Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሸን ባንክ 40 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ብድር ማግኘቱን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱ ንግድ ባንኮች ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት በውጭ ምንዛሪ መበደር እንዲችሉ ከሁለት ዓመት በፊት ፈቃድ የሰጠበትን መመርያ በመጠቀም ዳሸን ባንክ ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት 40 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘቱ ተመለከተ፡፡

ባንኮች ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት ተበድረው ለውጭ ንግድ መቀላጠፊያ አገልግሎት ሊያውሉ ይችላሉ በሚለው መመርያ መሠረት፣ ዳሸን ባንክ 40 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከሁለት የአውሮፓ የፋይናንስ ተቋማት ማግኘቱ ታውቋል።

ዳሸን ባንክ ይህንን ብድር አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ብድሩን የሰጡት የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት (ቢአይአይ) እና የኔዘርላንድ የሥራ ፈጠራና ልማት ባንክ የሆነው ኤፍኤምኦ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ ሁለቱ የፋይናንስ ተቋማት እያንዳንዳቸው 20 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 40 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለዳሽን ባንክ ማቅረባቸው ታውቋል።

ሁለቱ የፋይናንስ ተቋማት ለዳሸን ባንክ ብድሩን መፍቀዳቸውን በይፋ ያሳወቁ ሲሆን፣ ይህ የብድር አቅርቦት ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን የግብርና ምርት ለማሳደግና በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ለማሻሻል የሚያስችል ይሆናል ተብሏል፡፡ 

‹‹ቢአይአይ›› እና ‹‹ኤፍኤምኦ›› ለዳሸን ባንክ ያቀረቡት ገንዘብ በኢትዮጵያ 80 በመቶ የኅብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት፣ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 39 በመቶ ድርሻ ላለውና ለወጪ ንግዱ 90 በመቶ አስተዋጽኦ ለሚያበረክተው  የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ዕገዛ እንደሚኖረው ዳሸን ባንክ አስታውቋል፡፡

የቀረበው ብድር ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ለሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግለትና፣ በተለይም በግብርና ሥራ ላይ ለተሰማሩ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ግብዓቶችን በማሟላት ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ዳሽን ባንክ ገልጿል።

የፋይናንስ ተቋማት ትብብር ለግሉ ዘርፍ ዕድገት ጉልህ ሚና እንዳለው ባንኩ አስታውቆ፣ በዚህ ትብብር ‹‹ቢአይአይ›› እና ‹‹ኤፍኤምኦ›› የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የውጭ ምንዛሪ ማቀላጠፊያ መመርያ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ለሚገኝ የፋይናንስ ተቋም በውጭ ምንዛሪ የቀረበ የረዥም ጊዜ ብድር ሲሰጡ የመጀመሪያዎቹ መሆናቸውንም ጠቅሷል፡፡ ይህ ፋና ወጊ ተግባር ገበያውን በማነቃቃት ከዓለም አቀፍ ፋይናንስ አቅራቢዎች ተጨማሪ ሀብት ለማሰባሰብ መተማመንን ለመገንባት የሚያግዝ መሆኑንም የባንኩ መረጃ አመላክቷል፡፡

የፋይናንስ አቅርቦቱ በግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ የተሰማሩ አምራቾችና ነጋዴዎችን የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበትና በኢትዮጵያ የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ አጋዥ እንደሚሆንም ጠቅሷል፡፡ 

በብድሩ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ፣ ‹‹በውጭ ምንዛሪ የቀረበው ብድር በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ደንበኞችን ለማገዝ እንደሚውልና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ባንካችን ከሁለቱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሥራቱ ለአገር የሚተርፍ በርካታ ልምድ፣ ዕውቀትና የአሠራር ዘይቤ እንዲቀስም ያግዘዋል፤›› ብለዋል።

የቢአይአይ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የፋይናንሺያል አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት ስቴፈን ፕሪስትሊ  በዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ላይ የመጀመሪያዎቹ ተቋማት በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ቢአይአይ በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በፊት ኢንቨስት ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት ቢአይአይ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ ቀዳሚው እንደሆንም ተናግረዋል።

የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት፣ ‹‹ከኤፍኤምኦ ጋር የደረስንበት አጋርነት ወደ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በልማት የፋይናንስ አቅራቢዎችና የንግድ መዋዕለ ንዋይ አንቀሳቃሾች ትብብር ሊመጣ የሚችለውን ከፍ ያለ ሀብት አመላካች ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኤፍኤምኦ የፋይናንሺያል ኢንስቲትዩሽን ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ማርኒክስ ሞንስፎርት  በበኩላቸው፣ ዳሸን ባንክና  ኢትዮጵያ  የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲያገኙ በሚያስችለው በዚህ ፈር ቀዳጅ አጋጣሚ በመሳተፋቸው ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱ ባንኮች ከውጭ አበዳሪዎች ብድር መበደር የሚከለክላቸው ሕግ መሻሩንና ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት ብድር መበደር የሚያስችለውን መመርያ ያወጣው፣ ነሐሴ 2012 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡ መንግሥት ባንኮች ከውጭ አበዳሪዎች በውጭ ምንዛሪ እንዲበደሩ የፈቀደበት ዋነኛ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ምንጮችን ለማስፋትና የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ እንዲያስችል መሆኑን በወቅቱ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች