Saturday, September 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ የገባችበት ቀውስ ሰላማዊ መቋጫ ያግኝ!

በአሁኗ ኢትዮጵያ አገር የሚያስተዳድረውን መንግሥት ጨምሮ፣ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንቀሳቃሾች፣ የተለያዩ አደረጃጀቶች አመራሮች፣ የመደበኛው ሚዲያና የማኅበራዊ የትስስር ገጾች ተዋንያን፣ በአክቲቪስትነትና በተንታኝነት የተሰማሩና የመሳሰሉት አገር ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ይልቅ በስሜት በሚነዱ ምስቅልቅሏ ሲወጣ የራሳቸውን አዎንታዊና አሉታዊ አበርክቶ መገምገም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሩቅ ሆነው በሌላው መስዋዕትነት የሚፈልጉትን ለማስፈጸም እንቅልፍ አጥተው ከሚውረገረጉ ጀምሮ፣ አገር ውስጥ ሆነው ለሚፈጠሩ ችግሮች መላ ከመዘየድ ይልቅ በእሳት ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፉ እየበዙ ነው፡፡ ጥቂቶች በተቆጣጠሯቸው የመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት ቂማቸውንና በቀላቸውን ለመወጣት በግራና በቀኝ ተሠልፈው እሳት ሲያቀጣጥሉ፣ ብዙኃኑ ሕዝብ ግን የሚያዳምጠው አጥቶ በዛሬውና በነገው መካከል ምን ሊፈጠርበት እንደሚችል እያሰበ በሥጋት ሕይወቱን እየገፋ ነው፡፡ ያለ ኃጢያታቸው ፍዳ የሚያዩ ኢትዮጵያውያን ከሸፍጥና ከሴራ ፖለቲካ የሚገላግላቸው አጥተው፣ አገራቸው በየዕለቱ ሰላም እየራቃት ከድጡ ወደ ማጡ እየተሸጋገረች ማቆሚያው ካልታወቀ ከዛሬ ይልቅ የነገው ጉዳይ በእጅጉ ይጨንቃል፡፡ መንግሥትም ሆነ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ እየመጣ ያለውን መከራ ይገንዘቡ፡፡

ለአገራቸው በጣም ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ሊያበረክቱ የሚችሉ የተከበረ ሙያ ያላቸው ሰዎች አገር ጥለው ሲሸሹ፣ ወጣቶች ማቆሚያ ባጣው ችግር በመመረር አስጨናቂውን የስደት መንገድ ሲመርጡ፣ የከተማም ሆነ የገጠር ነዋሪዎች ሰላማቸውና ደኅንነታቸው ተናግቶ መንቀሳቀስ ሲቸገሩ፣ በየቦታው ታጣቂዎች ንፁኃንን እያገቱ ሲገድሉና የማስለቀቂያ እያሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሲጠይቁ፣ በአጠቃላይ ለሰላም ያለው ተስፋ ደብዝዞ ቁዘማ ሲበዛ ከሕዝብ ጋር ተነጋግሮ መፍትሔ መፈለግ ካልተቻለ የአገር ህልውና የባሰ ሥጋት ውስጥ ይወድቃል፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ጥያቄም ሆነ ተቃውሞ ካላቸው ወገኖች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት በመፍጠር፣ ያጋጠሙ ችግሮች በሕጋዊና በፖለቲካዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ ተነሳሽነት መኖር አለበት፡፡ ከአውዳሚው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጉዳቶች ያላገገመች አገር፣ በብርሃን ፍጥነት ተመልሳ እዚያው ዕልቂትና ውድመት ውስጥ ስትገኝ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የተደረገው ግጭት የማስቆም ስምምነት ፊርማ ሳይደርቅ፣ በአማራ ክልል ውስጥ ሌላ ዙር አውዳሚ ግጭት መቀስቀሱ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡

ከጦርነት ወደ ጦርነት ከመግባት በፊት ችግሮችን በምክንያታዊነት ላይ በመመሥረት ለመነጋገር ዕድል መስጠት ይገባ ነበር፡፡ አገር በተደጋጋሚ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስትተዳደር በገጽታዋ ላይ ከሚፈጠረው አሉታዊ ዕሳቤ በተጨማሪ በሕዝብ ላይ እደረሱ ያሉ ተደጋጋሚ የሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣ የንብረት ውድመት፣ መፈናቀል፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሥነ ልቦና ቀውስና የመሳሰሉ አስከፊ ጉዳቶች ሊያሳስቡ ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአገር ኢኮኖሚ ላይ እየደረሰ ያለ ሊጠገን የማይችል ጉዳት አለ፡፡ አርሶ አደሮች አስፈላጊዎቹን የእርሻ ግብዓቶች አግኝተው በሰላም ማረስ ካልቻሉ ከፍተኛ የምርት እጥረት ያጋጥማል፡፡ ለኤክስፖርት የሚሆኑ ምርቶች በአግባቡ ተመርተው ወደ ውጭ የማይላኩ ከሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ይባባሳል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶች ካልተመረቱ ችግሩ የበለጠ እየከፋ ይሄዳል፡፡ ነጋዴዎች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውረው መነገድ ካልቻሉ፣ ኢንቨስተሮች በቢሮክራሲና በፀጥታ ችግር መሥራት ካቃታቸው፣ እንዲሁም ለኢኮኖሚው የሚበጁ ተግባራት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መደነቃቀፋቸው ከቀጠለ ተስፋ ቆራጮች ይበራከታሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በኮቪድ-19 እና በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ቀውስ አይረሳም፡፡ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠሙ ግጭቶች ካደረሱት ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት በተጨማሪ፣ ከ28 ቢሊዮን ዶላር በላይ ውድመት በደሃ አገር ላይ መድረሱ መቼም ቢሆን ታሪክ የማይዘነጋው የዘመኑ ዘግናኝ ክስተት ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አስደንጋጭ ክስተት ውስጥ በውጭ ኃይሎች ግፊት ከተወጣ በኋላ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ዶላር የመልሶ ግንባታ ዕርዳታ እንዲያደርግ ጥያቄ እንደቀረበለት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አሉታዊ ገጽታ ተይዞና ላወደምነው ዕርዱን ተብሎ እርጥባን እየተጠየቀ፣ ተመልሶ እዚያው አረንቋ ውስጥ ሲገባ ለጋሾቹ እንደ ወፈፌ ቢያዩን ሊገርም አይገባም፡፡ እነዚህ ችግሮቻቸውን በሠለጠነ መንገድ ተነጋግረው መፍታት ያቃታቸው ናቸው ብለው ጀርባቸውን ቢሰጡም፣ ጥፋቱ የእኛ እንጂ የእነሱ አይሆንም፡፡ ኢኮኖሚው እየደቀቀ የሰው ልጅ ምግብ ማግኘት የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ውጊያን መደበኛ ሥራ ማድረግ ያሳፍራል፡፡

በኢትዮጵያ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምክክር መስመር መያዝ የሚችለው፣ የአገር ጉዳይ ይመለከተናል ከሚሉ ወገኖች ጋር በሥርዓት ተቀምጦ መነጋገር ሲጀመር ነው፡፡ በኃይል ዓላማን ማሳካት እንደማይቻል በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተገታው የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ህያው ምስክር ነው፡፡ በአማራም ሆነ በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ትጥቅ ያነሱ ኃይሎች በሙሉ ወደ ምክክር መድረኩ እንዲመጡ የሚያስችል ዓውድ ይፈጠር፡፡ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ በፍጥነት ተገቶ በእኩልነት ለመነጋገር የሚያስችል የንግግርና የድርድር መድረክ ሲኖር፣ ቅሬታ ያላቸው ወገኖችም ሆኑ ድርጊቶችን በሐዘንና በትዝብት የሚመለከቱ በሙሉ ለመፍትሔ ፍለጋው ዕገዛ ለማድረግ ወደኋላ አይሉም፡፡ ከዚያ ውጪ እከሌ ይህንን አካባቢ ተቆጣጠረ፣ እንቶኔ ደግሞ ያንን ሥፍራ በቁጥጥሩ ሥር አዋለ የሚለው ፕሮፓጋንዳ ለአገር ሰላም ምንም አይፈይድም፡፡ እስካሁን የፈሰሰው ደም ይበቃል፡፡ ከዚህ በላይ መጨመር ጥፋቱን የበለጠ ያባብሰዋል እንጂ አይጠቅምም፡፡ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባችሁ ወገኖች በሙሉ የሕዝብ ሕይወት ለአደጋ እየተጋለጠ አገር ህልውናዋ እንዳያከትም ተባበሩ፡፡

ኢትዮጵያውያን በርካታ የመከራ ዘመናትን አብረው ያሳለፉና የሚጋሯቸው ብዙ አኩሪ ማኅበራዊ እሴቶች ሲኖሯቸው፣ በተለያዩ ማንነቶች የሚገለጹ ልዩነቶች መኖራቸው እስከማያስታውቅ ድረስ በጋብቻ ጭምር ተዛምደው አገራቸውን በጋራ ሲጠብቁ እንደነበር ለማንም ነጋሪ አያሻም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችም ይህንን ዘመን ተሻጋሪ አንፀባራቂ ታሪክ ያለውን ሕዝብ ቢመስሉ ኖሮ፣ ራሳቸውን ከአገር በላይ እየቆለሉ አገር ማመሰቃቀል የዘወትር ሥራ አያደርጉም ነበር፡፡ በፖለቲካ ሴረኝነት ከተካኑ አደገኞች ጀምሮ በደም እስከሰከሩ እኩያን ድረስ የሚፈጸመው ክፋት፣ ከዚህ ቀደም ለእናት አገራቸው ኢትዮጵያ በክብርና በፍቅር ሕይወታቸውን ሲሰጡ ለነበሩ ኩሩ ኢትዮጵያውያን የሚያንገፈግፍ የታሪክ ወረበላነት ነው፡፡ ለአገራቸው ከፍተኛ ጥቅም የሚኖራቸው ሥራዎችን ማከናወን የሚችሉ ብዙዎች፣ በአገራቸው ተስፋ እየቆረጡ የባዕዳን አገሮችን በር እንዲያንኳኩ የሚያደርገው ይህ ሴረኝነት በፍጥነት ይቁም፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ማግኘት የምትችለው በመከባበርና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ግንኙነት ሲኖር ነው፡፡ በመገፋፋትና በመበሻሸቅ እንኳን አብሮ መሥራት መተያየትም ስለማይቻል፣ ኢትዮጵያ የገባችበት ቀውስ ሰላማዊ መቋጫ ያግኝ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...