Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአዲሱ ዓመት ሲቃረብ ቀልብን ወደ ሰላም አማራጮች መመለስ ያሻል

አዲሱ ዓመት ሲቃረብ ቀልብን ወደ ሰላም አማራጮች መመለስ ያሻል

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

አገራችን የለውጥ መንገድ ጀመረች በተባለችባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ተገማች ያልነበሩ ግጭቶችና ጦርነቶች ውሰጥ ከመግባት አልዳነችም፡፡ ከላይ ከላይ ሲታዩ የሥልጣን ሽኩቻ የሚቆሰቁሳቸው የእርስ በርስ ጦርነቶች ይምሰሉ እንጂ፣ የውስጥ ጦርነቶቹ (ግጭት የሚለው ቃል ስለሚያንስ) ከብሔር፣ ከእምንትና ከፖለቲካው ፅንፍ እየያዝ መምጣትና የመንግሥት የማስፈጸም አቅም መዳከም ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡ የዴሞክራሲ ምኅዳሩ መጥበብና የፖለቲከኞች ለመነጋገር አለመነሳሳትም የየራሳቸው አስተዋጽኦ ማድረጋቸው አልቀረም፡፡

በየአካባቢው በፖለቲካ አለመግባባትና ቅራኔ የሚቀሰቅሱ ጦርነቶች ደግሞ የአገርን ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት ከማውደም ባሻገር፣ “በቦሃ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ ድህነትና የኑሮ ውድነትን በማባባስ ወደ አጠቃላይ ቀውስ ነው የሚገፉን፡፡ እናም መጪውን አዲስ ዓመት ስንቀበል እንደ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ የችግሮቹን ሥረ መሠረት ለይቶ፣ ሁሉም ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይትና ዕርቅ እንዲመጣ ሳያሰልሱ መሥራት ይጠበቅብናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የግድም ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደሚታወቀው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ሁሉም የአቅሙንና የፍላጎቱን ያህል ያቅዳል። ከመጥፎ አመሎቹ ለመላቀቅ፣ በሙያው ክህሎት ለመራቀቅ፣ ትምህርቱን ለመጨረስ፣ የኑሮ ደረጃውን ለማሻሻል፣ ራሱ ለመማርና ልጆቹን ለማስተማር፣ ማኅበራዊ ግንኙነቱን ለማሳመር፣ ሥራውን በጥራትና በብዛት ለማከናወን፣ የአቅሙን ያህል ለመቆጠብ፣ ለመምረጥና ለመመረጥ፣ በጥቅሉ «ይጎዳኛል» የሚለውን ጥሎ «ይጠቅመኛል» የሚለውን ይዞ ለመቀጠል ያለውን አጋጣሚ ሁሉ ለመጠቀም ለራሱ ቃል ይገባል፡፡

መንግሥትም ቢሆን አገርን ከምስቅልቅል ቀውስ ውስጥ አውጥቶ በተስፋ ብርሃን ለማራመድ በቀጣይ ማድረግ አለብኝ ብሎ ማቀድ ግዴታው ነው፡፡ በተቀየረ ትውልድ ውስጥ ሆኖ በኖረው አመለካከትና ተግባር መራመድ አይቻልምና፡፡ እኔም አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ፡፡

የፖለቲካ በሩን ለውይይት ክፍት ማድረግ

የዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት መገለጫ ምርጫ ብቻ አይደለም፡፡ በየትኛውም ጊዜ ነፃ ውይይትና መደማመጥ እንዲዳብር መሥራት ያሻል፡፡ በእርግጥ ምርጫ የሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ የሚበጀንን ተወካይና የሚያስተዳድረንን መንግሥት ወደንና ፈቅደን በድምፃችን የምንመርጥበት፣ የማይበጀንን ደግሞ በካርዳችን የምንቀጣበትና ከሰጠነው ወንበር የምናነሳበት ዕድል ነው፡፡ ያን ለማድረግም ሆነ ለሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት ለመፍጠር የሚጠቅመው ግን ነፍጥ ማንሳት ሳይሆን በመተማመን፣ በድርድርና በመደማመጥ መግባባት ብቻ ነው፡፡

በየትኛውም ጉዳይና ጭብጥ ላይ ልዩነቶቻችንን ማጥበብ እንጂ፣ ልዩነትን በማስፋት የሚገኝ አገራዊ መፍትሔ የለም። ሁሉም ወገን ቢሆን የራሱ ጥያቄና የጥቅም ፍላጎት አለው፡፡ መፍትሔው ግን ነገሮችን በሚዛንና በሰጥቶ መቀበል መርህ ዓይቶ አቻችሎ መመለሱ ላይ ነው። ትናንት በትግራይና በኦሮሚያ፣ አሁን በአማራና በአንዳንድ የደቡብ አካባቢዎች ለሚነሱ አለመግባባቶች አማራጩ ኃይል ሊሆን አይገባም፡፡ ችግሮችን በግጭትና በጥይት እፈታለሁ ብሎ ማሰቡም ሆነ መነሳቱ ትክክልም አይደለም፡፡ መንግሥትም የሕዝብ ጥያቄዎችን የጥቂቶች እያስመሰለ በኃይል አፍኜ አገር አረጋጋለሁ ብሎ ማሰቡ አጉል ዕብደት ነው፡፡

ስለሆነም ከየትኛውም ነገር በፊት መደማመጥና ከልብ መነጋገር ከሁሉም ወገኖች የሚጠበቅ ነው፡፡ የፕሮፌሰር ህስቅያስ አሰፋ የሰላምና የዕርቅ ትርጉምና መንገዶች መጽሐፍ በገጽ 22 ላይ እንደሚያስረዳን፣ ሰዎች ብሶታቸውን ለመግለጽ ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ረብሻ ያደርጉ ይሆናል፡፡ ይህንን ሁኔታ የፖሊስ ኃይል (መከላከያ) በመላክ ለመስበር፣ ለመበተንና ለማቆም ይቻላል፡፡ ግን ይህን በማድረግ ብቻ ግጭቱን አቆምኩት ብሎ ማመን ራስን ማታለል ነው፡፡ ዋናው ነገር የግጭቱ ሥረ መሠረት ለሆኑት ብሶቶች ሁሉም ሊቀበሉት የሚችሉት መፍትሔ ማምጣት ነው፡፡

በየትኛውም አገር ሆነ የፖለቲካ ሁኔታ ከምርጫ ውጪ ሥልጣን የሚገኘው ሕገ መንግሥቱን፣ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር መሆኑን የታወቀ ነው። ይህ ደግሞ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። መጀመርያ ነገር ሥልጣን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ እንዲገኝ የሕዝብ ፍላጎት ነው። ሥልጣንን በአመፅ መቆናጠጥ አገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትም የለውም። እኛ ደግሞ ብዙ መከራ እንዳለፈ ሕዝብ ሥልጣንን በኃይል ከመፈለግ አባዜ ውስጥ መውጣት አለብን።

ሁለተኛ ነገር ሕገ መንግሥቱን እንዲያከብርና እንዲያስከብር የሕዝብ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ሕገወጥ የሥልጣን ጥማትን ለማርካት የሚፈልጉ ቡድኖችን የመቆጣጠር ሥራውን በብቃት መወጣት አለበት። አሁን ባለው ሁኔታ ቀድሞ ችግሮች ወዴት እንደሚሄዱ ተገንዝቦ እርምት ማድረግ አለመቻል ነው፡፡ መንግሥት ሕጋዊውን መንገድ እስከተከተለና ሰብዓዊነትን እስካስቀደመ ድረስ እጁን አጣጥፎ ሊመለከት አይችልም፣ መብትም የለውም። ከሁሉ በፊት ግን ሕዝብን ማዳመጥና አካሄዱን ከእውነታው ጋር መቃኘት ነው ያለበት፡፡ በደመነፍስ አገር አይመራም፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ መንግሥት የሚወስደው የፖለቲካ ወይም የሕግ ዕርምጃ መኖር አለበት። የግድም ነው፡፡ የጉልበት አማራጭ ግን ሁልጊዜም ቢሆን ዋነኛ ምርጫ ሊሆን አይችልም፣ አይገባምም፡፡ እናም አሉ የሚባሉ ጥያቄዎችን በመደማመጥና በሰላም ከመመለስ የተሻለ ዕድል የለንም ብሎ ማሰብ የሚችል ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት መታጠቅ ያስፈልጋል፡፡

እናም ነገሩን ሁሉ በቅን ልቡና ስናየው ያለውን መንግሥት ወይም ሥርዓት በጎዳና ላይ ነውጥና በኃይል ለመናድ ከመጣደፍ ይልቅ፣ ለጋራ አገር ደኅንነት ሲባል ሰላማዊ ትግል ማስቀደም ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ቢሆን ወገንን በወገን ላይ የሚያባላና የታሪክ ጠባሳ የሚያሳርፍ ጦርነት ከማባባስ መቆጠብ ነው ያለበት፡፡ በመሆኑም ሁሉም ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲሰባሰብ ፈጥኖ መድረኮችን ማመቻቸት ግድ ይለዋል፡፡ እውነተኛ ለውጥም ይጀምር፡፡

ይህን ስል በአገሪቱ ላይ ችግሮች የሉም ማለት አይደለም። ችግር የሌለበት አገር ከሰማይ በታች የለም። አብዛኞቹ ችግሮቻችን ግን (የሥርዓት ለውጥን ጨምሮ) በመነጋገር፣ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ራስ ወዳድነትና ስግብግብነትን አደብ እስካስገዛናቸው ድረስ፡፡ ሁሉም ችግሮች በመነጋገርና በመግባባት ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው ሲባል ግን፣ ጠንካራና ሆደ ሰፊ የሆኑ መሪዎች አያስፈልጉም ማለት አይደለም። በቅንነትና ሕዝብን በማስቀደም መነጋገር ብቻ ሳይሆን ከልብ በመደማመጥ በመግባባት ያስፈልጋል፡፡

ንግግሮች ሁሉ ወደ መግባባት የሚያመሩ መሆን አለባቸው። ንግግራችን የተሠሩ መልካም ሥራዎችንና በመሠራት ላይ ያሉ ጅምሮችን በመቀበል፣ በማድነቅና በማበረታታት፣ እንዲሁም ተገቢውን ክብር በመስጠት የሚጀምሩ መሆን ብቻ ሳይሆን የጋራና የተናጠል እንቅፋቶችንም ለይቶ የሚያስወግዱ ሊሆን ግድ ይላል። ሁሉንም ማጥላላት ሁሉንም ማወደስ ተገቢ አይደለም፡፡ ለችግሮችና ለፈተናዎች ዕውቅና ሰጥቶ በቅደም ተከተል ማረምና ሁሉም ለሰላምና ዴሞክራሲ የራሱን ሚና እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በተለያዩ ወገኖች ወይም ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ንግግሮች በአገራዊ ዓበይት ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩ፣ የሕዝባችንን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ያደረጉ ሆነው መቃኘት አለባቸው። እንደ ማንነታችን ብቻ ሳይሆን በጋራም አኩሪ ባህል ያለን መሆናችንን መዘንጋት የለብንም። ሙት ወቃሽ አያድርገኝ የሚል ግዙፍ ብሂል ያለን ሕዝብ ነን። በሕግ አምላክን የምናውቅ ነን፡፡ መከባበር አለብን። በአሜሪካ መሪዎችና ባለሥልጣናት ይሰዳደባሉ ስለተባለ እኛ ያለ ባህላችን መሰዳደብ አይገባንም። አሜሪካ ከእኛ የምትማረው ብዙ ነገር መኖሩን አንዘንጋ። ስድብ፣ ዘለፋ፣ ዛቻ፣ ወዘተ አያስፈልገንም። በቅንነትና በመከባበር ወደ ለውጥ ዕርምጃ መሄድ እንችላለን፡፡

በየፈርጁ አክራሪነትን እናውግዝ፡፡ አሁን ማንነትና ሃይማኖትን ወይም ጫፍ የረገጡ የፖለቲካ ፍላጎቶችን መነሻ አድርገው የሚቀጣጠሉ ውዝግቦች፣ ለአክራሪነት በር የሚከፍቱ እንዳይሆኑ በጥንቃቄ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ መግባቱ አይቀርም›› ቀደም ባሉት ዓመታት እንዳየነው በሃይማኖት ፅንፈኝነት ዙሪያ ከሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ጀምሮ፣ በዓለም ታሪክ በቀዳሚነቱ እስከሚታወቀው ኸዋሪጅ እስከተባለው አክራሪ ቡድን ድረስ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ፍንጮች መኖራቸውን መርሳት ሞኝነት ነው፣ ከታሪክ እንማር፡፡

በነገራችን ላይ «አክራሪነት» የሚለው ቃል የሚወክለው የሃይማኖቱን/የብሔር ጥቅሞቹን አጥብቆ የያዘን ግለሰብ ወይም ቡድን አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው ያመነበትንና የተቀበለውን የሃይማኖት/የማንነት ትርክትን አጥብቆ ሊያይ ወይም ላያይ ይችላል፡፡ ሐሳቦችን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አንስቶ ማራመድም አክራሪነት አይባልም፡፡ አክራሪነት የሚወክለው ‹‹Extremism›› የሚለውን ሃይማኖታዊ/ማንነታዊ/ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እስከ መጨረሻው ፅንፍ ድረስ በመለጠጥ፣ በልዩነቶች መካከል መቻቻልና መከባበር እንዳይኖር መሥራትን ነው። ይህ ዓይነቱ ፈተና ደግሞ የውስጥም የውጭም አገራዊ ተግዳሮታችን መሆኑን መርሳት አይገባም፣ እንታገለው፡፡

የአንድን ወገን (የሃይማኖትና የፖለቲካ አቋም) የበላይነት ለማስፈንና ሌሎች ሃይማኖቶች/አመለካከቶች በነፃ እንዳይንቀሳቀሱ የሚራመድ አቋም፣ በየትኛውም መንገድ ቢሆን ተቀባይነት ሊያገኝ አይገባም። እንደ እኛ ብዝኃነትና ልዩ ልዩ ፍላጎቶች በሞሉባቸው አገሮች ደግሞ ፈጽሞ የሚታሰብም አይደለም፡፡ አካሄዱ አደገኛ ከመሆኑም በላይ ተቀባይነት የሌለው ነው።

መንግሥትን ለመቃወም የሚደረጉ ሠልፎችና ስብሰባዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የኃይል ዕርምጃዎችና የነውጥ መንገዶች ላይ የእምነትም ሆነ የፖለቲካዊ አስተሳሰብ አክራሪዎች ይሳተፋሉ። የእነዚህ ወገኖች ዓላማ ያለውን ሥርዓት በየትኛውም መንገድ አስወግደው ‹‹ይሻላል›› የሚሉትን  ሌላ አዲስ ሥርዓት መተካት ነው። የአክራሪዎች ዓላማ ያለውን ሥርዓት አስወግደው የሚጠቅማቸው የመሰላቸውን ዕውን ለማድረግ መሥራት ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ይህን ጥቅም ግን ሌላ ኃይለኛ ወይም በለስ የቀናው እንደሚነጥቃቸው ጥርጥር የለውም፡፡ እናም በግጭት አገር ስናምስ ሕዝብ ሲደቅ ከመኖር ውጪ መፍትሔ የለውም፡፡

አሁን እንደሚታየው በዴሞክራሲና በሰላም መንገድ ተስፋ መቁረጥ ሲመጣ፣ ወይም የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ሲታይበት አክራሪነትና አሻጥር እየተባባሰ መሄዱ አይቀርም፡፡ ሌላው ቢቀር በኢኮኖሚ በተለይም በንግድ ሥራዎች ውስጥ ሳይቀር እጁን እየሰደደ፣ ‹‹መንግሥትን ይጥልልኛል›› የሚላቸውን ድርጊቶች እያራገበ የሚኖር ኃይል መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ይህም ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ሆድ እንዲብሰውና ለትግል እንዲነሳ ያነሳሳዋል። መንግሥትም ከእልህ ወጥቶ ነገሮች ማጤን አለበት፡፡

መሠረታዊ የሆኑ ሸቀጦችን መደበቅ፣ ሰው ሠራሽ እጥረት መፍጠር፣ ዋጋን ማናር፣ ኅብረተሰቡን ለማማረር የሚጠቀምባቸው ኢኮኖሚያዊ የሚመስሉ ፖለቲካዊ መገለጫዎቹ የሚስተዋሉት በአንፃራዊነት ሥልጡን በሚባሉት የፖለቲካ አሻጥርና የአክራሪነት መንገዶች ነው። አክራሪነትና የፖለቲካ ነውጠኝነት አሁን እንደሚታየው መንገድ፣ ገበያ፣ ሱቅ ቢዘጋበት ደስታው ነው። ምክንያቱም ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ የገበያና የግንኙነት አውታሮችን የሚዘጋው መንግሥት ነው በማለት፣ ሕግ እንደሌለ በማራገብ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እንደሚማረር ያውቃልና ነው። በአዲሱ ዓመት በተሻለ መነቃቃት ለአስተሳሰብ አክራሪነትና ነውጥ የሚያጋልጡ ችግሮችን ለመቅረፍ መሥራት ይገባል፡፡

ሕዝባችን በጅምላ ከመነዳት ይውጣ፡፡

የሚቀጥለው ጨዋታ ከምንጩ አግኝታችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ለተነሳሁበት ሐሳብ ቁምነገረኛ ጨዋታ ነውና ልድገምላችሁ፡፡ «ጉራጌ ማነው?» ከሚለው ተክሌ ወልደ ጊዮርጊስ በተባሉ ሰው ተዘጋጅቶ በካቲት 1997 ዓ.ም. ከታተመ መጽሐፍ ያገኘሁት ነው፡፡ በሰባት ቤት ጉራጌ የሚወራ የቆየ ታሪክ አለ፡፡ ታሪኩ አቡሽ ስለሚባል ሰው ነው፡፡ አቡሽ በትውልድ እነሞር እንቴዘራ ከሚባል ጎሳ ነው። አቡሽ ይሉኝታ የሌለው፣ ሰውን የማታለል ችሎታው በጣም ከፍተኛ የሆነና በተጠያቂነት ወይም በተከሳሽነት ሲቀርብም ማምለጫ መንገዱ አስቂኝ የሆኑለት ሰው ነበር። እናም እንዲህ ሆነላችሁ።

በሰባት ቤት ጉራጌ ታሪክ ሰውን መሸጥ ያልተለመደና የተነወረ ድርጊት ሆኖ ቆይቷል። በኢትዮጵያ ባሪያ መሸጥና መግዛት በሕግ ባልተከለከለበት ጊዜ እንኳን፣ አንድ የሰባት ቤት ጉራጌ ተወላጅ ሌላውን የሰባት ቤት ጉራጌ ኅብረተሰብ አባል በባርነት መሸጥ ክልክል ነበር። አቡሽ ግን ሰውን በማታለልና በማፈን መሸጥ ዋና ተግባሩ ነበር።

በጉራጌ አገር ሠፈር ለሠፈር በመዘዋወር ሰውን አድኖ መሸጥ የአቡሽ ዋና መተዳደሪያ ሆነ፣ አቡሽ ሰው ሲሸጥ ባዳ ነው ዘመድ ነው ብሎ አይመርጥም፡፡ ከሸጣቸው ሰዎች ውስጥ ብዙዎች የገዛ ዘመዶቹ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ይህን መጥፎ ድርጊቱን እንዲያቆም በተደጋጋሚ ቢመከርም ምክሩን ከምንም ሊቆጥረው አልቻለም። ስለዚህ በመጨረሻ ከአገር እንዲባረር በሕዝቡ ተወሰነበት። አቡሽ ይህን ውሳኔ ሰምቶ ነበርና ውሳኔው ሳይፈጸምበት ለማክሸፍ የሚሆን ቀላል ዘዴ ፈጠረ።

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ትልቅ ሰው ሞቶ ብዙ የእነ ሞር ሕዝብ ለቅሶ በተቀመጠበት ድንገት ብቅ ይልና በሕዝቡ ፊት ቆሞ ኮስተር ባለው ፊቱ ሰላምታ ካቀረበ በኋላ ጮክ ብሎ፣ ‹‹እኖር ተሳ ቧከም ተሳ›› ማለትም፣ ‹‹እነ ሞር ተነስ ተብለሃል ተነስ››› ሲል የተቀመጠው ሁሉ በአንዴ ብድግ አለ። አቡሽ ወዲያውኑ፣

‹‹እኖር ቸራ ቧከም ቸራ›› ማለት «እነ ሞር ቁጭ በል ተብለሃል ቁጭ በል» ሲል የቆመው ሁሉ ቁጭ አለ (ተቀመጠ) አቡሽ በመቀጠል ምን አለ መሰላችሁ፡፡ ‹‹ይኼ ሕዝብ ና ተብለሃልና እኔን ተከትለህ መንገድህን ቀጥል›› ብለው ጊቤ ወንዝ ድረስ የት ነው የምንሄደው ብሎ ሳይጠይቅ እየተከተለኝ ጊቤ ወንዝ ይገባ ነበር» አለና አንድ ጥያቄ አቀረበ።

ጥያቄውም «ተነስ ተብለሃል» ሲሉት ማን አለኝ? ሳይል ተነስቶ የሚቆም «ቁጭ በል ተብለሃል» ሲሉት ማን አለኝ? ብሎ ሳይጠይቅ የሚቀመጥ እንደ ጎተቱት የሚጎተት ሕዝብ እየሸጥኩ ብጠቀምበት ለምን ጥፋተኛ ተደርጌ ከአገር እንድወጣ ይወሰንብኛል? አፋርዱኝ ከአገር አያስወጣኝም» አለ ይባላል።

ሕዝቡም የአቡሽን የማደናገርያ ትዕዛዝ ያለ ምንም ጥያቄ ተቀብሎ በመፈጸሙ በራሱ አፍሮ፣ ‹‹አታድብስ ባኸረሼ፣ ቀሪ ቀሪ ቃር ውስትወ›› ማለትም አታብዛው እንጂ በጥቂት በጥቂቱ ሲቸግርህ ሸጠህ እንዳትራብ ተጠቀም ተብሎ ተወሰነለት። ከአገር የመውጣቱም ፍረድ ተሻረለት ይባላል።

የአቡሽ ነገር የሚያስተምረን በማንኛውም ወገን ኑ ሠልፍ ውጡ፣ መንገድ እንዝጋ፣ ተኩስ እንግጠም እንሂድ፣ ወዘተ. ስንባል ምን? ለማን? የት? መቼ? ለምን?… ብለን መጠየቅ ያለብን መሆኑን ነው፡፡ ማንን ተከትለን ነው የምንሄደው? እሱ ራሱ ማነው ማለት አለብን፡፡ ‹‹ሆ›› በሉ ሲሉን ነገሩ ሳይገባን በጅምላ (Mob) ተከትለን መሄድ የለብንም፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።

በእንቅስቃሴያችን ሁሉ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ቆም እያልን መጠየቅ አለብን፡፡ በተለይ ለፖለቲካ ቡድኖች (አሁን ደግሞ ለዩቲዩብ ነጋዴዎችና አተራማሾች) የተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ በየትኛው መንገድ ብንሄድ ችግራችን ይፈታል፣ ይባባሳል የሚለውን ሳይገመግሙ መንጎድ፣ ሳያላምጡ እንደ መዋጥ ያለ አደጋ ያስከትላልና፡፡

እናም አዲሱን ዓመት በአዲስና በተሻለ መነቃቃት በሰላም ተቀብለን በሰላም ሠርተንበት በሰላም ለመሸኘት ያብቃን ስንል፣ ሁላችንም ለሰላምና ለምክክር ስንዘጋጅ ነውና እንሰናዳ፡፡ በተቻለ መጠን ድህነታችንንና አገራዊ ፈተናዎቻችንን በጋራ፣ የየግል ኑሯችንን በየራሳችን ለማሸነፍ እንንቀሳቀስ፡፡ ከሁሉ ከሁሉ መንግሥትም ወደ ቀልቡ ተመልሶ አገርንና ሕዝብን ያስቀድም፣ ከጦርነትም መፍትሔ አይጠብቅ፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...