Sunday, October 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በኢሕአዴግ ዘመንም ሆነ አሁን ባለው አስተዳደር የአንድ የፖለቲካ ኃይል ድምፅ ብቻ ነው የሚሰማው›› ደስታ ጥላሁን፣ የኢሕአፓ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

የሁልጊዜ ምኞቴ ሰላም በምድራችን፣ ሰላም በአገራችን ተፈጥሮ ማየት ነው ትላለች፡፡ በግልም ቢሆን ራሴን ሰላማዊ ሁኔታ ላይ ሁሌም ማግኘት እፈልጋለሁ ስትል ታክላለች፡፡ ምክንያቱም ሰላማዊ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሰው ምንም ነገር መፍጠር ይችላል ብላ እንደምታምን ታስረዳለች፡፡ ወላጅ አባቷ በጋዜጠኝነት ያቤሎ ከተማ ተመድበው በሚሠሩበት ወቅት በዚያው በያቤሎ እንደተወለደች የምትናገረው ወጣቷ ሴት ፖለቲከኛ ደስታ ጥላሁን፣ በኢሕአፓ ፓርቲ ውስጥ በዋና ጸሐፊነት የፖለቲካ ተሳትፎ ታደርጋለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወደ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊነት መጥታለች፡፡ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በፋርማሲ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀች ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፋርማኮሎጂ ለሁለተኛ ዲግሪ እየተማረች መሆኑን ገልጻለች፡፡ ‹‹በአባቴ ተፅዕኖ ወደ ፖለቲካ ገባሁ›› የምትለው ወጣቷ ፖለቲከኛ ስለፖለቲካ ተሳትፎዋ፣ ስለፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴና ስለአገራዊው የፖለቲካ ሁኔታ ከዮናስ አማረ ጋር ሰፊ ቆይታ አድርጋለች፡፡ ከአንቱታ ይልቅ በአንቺነት እንድትጠራ በፈቀደችው መሠረት በሪፖርተር ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝታ የሰጠችው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ፖለቲካ ለምን ገባሽ?

ደስታ፡- በአባቴ የተነሳ ነው፡፡ አባቴ ጥላሁን እንደሻው ጋዜጠኛ፣ ፖለቲከኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነበር፡፡ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ የእሱን እግር ተከትሎ ወደ ፖለቲካው የመግባት ፍላጎት አደረብኝ፡፡ የእሱን ሥራ ለማስቀጠል ብቻ ሳይሆን፣ የራሴንም አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው በፖለቲካው የተሠለፍኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ለምን ተቀላቀልሽ?

ደስታ፡- የቱ ነው በኢትዮጵያ ምርጡ ፓርቲ ብዬ አይደለም ወደ ፓርቲ ፖለቲካ የገባሁት፡፡ በአንድ የፖለቲካ ማኅበር ጥላ ሥር ገብቶ መታገሉ የተሻለ አማራጭ መንገድ መሆኑን አምንበታለሁ፡፡ ኢሕአፓ ግን ያለው ታሪክ፣ የአባላቱ የፖለቲካ ፅናት፣ ባነበብኳቸው የእነሱ ተሞክሮዎችና የሕይወት ልምድ የተነሳ ለእኔ እንደ አርዓያ ሆኖኛል፡፡ አባቴም ከልጅነት ጀምሮ ስለኢሕአፓ ይነግረኝ ነበርና ወደ ኢሕአፓ እንድሳብ አድርጎኛል እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– በእርግጥ ኢሕአፓ የሚመስጥ ታሪክ አለው ይባላል፡፡ ግን እንዲያው ያን ዓይነት የትግል ፅናት በአሁኑ ትውልድ ውስጥ ሲንፀባረቅ አስተውለሽ ታውቂያለሽ?

ደስታ፡- ትውልዱ ውስጥ ባይታይም ነገር ግን ደግሞ ኢሕአፓ ያኔ ሲያነሳቸው የቆዩ ጥያቄዎች ገና አልተመለሱም፡፡ ለኢትዮጵያ ለውጥ ወይም ሪፎርም በአንዴ ዝም ብለህ ተነስተህ የምታመጣው ሳይሆን፣ ተቋማትን በመፍጠር የምትገነባው ሒደት ነው፡፡ ተቋማትን ከመገንባት አንፃር ደግሞ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ፡፡

 

ሪፖርተር፡- ኢሕአፓን ጨምሮ በወቅቱ የታገሉ እንደ መኢሶን የመሳሰሉ ድርጅቶች ወደ ሥልጣን ቢለወጡና ደርግ ከቦታው ገለል ቢል ኖሮ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ይቀየር ነበር? እነዚያ ኃይሎች ሥልጣኑን ቢይዙ በዴሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብትና በነፃነት አያያዝ ኢትዮጵያ የምንመኘውን ዓይነት አገር ትሆን ነበር?

ደስታ፡- ሙሉ ለሙሉ እንደዚያ ትሆን ነበር ባልልም፣ በተወሰነ ደረጃ ግን አሁን ካለንበት የተሻለ አማራጭ መንገድ ይኖረን ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ በ1997 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ገለል ብሎ ተቃዋሚዎቹ ወደ ሥልጣን ቢመጡ፣ ወይም ያገኙትን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወንበር ተጠቅመው ፓርላማ ገብተው ቢታገሉ ኢትዮጵያ ትለወጥ ነበር እየተባለ ይነገራል፡፡ በዚህ ትስማሚያለሽ?

ደስታ፡- እንደ አገር በተደጋጋሚ የፖለቲካ ውድቀቶች አጋጥመውናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢሕአፓ ሥልጣን ይዞ ቢሆን ኖሮ፣ ወይም 97 ላይ ተቃዋሚዎች ሥልጣኑን ተረክበው ቢሆን ኖሮ፣ የቅርቡ የፖለቲካ ለውጥ ጊዜ የተሻለ አማራጭ መንገድ ተከትለን ቢሆን ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ለውጥ ይኖር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፍፁም ነው አልልም፡፡ ምክንያቱም አመራሮች ላይ ብዙ ጊዜ እንከኖች ይኖራሉ፡፡ ከውጭም ከውስጥም ከለውጡ በተቃራኒ ሊቆሙ የሚችሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኃይሎች ይኖራሉ፡፡ ቀጥታ ሥልጣን በመያዝ ብቻ ለውጡ ይሰምራል ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም አሳታፊነት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና አሁንም ድረስ የተገፉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሥልጣኑም ሆነ በኢኮኖሚው ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ትልቁና መሠረታዊው የሕዝቡ ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ባልተመለሰበት፣ ፍትሐዊነት ባልሰፈነበትና የሕግ የበላይነት ባልተፈጠረበት፣ ዴሞክራሲያዊ አሠራርና እኩልነት ባልተፈጠረበት አገር ውስጥ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ በእነዚያ የለውጥ አጋጣሚዎች ያልናቸው የፖለቲካ ተዋንያን ወደ ሥልጣን መጥተው ቢሆን ኖሮ ደግሞ አሁን፣ ያለንበት ነባራዊ ገጽታ የተለየ ይሆን ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን ልናይ የምንችል የነበረው ለውጥ ፍፁም ይሆን ነበር ብዬ መናገርም አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ሁልጊዜ የፖለቲካ ሽግግር በየተፈጠረበት ምዕራፍ መሰናክልና እንቅፋት የሚያጋጥመው ለምንድነው ትያለሽ?

ደስታ፡- ቅድምም እንዳልኩት ነው፡፡ ለለውጥ የሚታገሉት አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን የታገሉት ወጣቶች ወደ ሥልጣን የሚመጡበት ዕድል የለም፡፡ ወጣቶችን ለፖለቲካ ፍጆታቸው የሚፈልጉ አካላት ወጣቶች እንዲሞቱላቸው፣ እንዲሰውላቸው በማድረግ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በስተመጨረሻ ግን ሥልጣኑን የሚጨብጡት የታገሉት ወጣቶች ሳይሆኑ፣ ወጣቶቹን ለመስዋዕትነት ያቀረቡት ወገኖች ናቸው፡፡ ለለውጡ የታገሉት ወደ ሥልጣን ይመጣሉ ወይ አንዱ ጥያቄ ነው፣ ለለውጡ የታገሉት አካታች በሆነ ሁኔታ በለውጡ ይጠቀማሉ ወይ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ ወትሮውንም የተረሱ ሴቶችና ሕፃናት ጥያቄ ይነሳል፡፡

የደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትን እንደ ማሳያ ማንሳት ይቻላል፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የነበረውን ሁኔታም ማየት ይቻላል፡፡ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር የተደረጉ ጦርነቶች እንዲሁም በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ጦርነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ግጭቶች የሞቱትና ዋና ሰለባ የነበሩት ወጣቶች፣ አረጋዊያን፣ ሴቶችና ሕፃናት ነበሩ፡፡ ነገር ግን በስተመጨረሻ የሰላም ድርድሮቹ ሲደረጉ የተደራደሩት አካላት ግን ሌሎች ናቸው፡፡ የተደራደሩት ነገር እንኳ ስለምን እንደሆነ ለእኔ ብዙም ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ ምናልባት እናንተ ካወቃችሁ ትነግሩናላችሁ እንጂ የድርድሩን ጭብጦች እንኳን አናውቅም፡፡ ከድርድሩ በኋላ ተስማማን የሚሏቸውን ጉዳዮችም ማስፈጸም ላይም ቢሆን ችግሮች አሉ፡፡ በአጠቃላይ እኔ በግሌ ይህን ዓይነቱ ድግግሞሽና አዙሪት ካልተለወጠ በስተቀር ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ቁጭት ያሳድርብሻል?

ደስታ፡- አዎ እኔ ብዙ ነገሮች ይቆጩኛል፡፡ እንደ አንድ አገሩን እንደሚወድ ዜጋ፣ እንደ አንድ ፖለቲከኛ፣ እንደ አንድ ወጣት በአገር ደረጃ ብዙ ከስረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ከዚህ ኪሳራ ለመውጣት በተለይ መሪዎቻችን በቅን ልቦና፣ በተረጋጋ መንፈስና በሆደ ሰፊነት ሕዝቡን ቀርበው ማነጋገር መቻል አለባቸው፡፡ የሕዝቡን ተጨባጭ ጥያቄ ወረድ ብለው ማዳመጥ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሌሎች ፖለቲከኞችስ ምንድነው የሚሉት ብለው ማዳመጥ አለባቸው፡፡ በእልኸኝነት አገር አይመራም፡፡ በሌላ ጎራ የተሠለፉት ደግሞ በመሰዳደብና በመወቃቀስ የሚፈታ ነገር እንደሌለ መገንዘብ አለባቸው፡፡ እኔ መፍትሔ ብዬ የምናገረው ነገር ቁጭ ብለን እንነጋገር የሚል ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ ሁሉም ችግሩን አምጥቶ ተደማምጠን ለችግሮቻችን የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ እንጂ ሌላው አያዋጣም ነው የምለው፡፡ የድሮ ታሪክና ትርክት እያወራን፣ እኔ ባልተፈጠርኩበት ዘመን ስለሆነ ነገር ጊዜዬን እየፈጀሁ ወደኋላ መሄድ አልፈልግም፡፡ እኔ እንደ አንድ ራዕይ እንዳለው ወጣት ሴት ፖለቲከኛ እንዲሁም እንደ አንድ ለአገሬ ጥሩ እንደሚመኝ ሰው መፍትሔ ብዬ የማምነው ቁጭ ብሎ መነጋገርን ብቻ ነው፡፡

በጣም ብዙ ችግሮች አሉብን፡፡ ሥራው አንድና ሁለት ብለን በቀላሉ ቆጥረን የምንሠራውም አይደለም፡፡ ሒደቱ ጊዜ ይጠይቃል፣ ቁጭ ብለን መነጋገር ይጠይቃል፡፡ ችግሮቻችን በጣም ሥር የሰደዱ ናቸው፣ ተደራራቢ ናቸው፣ አንዱን ፈተን ሳንጨርስ ነው ሌላው የመጣብን፡፡ ስለዚህ ጊዜ ያስፈልጋል፣ ሀብት ይጠይቃል፣ የሰው ሀብት ይፈልጋል፣ ሎጂስቲክስ ይፈልጋልና ይህን የሚያሟሉ አካላትን አሰባስቦ በቁርጠኝነት ተቀምጦ ተነጋግሮ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ የሆነ ወገን መግለጫ ስላወጣ ወይም ሌላው የሆነ ነገር ስላለ የሚፈታ ነገር የለም፡፡ ቁጭ ማለትና መረጋጋት ይፈልጋል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ባህላችን አለመደማመጥ የሰፈነበት ነው፡፡ ጥላቻና መቃቃር የሞላበት ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ተቃርኖ መቆም የበዛበት ነው፡፡ ስለዚህ ችግራችንን ለመፍታት ይህን ቀይረን መደማመጥ ማስፈን  አለብን፡፡ በተለይ ባለፉት 31 ዓመታት የተዘመረው የብሔር ፖለቲካ የፈጠረው የራሱ ችግር አለ፡፡ እኔ ለምሳሌ በብሔሬ እኮራለሁ፡፡ ሰዎች የብሔር ማንነታቸው ዕውቅና ሊያገኝ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን ደግሞ ከብሔር የሚበልጥብኝ ጉዳይም አለ፣ አገር አለኝ፡፡ አገር ሲኖረኝ ነው ስለብሔሬም ሆነ ስለግል ማንነቴ መናገር የምችለው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ አገርን ካስቀጠልን በኋላ፣ ሕዝብ ከገነባን በኋላ፣ የብሔር ማንነቴ እንዲታወቅ መደረግ አለበት፡፡ እንደ ብሔሬ እንደ አካባቢዬ ደግሞ ተጠቃሚ መሆን አለብኝ፡፡ ጉዳዩ ስለአገር ስለሆነ ቁጭ ብለን መነጋገር ወሳኝ መፍትሔ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ጠመንጃ እንደ መፍትሔ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን የትም አገር ቢኬድ በጠመንጃ መፍትሔ መጥቶ አያውቅም፡፡ በእኛ አገር ተደጋጋሚ ልምድም ካየነው እሱ ውጤቱ ኪሳራ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ መሣሪያ መፍትሔ ይሆነናል ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡– ትግበራው ቢዘገይም አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተዋቅሮ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህ አማራጭስ መፍትሔ ይሆናል?

ደስታ፡- አንዱ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቸኛው የኢትዮጵያን ዕጣ ፋንታ የሚወስን መፍትሔ ነው ብዬ ግን አላስብም፡፡ ብንጠቀምበትና ሁላችንም ኮሚሽኑን ብናግዘው አንዱ አገራዊ ችግሮቻችንን መፍቻ አማራጭ መፍትሔ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች አማራጮችም ሲቀርቡ ይታያል፡፡ ራሱን የቻለ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ይዋቀር የሚሉም አሉ፡፡

ደስታ፡- እኔ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ይመሥረት ከሚሉት ወገኖች አይደለሁም፡፡ በምርጫ ሥልጣን ላይ ያስቀመጥነው መንግሥት አለ፡፡ መንግሥት ተገቢውን ሥራ እንዲሠራ ማድረግ እንችላለን፡፡ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑም ሥራውን እንዲሠራ ማድረግ እንችላለን፡፡ መንግሥት በአገራዊ ምክክሩ ሒደት ደጋፊና ምቹ ሁኔታን ፈጣሪ ነው መሆን የሚችለው፡፡ ብዙ የአገር ሀብት ያለው መንግሥት ዘንድ እንጂ ተቃዋሚዎች ጋ አይደለም፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምክክሩ ተሳታፊ መሆን ነው ያለብን፡፡ መንግሥት ጣልቃ ሳይገባና ሒደቱንም ወደ ራሱ ሳይጠልፍ ጤናማ አገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታን በመፍጠርና በሀብት በመደገፍ አንዱ ባለድርሻ መሆን ይችላል ብለን ነው የምናምነው፡፡ አገራዊ ምክክር ሲባል ግን ግልጽነት ሊኖር ይገባል፡፡ ከእኛም ከተቃዋሚዎችም ሆነ ከማኅበረሰቡ የሚነሱ የግልጽነት ጥያቄዎች አሉ፡፡ ሌላው ተዓማኒነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊትም ቢሆን ብዙ ውይይቶች ተደርገውና ብዙ ኮሚሽኖች ተቋቁመው ምንም ሳይሠሩ መክነው ስለቀሩ የተዓማኒነት ጥያቄ ይቀርባል፡፡ ሌላኛው የአካታችነት ጥያቄ ነው፡፡ መላው ኢትዮጵያዊና በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ መሳተፍ መቻል አለበት፡፡ የመረጃ መረብም ሆነ የመረጃ ምንጭ በበቂ ደረጃ ያልተዳረሰበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ስለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ሆነ ስለሥራው በቂ መረጃ ያልደረሰው የኅብረተሰብ ክፍል ይኖራል ብለን እንገምታለን፡፡ በተዋረድ ታችኛው ከመረጃም ሆነ ከሚዲያ ተገልሎ የሚኖረው ኅብረተሰብ ዘንድ ጭምር ግንዛቤው መድረስ አለበት፡፡

ወደ ኅብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ዘንድ ለመድረስም ቀላልና ቀልጣፋ የመረጃ መፍሰሻ መንገድ ያስፈልጋል፡፡ ኮሚሽኑ ኢንተርኔት በዋናነት የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይጠቀማል፡፡ ነገር ግን እነዚህ መረጃ ማሠራጫ መንገዶች ሰፊው ማኅበረሰብ ጋ ገና አልደረሱም፡፡ ከኅብረተሰቡ የሚመጡ ጥያቄዎችም ሆኑ መልዕክቶችና ሐሳቦች በቅጡ ለኮሚሽኑ እንዲደርሱ ብዙ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ብዙ አማራጮች ሊፈጠሩ ይገባል፡፡

ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ ደግሞ የውክልና ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ወጣት ሴት እንደ መሆኔ ወጣቶችም ሴቶችም በሚገባ መወከል አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አርሶ አደር፣ ነጋዴ፣ የተማረም ያልተማረም የሚባል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በዚህ ውስጥ መሳተፍ አለበት፡፡ አንዳንዴ ስለጉዳዩ ድርድር የሚል የተዛባ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ ድርድር ሳይሆን ግን በአገር ጉዳይ ላይ ምክክር ማድረግ ነው የአገራዊ ምክክሩ ግብ፡፡ ስለዚህ እከሌ መጥቶ ይደራደር ወይም እከሌ አይደራደር የሚባል ነገር የለም፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ያገባኛል የሚል ብቻ ሳይሆን አያገባኝም ብሎ የተቀመጠውም ይምጣና የምክክሩ ጠረጴዛ ላይ ይሳተፍ፡፡

እዚህ ላይ በምክክሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ አካላት መሳተፍ አለባቸው፡፡ ኅብረተሰቡ በማን ነው የሚወከለው የሚለው ጉዳይ በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ የሚወክለንን አካል ስንመርጥ የእኛን ጥያቄ በትክክለኛና በተገቢው ሁኔታ የሚያቀርብ መሆን አለበት፡፡ ሌላኛው በምክክሩ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ጉዳይም ጥንቃቄ ሊለየው አይገባም፡፡ የኅብረተሰቡን ፍላጎት የሚያቅፉ መሆን አለባቸው፡፡ አንዳንዱ አካባቢ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዱ አካባቢ መንገድ፣ ሌላው የፖለቲካ ጉዳይ፣ አንዱ ክልል እፈልጋለሁ ሊል ይችላል፣ ሌላኛው ደግሞ ባለሁበት ቦታ በሰላም ለመኖር የምችልበት ሁኔታ ይፈጠርልኝ የሚል ሊሆን ይችላል ጥያቄው፡፡ እነዚህን ሁሉ ሁኔታዎች ሲያሟላ ነው ብሔራዊ ምክክሩ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው፡፡

ሪፖርተር፡- ሒደቱ ብዙ ጊዜ  ፈጅቷል ይባላል፡፡

ደስታ፡- ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሦስት ዓመታት ነው የተሰጠው፡፡ በዚህ ጊዜ መላው የአገሪቱን ክፍል የሚወክሉ ተሳታፊዎችን አወያይቶ የኅብረተሰቡን ጥያቄ ይዞ መምጣት እንዳለበት ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን አንድ ዓመት ከስድስት ወሩን በዝግጅትና በቅድመ ዝግጅት ነው ያገባደደው፡፡ አሁን የቀረው አጭር ጊዜ ነው፡፡ ይህንኑ ጊዜ በአግባቡ ተጠቅሞ ኮሚሽኑ ውጤታማ የሆነ ውይይት ማድረግ አለበት፡፡ እዚህ ሒደት ውስጥ የገቡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮን ስናይ የተሳካ ብሔራዊ ምክክር ማድረግ ፈታኝ ነው፡፡ የመኖች የተሳካ የሚባል የምክክር ሒደት ውስጥ ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ መጨረሻ ላይ ግን ወደ ጦርነት ነው የተሻገሩት፡፡ እስካሁንም ከጦርነት አልወጡም፡፡ ሱዳንን ማየት እንችላለን፣ ሊቢያንም መመልከት እንችላለን፡፡ በተለያዩ አገሮች ለምሳሌ ስኬታማ ሒደት የነበራቸው እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉትን ካየን የተሳካ ቢሆንም፣ በመጨረሻ የተጠለፈበትን ሁኔታ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ የሌሎችን ከማጥናት በተጨማሪ በራሳችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ምክክር ማካሄድ አለብን ብዬ ነው የማስበው፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሲዋቀር ከአዋጁ ጀምሮ የተቋሙን አደረጃጀት በተመለከተ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ሲቀርብ ነበር፡፡ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ የምክክር አወያዮችና አመቻቾች የሚመረጡበት መሥፈርት ሲያስቀምጥም እንዲሁ ቅሬታ ተሰምቷል፡፡ አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከዚህ ጉዳይ በጊዜ ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ ሐሳባችን አልተደመጠም፣ ሒደቱም በመንግሥት ተጠልፏል በሚል አንዳንድ ወገኖች ተቃውመውታል፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ስኬታማ ምክክር ሊደረግ ይችላል?

ደስታ፡- ቅድምም እንዳነሳሁት አሳታፊነት ወሳኝ ነው፡፡ ከአሳታፊነት አንፃር ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ካየነው ከ11 ኮሚሽነሮች ሦስቱ ብቻ ናቸው ሴቶች፡፡ ሦስት ብቻ መሆናቸው ሳይሆን የዕድሜ ስብጥር ጉዳይም ይታያል፡፡ እኔ በዚህ ኮሚሽን ተወክያለሁ ለማለት ጥያቄ አለኝ፡፡ ከእኔ በታች ደግሞ ሌሎች በጣም ወጣት ሴቶችም አሉ፡፡ ሴቶች እንደ አጠቃላይ በብዙ ነገሮች ቢረሱም ታዳጊ ሴቶች ደግሞ የበለጠ ይረሳሉ ወይም የመደመጥ ዕድል አያገኙም፡፡ ይህን የውክልና ጥያቄ ጨምሮ ብዙ ውስንነቶች ቢኖሩበትም እንኳን ብሔራዊ ምክክሩ ወደኋላ ተመልሶ ድጋሚ ይመሥረት የሚል ጥያቄ ላይ አንገኝም፡፡ አሁን እሱ ታልፏል፡፡ ያም ቢሆን ግን ጥያቄ ይዘው የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ የራሳቸው ኮከስ ፈጥረው የወጡ አሉ፡፡ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ግልጽነት ስለሚጎድለው በሒደቱ አንሳተፍም፣ ጥያቄያችን ይመለስ ብለው ጥያቄዎቻቸውን አስገብተዋል፡፡ ሆኖም ኮሚሽኑ ቅርብ ጊዜ እነዚህን ወገኖች እያነጋገራቸው መሆኑን አውቃለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምንም ፋይዳ የሌለውና ጥርስ የሌለው አንበሳ እየተባለም ይተቻል፡፡ የምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ከሆንሽ በኋላ ቀረብ ብለሽ ያየሽው ሁኔታ ከሚባለው የተለየ ነው?

ደስታ፡- በፍፁም እንደዚያ ማለት አይቻልም፡፡ ምክር ቤቱ ብዙ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ከተለያዩ አገሮች ተወካዮች ጋር ይነጋገራል፣ ይመካከራል፣ እንዲሁም ይደራደራል፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ሥልጠና ያዘጋጃል፡፡ ግንዛቤ እንዲኖር ብዙ ሥራዎችን ይሠራልና ምንም ሥራ አልሠራም ተብሎ መናገር አይቻልም፡፡ እኔ በሴቶች ኔትወርክ ጭምር በዚህ ምክር ቤት ውስጥ እንደ መሳተፌ፣ ብዙ ዕቅድ አውጥተን የሠራናቸው ሥራዎች መኖራቸውን በተጨባጭ አውቃለሁ፡፡ ግን ደግሞ መሥራት የሚገባውን ያህል ሠርቷል ብዬ ደግሞ አላስብም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማለት ትልቅ ሥራ መሥራት የሚችል አካል ነው፡፡ የፖለቲካ ሚዛን እንዲጠበቅ ማድረግ ይችላል፡፡ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችን መፍታት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በአቅም ማነስም ሆነ በሕግ ማዕቀፍ መጥበብ የተነሳ ብዙ እንቅስቃሴዎቹ የተገደቡ ሆነዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያም ቢሆን ግን ምክር ቤቱ ብዙ መሥራት የሚችልበት አቅም አለው፡፡ አሁን እኔ በዋና ጸሐፊነት ወደ ምክር ቤቱ መጥቻለሁ፡፡ በተቻለ መጠን ምክር ቤቱን የተሻለ እንዲሠራ ለማገዝ ጥረት አደርጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በርካታ ሴቶች ወደ ፖለቲካው መጥተው ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ አሳይተው የት ይደርሳሉ ተብሎ ሲጠበቅ መልሰው ደግሞ ከፖለቲካው ይጠፋሉ፡፡ በኢትዮጵያ 50 በመቶ የሕዝብ ቁጥር በሴቶች የተሸፈነ ነው እተባለ፣ ነገር ግን እጅግ ውስን የሆነ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መኖሩ ምን ያሳይሻል?

ደስታ፡- ብዙ ነገር እታዘባለሁ፡፡ ሴቶች ወደ ፖለቲካ መምጣት ያለባቸው ማንም መብት ወይም ችሮታ ስለሰጠን መሆን የለበትም፡፡ የሴቶች በፖለቲካ መሳተፍ ማንም የሚሰጥ የሚነፍጋቸው ሳይሆን፣ መሠረታዊ መብት ወይም የሰብዓዊ መብት ሆኖ መታየት ያለበት ጉዳይ ጭምር ነው፡፡ ሴቶች መብታችን እንደሆነ አውቀን ወደ ፖለቲካው መምጣት አለብን ብዬ ነው የማምነው፡፡ በዚህ አጭር ዓመታት የፖለቲካ ተሳትፎዬ ሁለት ዓይነት ሴቶችን ታዝቤያለሁ፡፡ ደፍረውና ቆርጠው ብዙ ችግሮችን ተቋቁመው ባላቸው አቅም ተሳትፎ ለማድረግ ቆርጠው ወደ ፖለቲካ የገቡ ጥቂት ሴቶች አሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ መሳተፍ እየፈለጉና ዕውቀቱም ሆነ ብቃቱ እያላቸው ወደ ፖለቲካ ከገባሁ፣ በራሴም ሆነ በቤተሰቤ ላይ ሌላ ጣጣ ይመጣል ብለው ራሳቸውን የገደቡ ሴቶች አሉ፡፡ መደረግ ያለበት እነዚህ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ደፍረው ወደ ፖለቲካው አደባባይ የመጡ ሴቶች ማብቃት፣ ማገዝና ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታታት አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ ያልመጡትም ሴቶች ግን መምጣት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ መጥተው መከራከር፣ መሟገትና መታገል አለባቸው፡፡ ቁጭ በማለታቸው የሚፈታ ችግር እንደማይኖር መረዳት አለባቸው፡፡

ሴቶች ወደ ፖለቲካው በሰፊው መጥተው የሚችሉትን ያህል ማድረግ አለባቸው፡፡ ራሳቸውን ከፖለቲካው አርቀው ቁጭ ቢሉም ከችግሩ አይድኑም፡፡ የፖለቲካው እሳት አይቆምም፡፡ ሄዶ ሄዶ ረሳቸውን አርቀው ከተቀመጡበት ገብቶ መፋጀቱ አይቀርም፡፡ ፖለቲካው አያገባኝም ብለው ቤታቸው ቢቀመጡም ፖለቲካው አይለቃቸውምና ገብተው ለራሳቸው እንዲታገሉ ነው የምመክረው፡፡ ይህን አስቸጋሪ የሆነ የፖለቲካ ምኅዳራችንን የተረዱ ሴቶች ብዙ አሉ፡፡ እንዳይሳተፉ ግን ብዙ እንቅፋት አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹም ለሴቶች አሳታፊነት የተመቹ መሆን አለባቸው፡፡ ሴቶች እንዲመጡ መቀስቀስና ራሳቸውን በደንብ ማስተዋወቅ አለባቸው፡፡ ከመጡ በኋላም ለእነሱ በሚያመች መንገድ የተሳትፎ ዕድልና መድረክ መፍጠር አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን የሴቶችን ተሳትፎ የጎተቱ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ያም ቢሆን እኔ ተቋቁሞ ማለፍ ይቻላል ብዬ ስለማስብ ችግሮቹን መዘርዘር አልፈልግም፡፡ እነዚህን ችግሮችም ቢሆን ማስወገድ የሚቻለው በውጣ ውረድ አልፈን መጥተን ችግሮቹን የሚቀርፉ ፖሊሲዎች እንዲቀረፁ በማድረግ፣ ያሉትን ሕጎችም ሆኑ ፖሊሲዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ጫና በማሳደር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መቀነስ ተጠያቂነቱ ብዙ ጊዜ ወደ ወንዶች ቢገፋም ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ባህላችን፣ ሃይማኖታችን፣ የፖለቲካ ሥሪታችን፣ ወይስ አጠቃላይ ሥርዓታዊ የሆነ ነው ችግሩ የሚሉ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ይነሳሉ፡፡

ደስታ፡- ችግሩ ሥርዓታዊ (ሲስተሚክ) የሆነ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በየዕለቱ ከቤትህ ስትወጣ ጀምሮ የሚገጥምህ ነገር ጉንተላው፣ ለከፋው፣ ስድቡ ሁሉ ሴቶችን የሚያስር ነው፡፡ በትራንስፖርት፣ በሥራ ቦታ፣ በገበያ በየቀኑ እንቅስቃሴዎች ሴቶች ፆታ ተኮር ለሆኑ ችግሮች ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ ያንን ሁሉ ተቋቁማ ነው ሴቷ ወደ ፖለቲካው መግባት ያለባት፡፡ ሥርዓታዊ የሆነውን ነገር ሁል ጊዜ ሴቷ ብቻ ተቋቁማ መኖር አለባት ማለት ግን ከባድ ነው፡፡ ለሴቶች የተመቸ የአኗኗር ሁኔታ በዚህ አገር ውስጥ ሊፈጠር ይገባል፡፡ በሁሉም መስክ ችግር አለ፡፡ በሁሉም መዋቅር ችግር አለ፡፡ ስለዚህ ከቤተሰብ ጀምሮ የእምነት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሥራ ቦታዎች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በትራንስፖርቱ፣ በገበያው፣ በአጠቃላይ በሁሉም መስክ ሴቶችን እኩል አካታች ያደረገ አሠራር መኖር አለበት፡፡ ሴቶች በተቻለ መጠን ራሳቸውን በማብቃትና በማጠንከር ላይ ብዙ መሥራት አለባቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የወንዶች ተባባሪነት አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተፎካካሪ ፓርቲዎች በየጊዜው መግለጫዎች ይሰጣሉ፡፡ በእነዚህ መግለጫዎች ደግሞ በአገሪቱ ላሉ ቀውሶች መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለበት በተደጋጋሚ ያስታውቃሉ ለአገራዊ ቀውሶች ተፎካካሪ ፓርቲዎችስ የሚወስዱት ድርሻ የለም?

ደስታ፡- ለአገራችን ችግር ተጠያቂው ሁላችንም ነን፡፡ ሁላችንም አስተዋጽኦ አለን ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከራሴ ጀምሮ ብንችል ሁላችንም ለሰላም ምክንያት መሆን አለብን ብዬ ነው የማምነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር መፍትሔ ነው የምንለውን ለመጠቆም ስንሯሯጥ እንታያለን፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የአገራችን ተጨባጭ ችግር ምንጩ ምንድነው ብሎ በመሠረታዊነት አተኩሮ መሥራት ላይ ብዙ ይቀረናል፡፡ እንደ አንድ ግለሰብ፣ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ፓርቲ አባል የችግሩ ምንጭ ምን እንደሆነ ማወቅ መቅደም አለበት እላለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ የተለያዩ ዝርዝር ችግሮች ቢነሱም በእኔ ግምት ግን መሠረታዊ የኢትዮጵያ ችግር ከድህነት ወይም ከኢኮኖሚ ችግር ነው የሚነሳው፡፡ የብዙኃኑ ኅብረተሰብ ጥያቄ የኢኮኖሚ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ነው፡፡ ሌላው ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጩ ችግሮችም አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱን ስናይ አገሪቱ ዴሞክራሲያዊ የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት እንደምትከተል ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር በኢሕአዴግ ዘመንም ሆነ አሁን ባለው አስተዳደር የአንድ የፖለቲካ ኃይል ድምፅ ብቻ ነው የሚሰማው፡፡

ፓርላማው ላይ የሚሰማው ድምፅ አንድ ዓይነት ነው፡፡ በኢሕአዴግም ሆነ በብልፅግና ዘመን የፖለቲካ ሥልጣኑን ለጨበጠው ኃይል የሚሠራ ፓርላማ ነው ያለው፡፡ የሕዝብ እንደራሴዎች የሚለው ቃል ሕዝብ ራሱ ማለት እንደሆነ በግሌ ቢገባኝም፣ ነገር ግን ፓርላማው ከሕዝብ ይልቅ ለመንግሥት የወገነ ነው፡፡ ሚዲያውም ቢሆን ለመንግሥት የሚሠራና የመንግሥትን ድምፅ የሚያስተጋባ የበዛበት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የአገራችን መሠረታዊ ችግሮች ይፈታሉ ብዬ አልገምትም፡፡ ስለዚህ ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ብንሆን ሁሉንም ነገር ወደ መንግሥት ብቻ መግፋት የለብንም፡፡ እኛም ለችግሮች ኃላፊነት መውሰድ አለብን፡፡ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ስም እኮ የሚሠራ ብዙ ነገር አለ፡፡ እኛም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ መንግሥትም እንደ መንግሥት ኃላፊነቶቻችንን መለየት መቻል አለብን፡፡ ነገር ግን እኛ በሰላማዊ መንገድ የምንንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት እንደ መሆናችን ማድረግ የምንችለው መግለጫ በማውጣት መታገል ሊሆን ይችላል፡፡ ደጋግመን መጮህ ነው የምንችለው፡፡ ደጋግመን የሕዝብ ድምፅ መሆን ነው ያለብን፡፡

መንግሥት ሆይ ይህንን ኃላፊነትህን በአግባቡ አልተወጣህምና እባክህ ኃላፊነትን የመወጣት ግዴታ አለብህ ብለን ማሳሰብና መጠየቅ ነው ያለብን፡፡ ይህንን ከበቂ በላይ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ አሁንም ቢሆን ችግሮቹ እስካልተፈቱ ድረስ ይህን ማድረጋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ መንግሥትም ኃላፊነቱን አውቆ በትክክል መሥራት አለበት፡፡ አንዳንዴ የመንግሥት ኃላፊነት የተረሳም ይመስለኛል፡፡ መሠረታዊ የሆኑ የሰዎች መብቶች እየተከበሩ አይደለም፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ ጥያቄ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ መጥተህ፣ ሄደህ፣ እዚህ ቦታ ተወልደህ፣ ሠርተህ ያፈራኸው ሀብት በደቂቃዎች ውስጥ ሲወድምና ማንም ለጥፋቱ ተጠያቂ ሳይሆን ሲቀር እያየን ነው፡፡ የሰዎች ሕይወት ያላግባብ እየጠፋ ነገር ግን ተጠያቂ የሌለበት ሁኔታ እያየን ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከሁሉ በላይ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የፖለቲካ ድባብ የፓርቲ ፖለቲካን ተፈላጊነት እያሳጣው ነው ይባላል፡፡ እዚህም እዚያም ሕዝቡ በራሱ መንገድ ጥያቄ ሲያነሳና በደቦ ሲንቀሳቀስ እንጂ፣ በአንድ የፖለቲካ ማኅበር ሥር ተደራጅቶ የመታገል ጉዳይ እየቀረ ሄዷል ይባላል፡፡ ይህንም ደግሞ በአማራም ሆነ በሌሎች ክልሎች እየታየ ሲሆን፣ የፖለቲካ ድርጅቶች የማይመሯቸው ያላስተባበሯቸው እንቅስቃሴዎች በአገሪቱ በዝተዋልም ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እንዲባባሱ ምክንያት መሆኑ ይጠቀሳል?

ደስታ፡- በዚህ እስማማለሁ፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ጠፍተው ሳይሆን ብዙ አሉ፡፡ ፓርቲዎቹ ሐሳብ ሳይኖራቸው ቀርቶም አይደለም፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚካሄደው ትግል ብዙ ጊዜ ተሞከረ፡፡ ነገር ግን መጨረሻው ብዙ ጊዜ የአባላት ወይም የአመራሮች መታሰር ነው የታየው፡፡ ይህ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በሕዝቡ ውስጥ እየተፈጠረ ሄዶ መጨረሻው መታሰር ከሆነማ፣ ከፓርቲዎች ይልቅ በራሴ መንገድ ልሞክረው ወደ የሚል ስሜት ውስጥ ገብቶ ከሆነ አላውቅም፡፡ ግን ሁኔታው ይህ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል በድንገት የፈነዳ ችግር አይደለም የተፈጠረው፡፡ እዚያ አካባቢ ብዙ ጥያቄዎች ሲነሱ ነበር፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጥያቄዎች ነበሩ፣ ጦርነቱ ካበቃ በኋላም ጥያቄዎች ነበሩ፣ አሁንም ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ቅድም እንዳልኩት መንግሥት ለእነዚህ መሰል ጥያቄዎች ቀድሞ ጆሮ መስጠት አለበት፡፡ በሆደ ሰፊነት እህ ብሎ ሕዝቡን ማድመጥ አለበት፡፡ በእኛ አገር ፖለቲካ የአንዳንድ ነገሮች አተረጓጎም ይጣመማል፡፡ ለምሳሌ ችግሮችን በሆደ ሰፊነት ማየት ሲባል ችግሩ እየተፈጠረ እያዩ ዝም ብሎ እጅን አጣጥፎ ተቀምጦ መታዘብ ማለት አይደለም፡፡ ተግባራዊ ዕርምጃና ምላሽ መስጠት በሚያስፈልግ ወቅት መንግሥት በቶሎ ፈጣን መልስ መስጠት አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ችግሮች የት ድረስ እንደሚሄዱ እያየን ነው፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ችግሮች ሲፈጠሩ የሚያራግቡበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ እያየን ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ሕዝብ ጥያቄ ሲያነሳ ጆሮ መስጠት የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ እንዳያደርግ ከልክለህ፣ እንዳይወጣ አድርገህ፣ በርህን ዘግተህ ሕዝብን ዝም ማሰኘት አትችልም፡፡ ይህ የሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄ ደግሞ ቁጣና ተቃውሞ የተቀላቀለበት ነው፡፡  ‹‹የሚበላውን ያጣ ሕዝብ መሪዎቹን በመጨረሻ ይበላል›› የሚል አንድ አባባል ከዚህ ቀደም ሰምቻለሁ፡፡ ይህ እውነትነት አለው፡፡ ዝም ብሎና ብዙ ታግሶ ቆይቶ በቁጣ የተነሳን ሕዝብ በጦርም ሆነ በድሮን አትመልሰውም፡፡ ስለዚህ ሕዝብ ጥያቄ ሲያነሳ ቀረብ ብሎ ችግሩን አድምጦ መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ በአንድ በኩል በሕዝብና በመሪዎች መካከል ሰፊ ርቀት እየተፈጠረ መምጣቱን ያሳየኛል፡፡ በአመራሩና በሕዝቡ መካከል ሰፊ ርቀት ተፈጥሯል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በትክክል ካለመተግበሩ የተነሳ ሥልጣን ባልተማከለ ሁኔታ ከመከፋፈል ይልቅ፣ ወደ አንድ ማዕከልና ወደ አንድ ነጥብ እየተሰበሰበና እየተከማቸ ይገኛል፡፡ ላይ ባሉና ታች ባሉ አመራሮች መካከል ግንኙነቱ የላላ ይመስለኛል፡፡ የክልሎች አወቃቀር፣ እንዲሁም የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ግንኙነት ከየት ወዴት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ አንዳንዴ ክልሎች ሌላ ጊዜ ደግሞ ፌዴራሉ በበላይነት ሲቆጣጠሩት ይታያል፡፡ ሁኔታውን በትክክል የተረዱትም አይመስለኝም፡፡    

ሪፖርተር፡- በዚህ ውስብስብ ችግር የተነሳ አገሪቱ ድንገት እንዳትፈራርስ አያሠጋሽም?

ደስታ፡- እንደዚያ አላስብም፣ ተስፋ አለን፡፡ ነገሮች ይስተካከላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚያም ነው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብቼ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት እየሠራሁ ያለሁት፡፡ ሆኖም የእኔ በጎ ምኞት ብቻ ወይም የእኔ መትጋት ብቻ ያን ዕውን ያደርጋል ብዬም አልገምትም፡፡ መንግሥት በዚህ ላይ አጠንክሮ መሥራት አለበት፡፡ አሁን የአገረ መንግሥት መፍረስ ምልክቶች በትክክል እየታዩብን ነው፡፡ ብዙ ቦታዎችን መንግሥት ማስተዳደር ያልቻለበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት የምንገባበት አጋጣሚ ያለ ይመስላል፡፡ ነገር ግን አሁንም፣ ዕድል አለን ቢሆን ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ያን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ አለ? ከመንግሥት ባህሪ ወይም ከሥርዓቱ ቁርጠኝነትና ቀናነት አንፃር ምን ይታይሻል?

ደስታ፡- እንግዲህ እኛ ለመንግሥት መልሰን መላልሰን እየተናገርን ነው፡፡ ቁርጠኝነት ይጠይቃል የምንለው ወደን አይደለም፡፡ መንግሥት ለሰላማዊ ንግግሮችና ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ሁኔታዎችን አመቻች መሆን አለበት፡፡ ለመነጋገር መቼም አይረፍድምና አሁንም ሰዓቱ አልረፈደም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከጦርነት በኋላ ከተገዳደሉት ሰው ጋር ተቀምጦ መነጋገር እንዳለ በዚህች ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ዓይተናል፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የኤርትራን ሁኔታ ዓይተናል፣ የሱዳንን ሁኔታም ዓይተናል፡፡ ለመነጋገር መቼም አይረፍድም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአፓ ዋናው የሚታገልለት ጉዳይ ምንድነው?

ደስታ፡- ኢሕአፓ ሲመሠረት እንደ ፋሽን የነበረው ርዕዮተ ዓለም ሶሻሊዝም ስለነበር፣ ልክ በጊዜው እንደ ተመሠረቱ ፓርቲዎች ሁሉ ሶሻሊስታዊ ፓርቲ ሆኖ ነው የተመሠረተው፡፡ ከዚያ በኋላ በተለይ ከተመሠረቱ ከአሥር ዓመታት በኋላ ማለትም የዛሬ 40 ዓመት አካባቢ ወደ ሶሻል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለማቸውን በዚያው በተሰደዱበት ውጭ አገር ቀይረዋል፡፡ የፖለቲካ ለውጥ በአገራችን በመጣ ወቅት ልክ እንደ ኦነግና ግንቦት ሰባት ሁሉ ውጪ ላሉ ድርጅቶች ጥሪ ሲደረግ ነው ኢሕአፓም ወደ አገር የገባው፡፡ ይዞት የመጣውም ሶሻል ዴሞክራሲ አይዲዮሎጂ [ርዕዮተ ዓለም] ነው፡፡ ፍትሕ፣ አንድነትና እኩልነትን ማዕከል ያደረገ ርዕዮተ ዓለም ነው የሚከተለው፡፡ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ክፍፍል ማምጣትና የማኅበረሰቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ያተኩራል፡፡ እርስ በእርስ ተያይዞ በአንድነት አገርን መቀየር ይቻላል ብሎ ያምናል፡፡ ብዝኃነት ያለውን አገር በፌዴራላዊ ሥርዓት በመተባበርና እጅ ለእጅ በመያያዝ መለወጥ ይቻላል ብሎ እየታገለ ነው፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች