Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየህዳሴ ግድቡ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በጥቂት ቀናቶች ውስጥ ይጠናቀቃል ተባለ

የህዳሴ ግድቡ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በጥቂት ቀናቶች ውስጥ ይጠናቀቃል ተባለ

ቀን:

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት እየተካሄደ መሆኑንና በጥቂት ቀናቶች ውስጥ የታቀደው ሙሌት ይጠናቀቃል ተባለ።

በህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አለቃቅን በተመለከተ ከግብፅና ሱዳን መንግሥታት ጋር እየተደራደረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታና አራተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ያለምንም እንከን እየተከናወነ መሆኑን ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሰሞኑን አረጋግጠዋል።

አራተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ከዘንድሮው የዝናብ ወቀት በፊት ለመያዝ የሚያስችለው የግድቡ ከፍታ ግንባታ መጠናቀቁንና የውኃ ሙሌቱም በቂ ዝናብ በመኖሩ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች በቂ ውኃ እንዲያልፍ በማድረግ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ሪፖርተር ከባለሙያዎች ባገኘው መረጃ ደግሞ፣ አራተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ለመያዝ የሚያስፈልገው የግድቡ የመካከለኛ ክፍል ከፍታ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 600 ሜትር ወደ ሚፈለገው 625 ሜትር ከፍታ የማድረስ ሥራ ከተጠናቀቀ አንድ ወር አልፎታል። 

ይህንንም ተከትሎ አራተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ከተጀመረ መሰነባበቱን የጠቆሙት ምንጮቹ፣ ዘንድሮ በግድቡ የሚካሄደውን የውኃ ሙሌት ለማጠናቀቅ የቀረው የአንድ ሳምንት ዕድሜ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። 

በዘንድሮው ክረምት የሚያዘው የውኃ መጠን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተያዘው ድምር የውኃ መጠን ጋር ከሞላ ጎደል እኩል ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት ምንጮቹ፣ የዘንደሮውን የውኃ ሙሌት በተራዘመ ጊዜ ለማከናወን የተመረጠው በዚሁ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል። 

የዘንድሮውን ያህል የውኃ መጠን በአንድ ክረምት ተይዞ እንደማይታወቀው ሁሉ ወደፊትም ይህንን ያህል የውኃ መጠን በአንድ ክረምት የመያዝ ዕቅድ እንደሌለ ምንጮቹ ገልጸዋል።

በመሆኑም ዘንድሮ ለመያዝ የታቀደው የውኃ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ የውኃ ሙሌት ሒደቱ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች (ግብፅና ሱዳን) ላይ አሉታዊ ጉዳት እንዳያስከትል በማሰብ በተራዘመ ጊዜ እንዲከናወን መደረጉን አስረድተዋል። 

እስካለፈው ዓመት ክረምት ድረስ በሦስት ዙር በተካሄደው የግድቡ የውኃ ሙሌት የተያዘው አጠቃላይ የውኃ መጠን 22 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን፣ በዘንድሮ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት የሚያዘው የውኃ መጠን ግን 20 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እንደሚሆን ምንጮቹ ጠቁመዋል። 

በመሆኑም የዘንድሮው የውኃ ሙሌት ሲጠናቀቅ በግድቡ ጀርባ የሚተኛው አጠቃላይ የውኃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እንደሚሆን ገልጸዋል። ይህ የውኃ መጠን በንጽጽር ሲገለጽ ከሞላ ጎደል ሁለት ጣና ሐይቅን ይሆናል ብለዋል።

በግድቡ የውኃ ሙሌት ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ ባለሥልጣን በበኩላቸው ዘንድሮ የሚካሄድ የውኃ ሙሌት በታየዘው ዕቅድ መሠረት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን፤ ነገር ግን የውኃ ሙሌቱ እንዳለፉት ዓመታት በግድቡ አናት ላይ አልፎ እንዲፈስ ላይደረግ ይችላል ብለዋል።

በምክንያትነት ከጠቀሷቸው ነጥቦች መካከል አንዱ፣ ውኃው በግድቡ አናት ላይ እስኪፈስ ድረስ ሙሌቱን ማከናወን፣ ቀጣዩን የመካከለኛ ክፍል ግንባታ በፍጥነት ለማስጀመር የተያዘውን ዕቅድ ያስተጓጉላል የሚል ነው። ውኃው በግድቡ አናት እንዲፈስ ከተደረገ የግድቡን የመካከለኛ ክፍል ግንባታ ለመጀመር የውኃ መጠኑ ወደ ታች እስኪጎድል ድረስ መጠበቅን እንደሚጠይቅ፣ ይህ ደግሞ የግድቡን መካከለኛ ክፍል ከፍታ በፍጥነት ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ እንደሚያስተጓጉል አስረድተዋል። በተጨማሪም፣ ዘንድሮ ለመያዝ የታቀደው የውኃ መጠንን በዕቅዱ መሠረት ከመያዝ ባለፈ ውኃው ተትረፍርፎ በግድቡ አናት ላይ እንዲፈስ ማድረግ ኢትዮጵያን ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ያልተገባ ጫና ከማጋላጥና የግድቡን ፖለቲካ ከማጦዝ በስተቀር ፋይዳ እንደሌለው ገልጸዋል። 

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ የውኃ ሙሌትና አለቃቅን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል ባለፈው ሳምንት በግብፅ ከተማ ካይሮ እንደ አዲስ የተጀመረው ድርድር በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁና ሁለተኛ ዙር ድርድር በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ መገለጹ ይታወሳል።

የመጀመሪያው ዙር ውይይትን በተመለከተ መረጃ የሰጡት አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ በካይሮው ድርድር 16 አንቀፆችን የያዘ ረቂቅ ሰነድ ቀርቦ በዘጠኙ አንቀጾች ላይ የሦስቱ አገሮች ተደራዳሪዎች የየራሳቸውን አስተያየትና ሊታከል ይገባል ያሏቸውን አንስተው መጠናቀቁን ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...