Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየምዕት ዓመቱ ደጃዝማች ማስታወሻ

የምዕት ዓመቱ ደጃዝማች ማስታወሻ

ቀን:

ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ በዘውዳዊው ሥርዓት የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩና በአሁኑ ጊዜ የ99 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ‹‹ሕይወቴ ለአገሬ ለኢትዮጵያና ለወገኖቼ ኢትዮጵያውያን ዕድገት የነበረኝ የሥራ ጥማት›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡

ቀደም ሲል የታተመው የግለ ታሪክ መጽሐፋቸው ከ1917 እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የግማሽ ምዕት ዓመት አገራዊና ግላዊ ሁነት ይሸፍናል፡፡

በዛጎል የመጻሕፍት ባንክ አዘጋጅነትና በእንዳለ ጌታ ከበደ (ዶ/ር) አወያይነት መርሐ ግብሩ ባለፈው ሳምንት የተከናወነው፣ በኢትዮጵያ የሳይንስ አካዴሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነ ጥበባት ነው፡፡ ለውይይት የቀረበው ይህ መጽሐፍ፣ ከደራሲው የግል ታሪክ ባለፈ በደርግ ሥርዓት አለፍርድ የተጨፈጨፉት 60 የመንግሥት ባለሥልጣናት ለአገርና ለወገን ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ ለዚህም የነበራቸውን ዕውቀትና ብቃት በዝርዝር ይተርካል፡፡

ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተጋረጠባትን ሰው ሠራሽ ችግሮች እንዴት እንደተወጣችው በመጽሐፋቸው ካካተቱዋቸው ታሪክ አዘል ነጥቦች ጋር በማያያዝ ደራሲው ገለጻና ማብራሪያ አድርገዋል፡፡

ከተንፀባረቀው አስተያየታቸው ለመረዳት እንደተቻለው ኢትዮጵያ በዮዲት ጉዲት፣ በግራኝ አሕመድ፣ በአፄ ሱሲንዮስ ዘመንና በፋሺስት ጣሊያን ወረራ፣ እንዲሁም በ1953 ዓ.ም. የታኅሣሥ ግርግር (መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ) ጊዜያት የተለያዩ መከራና ችግሮች ገጥሟታል፡፡

ከዚህም ሌላ በ1966 ዓ.ም. በደረሰው የአብዮት ፍንዳታና በ1983 ዓ.ም. በደርግ መውደቅና ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን በእጅ ባስገባበት ጊዜያት ችግሩና መከራው ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰና በ2010 ዓ.ም. ከኢሕአዴግ መውደቅ ጀምሮ እስካሁን ባለው የለውጥ መንግሥት የታየው መከራና ችግር በከፋ ሁኔታ ደረጃ ላይ እንደረሰ ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት አነጋገር፣ የታኅሣሥ ግርግር የተከሰተው የእርሻ ክፍለ ኢኮኖሚውን ለማዘመን የወጣው ዕቅድና ለስኬታማነቱም የተከናወኑ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች እንደ ውስጥ እግር እሳት ያንገበገባቸው የውጭ ጠላቶች በጠነሰሱት ሴራ ነው፡፡

ከተከናወኑትም እንቅስቃሴዎች መካከል ዕቅዱን ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል በ1945 ዓ.ም. አዋጁ መውጣቱን ይገኝበታል፡፡ በአዋጁም መሠራት ሥራና መሬት የሌለውና ጭሰኛ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሌ ግማሽ ጋሻ መሬት እየወሰደ ግብርና እንዲያካሂድ፣ ባለሀብቶችም በነፍስ ወከፍ 50 ብር እየከፈሉ አሥር ጋሻ መሬት እንዲወስዱና ወደ ልማት እንዲገቡ፣ ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ እንደሚያመቻች በአዋጁ መደንገጉን አስረድተዋል፡፡

የቀረ ነገር ቢኖር ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ ማፈላለግ ነበር፡፡ ይህንንም ለማሳካት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በሁለት የአውሮፓ አገሮች ጉብኝት እንዳደረጉና በጉብኝታቸውም ወቅት ብድር/ዕርዳታ ጠይቀው ሳይሳካላቸው እንደቀረ፣ በስተመጨረሻም ከቀድሞው ሶቪየት ሶሻሊስት ሪፐብሊክ የ400 ሚሊዮን ሩብል ብድር እንዳገኙ ደራሲው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ዕቅዱንም የሚያስፈጽም አካል ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር ተቋቋመ፡፡ የቀድሞ ክብር ዘበኛ መሥራችና የመጀመሪያው ዋና አዛዥ የነበሩትን ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊም ሚኒስትር ሆነው የሥራውን አጀማመርና አካሄድ እየተከታተሉ እንዲያስፈጽሙ ሙሉ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህም ከሆነ በኋላ ወደ ግብርና መሰማራት የሚፈልጉ ሰዎችና ባለሀብቱም ጭምር የመነሳሳትና ዕቅዱንም ሙሉ ለሙሉ ወደ መሬት ማውረድ ጅማሮ ለመታየት በቃ፤›› ያሉት ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት፣ ኢትዮጵያ አፍሪካን፣ መካከለኛ ምሥራቅንና በከፊል የእስያ አገሮችን መመገብ የሚያስችል ለም፣ ድንግልና ለእርሻ ተስማሚ የሆነ ሰፊ መሬት እንዳላት፣ በዚህ ላይ ደግሞ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ መዘመን ሲታከልበት፣ በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ የመሆን አጋጣሚ ሊፈጥርላት እንደሚችል ነው የገለጹት፡፡ ይኼም ሁኔታ ይበልጥ ያንገበገባቸው የውጭ ጠላቶች እንቅስቃሴውን ለማኮላሸት ሴራ መጠንሰሳቸውን በስፋት እንደተያያዙት አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እጅግ ስትራቴጂካዊ በሆነ ቦታ ላይ መገኘቱ፣ ለቀይ ባህርና ለሰሜን ምዕራብ የህንድ ውቅያኖስ ያላት ቅርበት፣ ጂቡቲ ወደ እናት አገራዊ ኢትዮጵያ ለመመለስ ወራት ብቻ መቅረቱ፣ ሶማሊላንድም ከኢትዮጵያ ጋር ለመዋሃድ ጥያቄ ማቅረቧ ለውጭ ጠላቶቿ ሴራ መጎንጎን ጥንካሬ ማበርከቱን ነው የገለጹት፡፡

የተጎነጎነውንም ሴራ ተሳክቶ በወቅቱ የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ የነበሩት ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና ግብረ አበሮቹ የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንደተከሰተ፣ በዚህም የተነሳ ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ ተብለው የተጠሩትና በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በሚገኘው አረንጓዴ ሳሎን የታደሙት የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሹማምንት የነበሩ 19 ሰዎች በጥይት ተረሽነው መገደላቸውን ደራሲው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በዚህ ጊዜ በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ሰው ግድያው በተፈጸመበት አካባቢ መታየታቸው፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የውጭ ጠላቶች እጅ ያለበት መሆኑን ላሳደረው ጥርጣሬ እርግጠኝነት እንደሚያሳይ ነው ያመለከቱት፡፡

ከአብዮቱ ፍንዳታም በኋላ፣ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አባላት በአራተኛ ክፍለ ጦር ስብሰባ አድርገው ሲወያዩ፣ የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ የነበሩት ጄኔራል አበበ ገመዳና ሌሎቹም ባለሥልጣናት ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው አፄ ኃይለ ሥላሴን ወትውተዋቸው እንደነበር፣ አፄውም ‹‹አትንኳቸው!!›› የሚል መልስ እንደሰጧቸው ደራሲው ተናግረዋል፡፡

‹‹ሚኒስትሮቹም በየተራ እየተያዙ ለእሥር መዳረጋቸውን፣ ይህንንም አድራጎት የተቃወሙ ሚኒስትሮች ቅሬታቸውን ለአፄ ኃይለ ሥላሴ አመልክተዋል፡፡ አፄውም ‹‹ምንም አትሆኑም ታሰሩ፣ ሥራችሁ ያወጣችኋል፤›› ከማለት በስተቀር ምንም ዓይነት ዕርምጃ አልወሰዱም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አፄው ችግሩ በራሳቸው ላይ የሚመጣ መስሎ ስላልታያቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህም ሆኖ ከአብዮቱ ፍንዳታ ጋር ተያይዞ የመጣው ችግርና የከፋ ሁኔታ በአሁን ጊዜ እየተባባሰና እያደገ መምጣቱ በገሃድ መታየቱን ገልጸው፣ በጎሳና በብሔር በሃይማኖትም መከፋፈል ተወግዶ በምትኩ ሰላምና መረጋጋት ከተፈጠረ የኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት መምጣቱ እንደማይቀር ነው የተናገሩት፡፡

በአንድ መድረክ እንደተገለጸው፣ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት በንጉሣዊው አገዛዝ ዘመን (ቅድመ 1967) የወላይታ አውራጃ አስተዳዳሪ የነበሩ ሲሆን፣ ፈር ቀዳጅ ሐሳብ አፍላቂና በዘመኑ ከነበሩ የልማት አርበኞች መካከል ከፍ ብለው ከሚነሱት አንዱ ናቸው፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...