Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናድምፃዊ አቡሽ ዘለቀ የሲዲ ቅጂውን እንዳያሠራጭ መከልከሉን ተናገረ

ድምፃዊ አቡሽ ዘለቀ የሲዲ ቅጂውን እንዳያሠራጭ መከልከሉን ተናገረ

ቀን:

ከሰሞኑ ‹‹እንደ አባቴ እወድሻለሁ›› የሚል አዲስ አልበም የለቀቀው በኦሮሚኛና በአማርኛ ቋንቋ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው ድምፃዊ አቡሽ ዘለቀ፣ ያሳተመው የሲዲ ቅጂ እንዳይሸጥ መከልከሉን ተናገረ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ለሙዚቃ አድማጮች የሲዲ ቅጂዎቹን ለመሸጥ ሲዲ አዟሪዎች ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ተሰማርተው ነበር ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ አዟሪዎች ሲዲውን እንዳይሸጡ በፖሊሶች መከልከላቸውን ድምፃዊው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

እንደ ‹‹ጃልጂሎ›› እና ‹‹ሙዴ›› በመሳሰሉ ቱባ የቦረና ባህልን በተላበሱ ዘፈኖቹ የሚታወቀው ድምፃዊው እንደ ‹‹ኩጃ፣ አሞቴ›› እንዲሁም ‹‹ማሎ ኢንተሎ›› የመሳሰሉ ዘመናዊ ሙዚቃዎችን በኦሮሚኛና አማርኛ ቋንቋዎች ለአድማጮች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ በመጣ ወቅት ቀድመው ለውጡን ከደገፉ የኪነ ጥበብ ሰዎች አንዱ የሆነው አቡሽ፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የወሰዷቸውን የለውጥ ዕርምጃዎች ያወደሰበት ‹‹አነቃን›› የተሰኘ ተወዳጅ ነጠላ ዘፈን በወቅቱ ማበርከቱ አይዘነጋም፡፡

በአገር ጉዳይ በተለይ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጠንካራ ስሜት በማንፀባረቅ የሚታወቀው ድምፃዊው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአገሪቱ ያለውን አስተዳደር የሚተቹ ሙዚቃዎችን በመሥራት ይጠቀሳል፡፡ ‹‹ባይነገስ ቢቀር›› በሚል ርዕስ ያቀረበው ሙዚቃ በብዙዎች ዘንድ በአነጋጋሪነቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ ‹‹አውጡት ከፓርላማ›› የሚልና ሕገ መንግሥቱን ተቺ የሙዚቃ ሥራ ይዞ መምጣቱ ብዙ ሲያነጋግር ነበር፡፡

ይኸው ‹‹አውጡት ከፓርላማ›› ዘፈን ጨምሮ በአጠቃላይ 15 የሙዚቃ ሥራዎቹ የተካተቱበት አልበሙ ዓርብ ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በሁሉም የማኅበራዊ ትስስር ገጾችና የሙዚቃ መተግበሪያዎች ይፋ ተደርጎ ነበር፡፡ የዚህ አልበም ቅጂም በሲዲ እንዲሠራጭ ዕቅድ የነበረው ድምፃዊው፣ ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲዲ አዟሪዎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች መሰማራታቸውን ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ በተለምዶ 22 አካባቢ፣ ኡራኤል፣ ቦሌ፣ ብሔራዊና ለገሃር አካባቢዎች ሲዲ ሲያዞሩ የነበሩ ሻጮች አትሽጡ ተብለው መከልከላቸውን አክሏል፡፡

‹‹ቀስ በቀስ እያየን እስከ አሥር ሺሕ ሲዲ ለማሳተም ዕቅድ ይዘን ነበር፤›› የሚለው ድምፃዊው፣ ሆኖም ሲዲ አዟሪዎቹ እንዳይሸጡ በፖሊሶች መከልከላቸውን ገልጿል፡፡ ‹‹ቦታ ለውጣችሁ ሞክሩት ተብለን ለውጠን በተለያዩ አካባቢዎች ለመሸጥ ጥረት አድርገናል፣ ሆኖም ተመሳሳይ ችግር ነው የገጠመን፤›› ብሏል፡፡

ችግሩን በተመለከተ ወደ ሕግ አካላት ለመውሰድም ሆነ ወደ ሙዚቀኞች ማኅበርና ወደ ሌሎች ወስዶ መፍትሔ የማፈላለጉ ጉዳይ ላይ ገና አለመወሰኑን ድምፃዊው ተናግሯል፡፡ ‹‹ሲዲ ማሳተሚያው ዋጋው በጣም ጨምሯል፡፡ አልበሙ በሲዲ ሲታተም ብዙ ወጪ ወጥቶበታል፡፡ ብሩ ምንም አይደለም ነገ ተሠርቶ ይገኛል፡፡ ሁኔታው ግን ትንሽ ቅር ያሰኛል፤›› በማለት ነው የተሰማውን ስሜት የተናገረው፡፡

‹‹አልበሙን ሲዲውን ካሠራጨን በኋላ ልናስመርቅ ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡ እሱንም ካልከለከሉን በዚያን ጊዜ ጥቂት ሲዲዎችን ለማስታወሻ ሰዎች እንዲይዙት እናደርጋለን፤›› ብሏል፡፡ ያም ቢሆን ግን አሁን ባለው ሁኔታ እንዳስፈላጊነቱ ነገሮችን ማራዘምና መከለስ እንደሚኖርበት ነው ግምቱን የገለጸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...