እንደ ኮሚሽኑ ኃላፊነቴ በዚያ መርካት አልፈልግም፡፡ በተለይ የቀድሞ ተዋጊዎች ያላቸውን ፍላጎትና በእኛ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ስለምናውቅ በዚህ አንረካም፡፡ በተገናኘን ቁጥር ሁልጊዜ መቼ ወደ አካባቢያቸው እንደሚሄዱ ጥያቄ ስለሚያነሱ ያላቸውን ጉጉት እናውቃለን፡፡ ሒደቱ ጥሩ አይደለም በሚል አይደለም፣ ጥሩ ነው ግን ተጨማሪ ሥራ መሥራት አለብን በተቻለ መጠን፡፡ የፍላጎትና የምኞት ጉዳይ ቢሆን በሁለት ዓመት በጨረስን፣ ግን ሊሆን እንደማይችል እያየን ነው ያለነው፡፡ ከሚመጣው ኅዳር በኋላ የሚቀረን የአንድ ዓመት አካባቢ ጊዜ ነው፣ በዚያ ጊዜም ይህን ሥራ ማሳካት እንደማይቻል ከአሁኑ እየታየ ነው ያለው፡፡ አይሳካም በሚል አይደለም ይህን የምንለው ግን በምንችለው እንድንገፋ ነው፡፡ እየሠራን ያለነውም በዚህ መንገድ ነው፡፡ አንድ ዓመት ከሠራን በኋላ የሚቀረን ሥራ ምንድነው የሚለውን እናያለን፡፡ እስካሁን ስንሠራ የቆየነው የዝግጅት ምዕራፍ የምንለውን ነው፡፡ ከተጀመረ እውነት ነው ሰባት ወይም ስምንት ወራት ቢሆን ነው፡፡ እኔ እንኳን ጥር ላይ ነው የጀመርኩት፣ ከዚያም ከአንድ ወር በኋላ ነው ምክትሎቹ የመጡት፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው የዝግጅት ምዕራፍ እየሠራን ያለነው፡፡ ትክክለኛውን ሥራ የጀመርነው በቅርቡ ነው፡፡ከሁለትና ከሦስት ወራት በላይ አይሆንም፡፡ እንዳልኩህ ልምድ ያላቸው የተመድ ሰዎች በፍጥነት መሄዱን ነው እየነገሩን ያሉት፡፡ ሥራው አጣዳፊ ስለሆነ በእርግጥ እኛ በዚህ አንረካም፡፡ በነገራችን ላይ ትልቁ ማነቆ ሆኖ ሥራችን በፍጥነት እንዳይሄድ የሚያደርገው ለሥራው የሚያስፈልገው ሀብትን በበቂ ሁኔታ አለማግኘት ነው፡፡ ለዚያም አሁን በተወሰነ ቁጥር ነው መጀመር የምንችለው እንጂ በከፍተኛ ቁጥር መጀመር አንችልም፡፡ ምናልባት እ.ኤ.አ. ከ2024 መጀመር በኋላ የተሻለ ሀብት ልናገኝ ስለምንችል ያኔ በትልቁ ቁጥር እንሠራለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተርበአንድ ወቅት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያስፈልግ ተገልጾ ነበር፡፡ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን አሁን ተከልሷል? የቀድሞ ተዋጊዎች ቁጥር ምን ያህል ነው?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- መጀመርያ ላይ የትጥቅ መፍታትና የተሃድሶ ፕሮግራም ሲወጣ የተዘጋጀ ግምት ነበር፣ አሁን እሱ ግምት ተሻሽሏል፡፡ አንደኛውና ትልቁ ምክንያት በወቅቱ ስንሠራ የነበረው ከሌሎች ተቋማት ባገኘነው የቀድሞ ተዋጊዎች ቁጥር ላይ ተመሥርተን ስለነበር ነው፡፡ ያኛው ቁጥር ለጅምር እንዲረዳን ብለን ነበር የያዝነው፡፡ በኋላም ያደረግነው ነገር ቢኖር ከመከላከያ ያገኘነውን መረጃ ይዘን ሌሎች ደግሞ አለን የሚሉትን የቀድሞ ተዋጊዎች ቁጥር ዝርዝር እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው። በቁጥሩ ላይ ልዩነት ነበር፡፡ እኛ ለምሳሌ ደንቡ ላይ በተቀመጠው መሠረት የቀድሞ ተዋጊ ማን ነው የሚለውን ስናጣራ ቁጥሩ መጀመርያ ከነበረው ከፍ ብሏል፣ ግን ክልሎች ይዘውት ከመጡት ደግሞ ያነሰ ነበር፡፡ አሁን የያዝነው የቀድሞ ተዋጊዎች ቁጥር ከ371 ሺሕ በላይ ነው፡፡ ይህ ቁጥር ከሁሉም ክልሎች የተገኘ፣ በኋላም ከመከላከያ ጋር ቁጭ ብለን የተስማማንበት ነው፡፡

ሪፖርተርጅማሮው ላይ በ250 ሺሕ ተዋጊዎች ቁጥር ነበር የታቀደው አይደል?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- በእርግጥ ጅማሮው ላይ የትግራይ ክልል ቁጥር ብቻ የተወሰደበት ሁኔታ ነበር፡፡ በኋላም ከመከላከያ ያገኘነው ቁጥር ነበር፣ እኛም ደግሞ ይህን ያህል ቁጥር ይዘን ለጊዜው ብንሠራ ይሻላል ያልነው ነበር፡፡ ስለዚህ ጥሩ የሚሆነው አሁን የተስማማንበት መጨረሻ ላይ ያለውን ቁጥር መውሰድ ነው፡፡ 371 ሺውን ይዘን ነው አሁን እየሠራን ያለነው፡፡ በፊት በኢትዮጵያ ከተደረጉት የተሃድሶ ፕሮግራሞች በላይ አሁን ብዙ ቁጥር አለ፡፡ ለዚህም ከፍተኛ የሆነ ሀብት ነው የሚያስፈልገው፡፡ የሥራው ባለቤት እኛው ነን፡፡ ዞሮ ዞሮ ሥራው መሠራት አለበት፣ አማራጭ ስለሌለን፡፡ መንግሥት የራሱን ድርሻ ይጫወታል፣ እስካሁንም ተቋም አቋቁሞ እየሠራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መረጋጋት ግድ የሚላቸው አካላት አሉ፣ ከእነሱም የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ይሠራል፡፡ የገንዘቡን መጠን አሁን መግለጽ አልፈልገም፣ ምክንያቱም የመንግሥትን ድርሻ መወሰን ይኖርብናል፡፡ ከአጋሮችም ጋር የጀመርናቸው ነገሮች አሉ፡፡ በመጨረሻም የፖሊሲ ውሳኔ የሚፈልጉ ነገሮችም አሉ፡፡ ይህ ውሳኔ እስኪተላለፍ ድረስ የገንዘቡን መጠን ለጊዜው ባልገልጽ ይሻላል፡፡

ሪፖርተርአሁን 371 ሺሕ ተዋጊዎች በካምፕ ነው የሚገኙት?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- አይደሉም፡፡ ግማሹ ካምፕ ውስጥ ናቸው፣ ሌሎቹ በየአካባቢው ነው ያሉት፡፡ ምን ያህሉ ካምፕ ውስጥ እንዳሉ በግልጽ መናገር አይቻልም፡፡

ሪፖርተርትልቁ ቁጥር ከትግራይ ክልል እንደሆነ ይገመታል፡፡ በየክልሉ ያሉትን በቁጥር መግለጽ ይቻላል?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- ትልቁ ቁጥር ያለው በእርግጥ በትግራይ ነው፡፡ ከተገለጸው 371 ሺሕ ውስጥ ወደ 70 በመቶ የሚሆኑት ትግራይ ናቸው፡፡ ቀጥሎ ኦሮሚያና አማራ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትልቅ ቁጥር ይዘዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወደ 5,000 አካባቢ እንገምታለን፣ በሌሎችም ክልሎች የተወሰኑ ቁጥሮች አሉ፡፡ እነዚህ ቁጥሮች አሁንም ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡ በኦሮሚያ የሚደረገው ስምምነት ባይቋጭም ተዋጊዎች በራሳቸው ትግሉን ጥለው መጥተው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እጅ የሰጡ በተሃድሶው ለማለፍ የወሰኑ አሉ፡፡ አሁን ይህን ቁጥር ይዘናል፡፡ ነገር ግን የሰላም ስምምነት በሚደረስበት ጊዜ ከአመፅ ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ይበዛል ብለን እናስባለን፡፡ በጋምቤላ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እንጠብቃለን፣ በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የተወሰኑ ቁጥሮችን እንጠብቃለን፡፡ በአፋርም በጋራ የተስማማነው ቁጥር አለ፡፡ ዋናውና ትልቁ ሥራችን፣ የስኬትና የውድቀት መለኪያ ሊሆን የሚችለው ግን በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚኖረው ሥራችን ነው፡፡ 

ሪፖርተርክልሎች ዘንድ አሁንም የቁጥር ልዩነቶች አሉ?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- አሁን ልዩነት የለም ተስማምተናል፡፡ የሚጨምር ሊኖር ይችላል፣ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች፡፡ ይህ ካልሆነ በስተቀር ልዩነት የለንም፡፡

ሪፖርተርበአሁን ጊዜ በካምፕ ተሃድሶ ላይ ያሉ አሉ፣ ከዚህ በኋላም የሚገቡ ይኖራሉ፡፡ መቼ ነው የመጀመርያው ዙር ተሃድሶ ተጠናቆ ወደ ማኅበረሰቡ መቀላል የሚጀመረው?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- መቼ እንደሚሆን ብዙ ቀናትን አቅደን ነበር፡፡ ለሥራው የሚፈለገውን ሀብት ከማፈላለግና ከቴክኒክ ዝግጅት ፍጥነት አኳያ ይህን ዕቅድ ማሳካት አልቻልንም። የካምፕ ዝግጅትና ሌሎች ዝግጅቶችም ከእኛ ቁጥጥር ውጭ በሚሆኑበት ሁኔታ የሚዘገይበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ አሁን የመረጥነው አካሄድ የእኛን ዝግጅት ጨርሰን ለሥራው ማስፈጸሚያ ሀብት ስናገኝ በዚህ ቀን ይተገበራል ብለን እናሳውቃለን፡፡ ከዚህ በፊት በመስከረም ብለን አስበን ነበር፣ ግን ያንንም በግልጽ ተናግረን ነበር፡፡ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው ብለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንም ትጥቅ ያልፈቱ አሉ፣ ግጭቶችም እየተስፋፉ ነው፡፡ ትጥቅ ቢፈቱም የድጋፍ እጥረት እያጋጠማቸው ነው፡፡ የተሃድሶ  ኮሚሽን ገና በዝግጅት ላይ ሆኖ ተግዳሮቶቹ አልበዙም?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- ትጥቅ ማስፈታት የእኛ ሥራ አይደለም፡፡ የመከላከያ ሥራ ነው፡፡ መከላከያ ደግሞ ትጥቅ እያስፈታ እንደሆነ፣ በተለይ የከባድና የመካከለኛ ደረጃ ትጥቆችን እንዳስፈታ በአደባባይ ተገልጿል፡፡ ከመከላከያ ጋር ባለን ግንኙነት ይህ ሥራ በተሳካ ሁኔታ እየሄደ እንደሆነና የእኛን ሥራ የሚያደናቅፍ እንዳልሆነ በግልጽ ተነጋግረናል፡፡ ሦስተኛው የነፍስ ወከፍ ወይም ቀላል የሚባሉት መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ ወደ ተሃድሶ ሲመጡ በመጀመርያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር፣ እዚያው ለምዝገባ ሲመጡ የያዙትን ትጥቅ እንዲያስቀምጡ ይደረጋል፡፡ እንግዲህ ከፌዴራልም ሆነ ከትግራይ ክልል የፖለቲካ አመራሮች ጋር ውይይት በተደጋጋሚ አድርገናል፡፡ በሁለቱም በኩል ጦርነትና እንደገና ወደ ግጭት መልሶ የመግባት ምንም ዓይነት ፍላጎት የለም፡፡ ጦርነት እንደማይጠቅም፣ ችግር አለ ቢባልም ችግሩ በውይይት መፈታት አለበት የሚል ፅኑ እምነት በፌዴራል መንግሥትም ሆነ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር ላይ እንዳለ ነው የሚያሳየው። ይህ በሚዲያው ወደ ጦርነት ተመልሶ ይኬዳል እየተባለ የሚቀሰቀሰው ነገር በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ነው ብዬ አላስብም፡፡ እኔ ደግሞ አመራሮቹ የሚያሳዩትን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ የማስገባት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በሁለቱ ዓመት ጦርነት የደረሰውን ውድመት እኮ አሁን ቁጭ ብለን እየቆጠርን ነው አይደል እንዴ?

ሪፖርተርበጉልበት ተነጠቅን የሚባሉ ቦታዎችን እናስመልሳለን እየተባለ የሚወራውስ?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- በሰላም ስምምነቱ እኮ እሱን በሚመለከት በግልጽ የተቀመጠ አቅጣጫ አለ፡፡ ድርድር ይካሄድበታል፣ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በሕጋዊ መንገድ ይፈታል ተብሏል፡፡ በእርግጥ ይህ ኮሚሽኑን የሚመለከት አይደለም፡፡ እኔ ግን እስከማውቀው ክርክር የተነሳባቸው ቦታዎች በሕጋዊ መንገድና በሕገ መንግሥቱ መሠረት መልስ ያገኛሉ፣ ሁለቱም ወገኖች ቁጭ ብለው ይደራደራሉ ነው የተባለው፡፡ ይህን ማድረግ ነው አሁን ትክክለኛ አካሄድ ተብሎ የሚታሰበው፡፡

ሪፖርተርበአማራ ክልል ከፍተኛ ውጊያ አለ፡፡ የዚህ ውጊያ ተሳታፊዎችም ተመልሰው ወደ ተሃድሶ መግባታቸው ይቀርም፡፡ ይህ የኮሚሽኑን ሥራ አያበዛውም?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- ይህንን የሚያነሱ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ የውጭ አጋሮቻችንም ይሄ ሁኔታ ተጨማሪ ሥራ አይፈጥሩባችሁም ወይ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ እኔ ግነ ስንደርስ ብናየው ጥሩ ነው የምለው፡፡ ቀደም ብሎ በአማራ ክልል የነበረ ሥራ አለ፣ በቁጥርም ከክልሉ ጋር የተስማማነው ነበር፣ ያ ቁጥር እንደተጠበቀ ሆኖ ግን የአሁኑ ሁኔታ ምን ሊያስከትል ይችላል? የሚለውን እሱም በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የሚቋጨው የሚለውን ማየት ይኖርብናል፡፡ ድልድዩን ስንደርስበት ብንሻገረው ይሻላል፡፡

ሪፖርተርስለዚህ ክለሳ መደረግ ካለበትም ይደረጋል?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- ድርድር ተደርጎ ወደዚህ ማዕቀፍ የሚገቡ ካሉ አዎ፡፡ ያው መንግሥትም ይህን በተጨማሪ ኃላፊነት ውሰዱ ብሎ የሚሰጠን ከሆነ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተርበትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ሰላማዊ ሠልፍ እስከ መውጣት ደርሰው ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ቶሎ ሳይደርስላቸው ቀርቶ ነው?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- በትግራይ ትጥቅ የፈቱ የቀድሞ ተዋጊዎች አሉ፡፡ ለእነሱ በመከላከያም በእኛም በኮሚሽኑ ሲሰጡ የነበሩ ፍጋፎች አሉ፡፡ መከላከያ አግዞን ቀለብ ከዚህ ይላክ ነበር፡፡ ተሸምቶና ተሰብስቦ እስኪደርስ ድረስ የተወሰነ መዘግየት ይፈጠራል። ለእነሱም ብቻ ሳይሆን ሥራ ላይ ላለውም መከላከያ የተወሰነ መዘግየት ይፈጠራል፡፡ ሰዎች ሠልፍ ቢወጡም ክልሉ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ችግሩ እንዳይፈጠር የሚያደርገው ጥረት ነበር፡፡ ችግሩ ወደ አመፅና ወደ ሌላ ነገር እንዳይተላለፍ ከመከላከያ ጋር ሆነን የተቻለንን ጥረት እያደረግን ነው ያለነው፡፡ በዋናነት ደግሞ ሁኔታዎችን ቁጭ ብለን እንነጋራለን፡፡ መቀሌ የሄድን ጊዜ ያነሳው አንደኛው ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ድጋፍ የሚዘገይበትን ሁኔታ እንዴት መቅረፍና ማፋጠን ይቻላል በሚል ነው የተወያየነው፡፡ ከመከላከያ በተሻለ ሎጂስቲክሱን በማንቀሳቀስ የተደራጀ ተቋም ያለ አይመስለኝም፡፡ እነሱ ደግሞ ድርብ ሥራ እያለባቸው የዚህን ሥራ ፋይዳ ስለሚረዱ እያገዙን ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ገብቶ ሊሠራ የሚችልበት ሁኔታ ካለም ለማየት እየሞከርን ነው፡፡

ሪፖርተርየድጋፍ መዘግየት ነው ሠልፉን ያስከተለው ማለት ይቻላል?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- አዎ፣ እሱ ነው እኔ እስከማውቀው፣ እንጂ ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ የለውም፡፡

ሪፖርተርበቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትጥቅ ከፈቱ ታጣቂዎች መልሰው ወደ ጫካ የገቡ አሉ፡፡ ኮሚሽኑ ይህን እንዴት ያየዋል?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- ወሬውን እንዳንተ ሰምቻለሁ፡፡ ግን ከወሬ ያለፈ አድርጌ አልወሰድኩትም፡፡ እኔ የማውቀው እውነታ አለ፣ እዚያም ሄጄ ከክልሉ ፕሬዚዳንት አሻድሊ ጋር ተወያይቻለሁ፡፡ የቤኒሻንጉልን ትንሽ ለየት የሚያደርገው ሁኔታ አለ፡፡ ክልሉ በፌዴራል መንግሥት ታግዞ ከጉምዝም ከቤንሻኒጉልም ታጣቂዎች ጋር ተደራድሮ   እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ጎረቤት አገር የነበሩትን ሁሉ መልሰው አምጥተዋቸዋል፡፡  ክልሉ በራሱ አቅም ሲያግዛቸው ነበር፡፡ ግን ወደ መልሶ ማቋቋም የመግባቱን ሥራ እኛ በደረስንበት ጊዜ ተረክበናል፡፡ ይህንን ስናደርግ ከመቆየት የተነሳ አንዳንዶቹ ተስፋ የመቁረጥና የተገባልን ቃል አልተፈጸመም ዓይነት ድምፅ የሚያሰሙ የተወሰኑ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ እንዳይሆን ነው እኛ ፈጥነን መሄድ የምንፈልገው፡፡ የቀድሞ ታጣቂዎችም ተመልሰው ወደ ጫካ መግባት መፍትሔ እንደማይሆን መረዳት አለባቸው፡፡

ሪፖርተርከመንግሥትናለጋሽ አካላት በተጨማሪ የግል ዘርፉን የመሳሰሉ ሌሎች የአገር ውስጥ አካላትስ ትብብር ምን ይመስላል? ጥሪ እየቀረበላቸው ነው?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- የግል ዘርፉ ከዚህ በላይ መሳተፍ አለበት፣ ምክንያቱም በጦርነቱ ተጎጂ ነው፡፡ ለጦርነቱ ሁላችንም ተነስተናል፣ ግን አሁን ደግሞ ለሰላም መነሳት መቻል አለብን፡፡ የግል ዘርፉ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ገንዘብ የሌለው ደግሞ በተለያዩ መንገድ ሊረዳ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በሥራ ፈጠራ፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን ሥራ በመቅጠርና በማሠልጠን፡፡ አቅማቸውን በመገንባትና እንደ ሕክምና ዓይነት ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በማሳከምና በመርዳት ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ አቅም ያላቸውም በፋይናንስ ዘርፉ ሊያግዙን ይችላሉ፡፡ ለዚህ ሥራ በውጭ ድጋፍ ብቻ መተማመን የለብንም፣ ከራሳችን መጀመር አለብን፡፡ በውስጥ መጀመር መቻል አለበት በሚል እስካሁን ከግል ዘርፉ ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ ኅብረተሰቡን እንዲቀሰቅሱ ከሲቪክ ማኅበራትና ከሚዲያ አካላትም ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ አገራችን ወደ መልሶ ግንባታ ምዕራፍ የገባች ስለሆነ በአንዱ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም ዘርፎች የመልሶ ግንባታ አካል መሆን መቻል አለብን፡፡

ሪፖርተርቀደም ብለው ገልጸውት እንደነበረው በኢትዮጵያ ከተደረጉ ሁለት የተሃድሶ ፕሮግራሞች ልምድ ተወስዶ ነበር፡፡ እነዚያ ግን ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቁ ጦርነቶች በመሆናቸው ከዚህኛው ጋር ልዩነት የላቸውም?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- ይኼኛውን ጨምሮ ሦስቱም የየራሳቸው ዓውድ አላቸው፡፡ ለምሳሌ የመጀመርያው በደርግ ጊዜ የነበሩ የቀድሞ ወታደሮችና ከኢሕአዴግ እንዲቀነሱ የተደረጉ ነበሩ፣ ይህ ራሱን የቻለ ዓውድ ነው የሚሆነው፡፡ በሁለተኛው ጊዜ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ሲከሰት ከመደበኛው ሠራዊት በተጨማሪ ብዙ የሰው ኃይል መልምለን ነበር፡፡ ከዚህም ውስጥ ወደ 150 ሺሕ ኃይል መልሰን ለማቋቋም ተገደናል፡፡ በእርግጥ በ2010 ዓ.ም. ለውጡ ሲመጣ ከውጭ እንዲገቡ የተደረጉ ቁጥራቸው ትንሽ ታጣቂዎችም ነበሩ፡፡ ለማንኛውም አሁን ዋናው ነገር የተገባውን የሰላም ስምምነት ሁሉም አክብሮ መፈጸምና ማስፈጸም ላይ ነው፡፡ ይህ ሲሆን መተማመን ይፈጥራል፣ ሌላ አማራጭም እንዳይታሰብ ያደርጋል፡፡ ይኼኛው ፕሮግራም በዕርዳታና በድጋፍ ይሠራል የሚል ሐሳብ ይያዛል፡፡ በኋላም ከዚህ ብዙ ተጠቃሚ ለመሆንና ብዙ ጥቅም የሚገኝበት አድርጎ የማሰብ ነገር አለ፡፡ በተጋነነ ሁኔታ የሚጠበቅ ሲሆን ከራሳቸው የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሰዎች ጋር አለመግባባት ይኖራል፡፡ የራሳችንን ብቻም ሳይሆን የሌሎችም የተሳካ ሥራ የሠሩ አገሮች ልምድን ወስደናል፡፡ አንድ ቡድን በቅርቡ ወደ ናይጄሪያ ልከን ነበር፡፡ እዚያም እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችና የቦኮ ሐራም ሰዎችን እንዴት አድርገው አስተሳሰባቸውን ለመቀየር ካምፕ አስገብተው እንደሚያሠለጥኗቸው፣ እንዲሁም ይህ ከእኛ ሁኔታ ጋር እንዴት ሊሄድ እንደሚችል ዓይተናል፡፡ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የአፍጋኒስታንና የኮሎምቢያን ልምዶችን እያየን ነው፡፡ የተመድ አጋዦቻችን እነዚህ ልምዶች ለእኛ ይሆናሉ ወይም አይሆኑም የሚለውን እየቀመሩ ያመጡልናል፡፡

ሪፖርተርበሰሜኑ ጦርነትና በሌሎች አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች ወደ 28 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መውደሙና ይህንንም መልሶመገንባት ለአምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡ የኮሚሽኑ የገንዘብ ፍላጎት ከዚህ ትልቅ አገራዊ ፍላጎት ጋር እኩል ሄዶ የመሳካት ዕድሉን እንዴት ይገመግሙታል?

ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር)፡- የገንዘብ ሚኒስቴር ለሚመራው የመልሶ ግንባታ ፕሮግራም እንዳልከው ለአምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡ የእኛ የተሃድሶ ፕሮግራም እዚያ ውስጥ አለ፣ ግን የገንዘብ ግምቱን ለብቻው ይዘናል፡፡ በአገራችን ውስጥ ብዙ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን መመለስና ትጥቅ ማስፈታት ሊሆኑ ይችላሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው፡፡ ዋናው ቅንጅት ነው፡፡ እኛም በምናገኘው ሀብት የትኛውን ብናስቀድም ይሻላል? በሚል እናቀናጃለን፣ እየተናበብንና እየተነጋገርን እንሠራለን፡፡ አካሄዱም እንደዚያ ነው የሚሆነው፡፡ እኔ ለብቻዬ ዘመቻ አድርጌ ሌላው ለብቻው የሚያደርግ ከሆነ ለአገርም አዋጭ አይደለም፡፡ በአብዛኛው ድጋፉን ለማሰባሰብ የምንሄደው አንድ አካባቢ ስለሆነ መናበብ፣ ማቀናጀትና በትብብር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይህን የሚያስተባብር ግብረ ኃይል አለ፡፡ ሁላችንም አንድ ላይ እንቀመጥና የትኛውን ከየትኛው እናስቀድም የሚለውን እየተነጋገርን እንሠራለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...