Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹የጎሳ ፖለቲካ›› አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ነው አሉ

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹የጎሳ ፖለቲካ›› አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ነው አሉ

ቀን:

  • መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲፈልግ ጠይቀዋል

ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና እናት ፓርቲ የተሰኙ የተፎካካሪ ፓቲዎች በወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹በጎሳ ፖለቲካ ዋጋ አየከፈለች ለምትገኘው ኢትዮጵያ›› መንግሥት መፍትሔ ይስጥ ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ የአገሪቱ ፖለቲካ እልህና ፉክክር የተጠናወተው ኋላቀር የሆነ የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ፣ በውስብስብ ሴራና በጥልቅ ጥላቻ የተበከለ ዕሳቤና መንገድ በመያዙ የአገሪቱን ችግርና መከራ የበለጠ እያራዘመው ነው ብለዋል፡፡

‹‹የብልፅግና መንግሥት የግብር ሳይሆን የስም ብቻ ቅያሪ አድርጎ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ የሕዝብ ብሶትን ከማድመጥና ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት ይልቅ፣ በእኔ ብቻ አውቅላችኋለሁ ‹የዕውር ድንብር ጉዞ› ሕዝባችንን ማጥ ውስጥ አገራችንን ደግሞ ከዕለት ወደ ዕለት ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እየከተታት ይገኛል፤›› ሲሉ በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡

በየቦታው የሚደመጡ ዋይታዎችና የድረሱልን ጥሪዎች በጆሮ ዳባ ልበስ እየታለፉና አንዱ ችግር በሌላው ችግር ላይ እየተደራረበ፣ መንግሥትም ባለፉት ተደጋጋሚ ጊዜያት የቀረቡ ጥሪዎችን ችላ እንዳላቸው ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል፡፡

እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የአማራ ክልል ዋና ዋና መንገዶች በመዘጋታቸው ለዕለት ጉርስና ጤና አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችና የፍጆታ ዕቃዎች ለሕዝብ መድረስ አለመቻላቸውን፣ ጤፍን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸውንና ጦርነቱ ከመጀመሩም በፊት የከፋ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ በሚገኘው ሕዝብ ላይ ተባብሶ የቀጠለው የኑሮ ቀውስ አሥጊና ሰቅጣጭ ደረጃ መድረሱን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በቅርቡ በተመሠረቱት የደቡብ ኢትዮጵያና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ከርዕሰ ከተማ መቀመጫነት ጋር በተያያዘ የተነሱ ጥያቄዎች እንዳይቀርቡ፣ መንግሥት እየወሰደ የሚገኘው ዕርምጃ ሌላ የቀውስ አቅጣጫ እየተከፈተ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የጋሞ ወጣቶች ያነሱትን ጥያቄ ተከትሎ በተወሰደ የኃይል ዕርምጃ፣ ከአሥራ ስምንት በላይ ንፁኃን ዜጎች መገደላቸውን ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አካተዋል፡፡

የሚታዩት ችግሮች አገር እንድትከተል ከተደረገው የጎሳ ፖለቲካ የሚመነጩ በመሆናቸው፣ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚችለው በሕገ መንግሥቱ ላይ መሠረታዊ ክለሳ በማካሄድ ብቻ መሆኑን ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እጂ ይህ ሒደት እስከሚካሄድ ድረስ መንግሥት ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ተመልክቶ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ እንደሚገባው፣ የኃይል አማራጭ በየትኛውም መንገድ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ፓርቲዎቹ አሳስበዋል፡፡

በአማራ ክልልም ሆነ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን የኃይል አማራጭ ተጠቅሞ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ሙከራ፣ አገርን ወደ ከፋ ቀውስ የሚከት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡   

‹‹ከሕዝብ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቶና ውጊያ ገጥሞ ያሸነፈ መንግሥት የለም›› የሚለው የፓርቲዎቹ መግለጫ፣ ‹‹የመንግሥት ሥልጣን የጨበጡትን ከክብር ዝቅ አድርጎ ሊያሰናብት ወደ የሚችል አቅጣጫ ሊገፋ እንዲሚችል መተንበይ ከባድ አይሆንም፤›› ብሏል፡፡

‹‹መንግሥት በአማራ ክልል ያሰማራውን የመከላከያ ሠራዊት በአስቸኳይ አስወጥቶ የአገራችን ዳር ድንበር ሊጠብቅ ወደ የሚችልበት መደበኛ ሥራው እንዲመልስ፣ ለአስቸኳይ አገር አድን ውይይት በሩን ክፍት በማድረግ ችግሮች በውይይትና ድርድር ብቻ እንዲፈቱ፤›› በማለት ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፓርቲዎቹ መንግሥት በክልል ምሥረታ ስም እያከናወነ የሚገኘው የክላስተር ጥርነፋ በቂ ጥናቶች ያልተደረጉበትና የተነሱ መሠረታዊ የማኅበረሰብ ጥያቄዎችንና ውሳኔዎችን ያላገናዘበ ስለሆነ፣ በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተገቢው ማስተካከያ እስኪደረግ በጊዜያዊነት ታግዶ በድጋሚ እንዲታይም ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...