Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የዳቦ ዋጋ ያለ ቅጥ መጨመርን መንግሥት እንደቀላል ነገር በዝምታ ማለፍ የለበትም!

ተከራይ ቋሚ አድራሻ የለውም፡፡ በግሌ አሁን ተከራይቼ የምኖርበት ቤት ሰባተኛ ቤቴ ነው፡፡ ኪራይ ሲጨምርብኝ ይቀንሳል ወደተባለ አካባቢ ሳፈገፍግ፣ በመሀል ከተማ የነበረው ኑሮዬ ዛሬ ወደ ዳር እየተገፋ ነው። አሁን የከተማዋ ዳር የምንላቸው አካባቢዎች ሁሉ መሀሉን በመምሰላቸው የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋቸው እየጨመረ በመሄዱ ከዚህ በኋላ የምንሸሽበት አካባቢና ቅናሽ ፍለጋ የምንፈልግበት ሁኔታም የተዘጋ ይመስላል፡፡ አሁን ማረፊዬ ጀሞ ነው፡፡ ጀሞ አንድ በሚባለው የጋራ ኮንዶሚኒየም ተከራይቼ መኖር ከጀመርኩ አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ሆኖኛል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የቤት ኪራይ በስንቶቻችን ላይ እንደጨመረ መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ ሳያንስ መሻሻል ያላሳየው የዋጋ ንረት ሲታከልበት ራስ ምታታችን ጨምሯል፡፡ ነገሩ በዝርዝር ብሮች ከሚገዛው ዳቦ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠር ክፍያ የሚጠየቅበት የቤት ኪራይ ድረስ የዋጋ ጭማሪው ዕድገትና ፍጥነት ግራ የሚያጋባ መፍትሔ ያጣም ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሌላውን ጉዳይ እንተወውና ስለዳቦ ገበያ የምንኖርበትን አካባቢ መሠረት አድርጌ ያለንበትን ሁኔታ ላመላክት፡፡ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ ክፍል የበለጠ የሚጎዳበት ይሆናል፡፡ በየሄድኩበት ሠፈር የምፈልጋቸውን ዕቃዎች ለመሸመት ደንበኛ የማድረግ ልምድ አለኝ፡፡ በጀሞ ካፈራኋቸው መካከል ከተከራየሁበት ኮንዶሚየም አጠገብ የሚገኝ አነስተኛ ዳቦ ቤት አንዱ ነው፡፡ ጀሞ ከገባሁ ከማግሥቱ ጀምሮ ዳቦ የምገዛው እዚሁ ዳቦ ቤት ነው፡፡ በአጭሩ የአንድ ዓመት ከሦስት ወር ደንበኛነት አለኝ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ዳቦ ቤት 100 ግራም ነው የሚባለውን ዳቦ እገዛ የነበረው በአምስት ብር ነበር፡፡ ይህ ከአንድ ዓመት ከሦስት ወራት በፊት የነበረ ዋጋ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የምገዛው አምስት ዳቦ ስለነበር ለአምስቱ ዳቦ 25 ብር እከፍላለሁ፡፡ ይህ ዋጋ ግን ብዙም ሳይቆይ ስድስት ብር ገባ፡፡ ሦስትና አራት ወር ቆይቶ ሰባት ብር ሆነ፡፡ የአምስቱ ዳቦ ዋጋ 35 ብር ሆነ ማለት ነው፡፡ ከሁለት ወር በፊት ደግሞ ይህ ባለመቶ ግራም ዳቦ በዱቄት ተወደደ ሰበብ ስምንት ብር ገብቶ አረፈው፡፡ ከዚህ ቅጥ እያጣ ከሄደው የዋጋ ንረት የሚያወጣን የለምና እያጉረመረምንም ቢሆንም መግዛታችንን ቀጥለናል፡፡ መቼም 100 ግራም ዳቦ ከዚህ በላይ ሊጨምር አይችልም የሚል እምነት ቢኖረኝም ይህ እምነቴ አልሰመረም፡፡ የተሻለ የስንዴ ምርት ተገኘ የተባለበት ወቅትም በመሆኑ እንዲያ መገመቴ ስህተት አልነበረም፡፡ ግን ስህተት ሆነ፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በወራት ልዩነት በአምስት ብር መግዛት የጀርኩት ዳቦ አንድ አንድ ብር እየጨመረ ስምንት ብር መድረሱ ጭማሪውን በመቶኛ ስናሠላው በአንድ ዓመት ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን እንገነዘባለን፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የስንዴና የዱቄት ዋጋ የተወሰነ ቅናሽ ባሳየበት ወቅት እንኳን የዳቦ ዋጋ አለመቀነሱን ልብ በሉልኝ፡፡ 

የዳቦው የዋጋ ጭማሪው ግን በዚህ የሚያቆም አልሆነም፡፡ የባሰው ነገር ያጋጠመኝ በዚህ ሳምንት ነው፡፡ ነሐሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በስምንት ብር የገዛሁት አንድ ባለ 100 ግራም ዳቦ ከሦስት ቀናት በኋላ በስምንት ብር ልገዛው አልቻልኩም፡፡ ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ እዚሁ ዳቦ ቤት ስሄድ የባለ መቶ ግራሙ ዳቦ ሁለት ብር ጨምሮ አሥር ብር መግባቱ ተነገረኝ፡፡ ከዚህ ቀደም ለሦስት ጊዜ ዋጋ ሲጨምሩ ጭማሪው አንድ አንድ ብር ነበር፡፡ የሐሙሱ ጭማሪ ከእስካሁኑ ተለይቶ በሁለት ብር የመጨመሩ ሚስጥርም ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ ከሁለት ጉርሻ በላይ የማትሆን ዋጋ ይቺ ሚጢጢ ዳቦ በጠቀስኩት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ጨመረ፡፡ ከመቼም ጊዜ  የበለጠ በግሌ ደንግጫለሁ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት አሥር ዳቦ መግዛት ይቻል የነበረው 50 ብር አሁን አምስት ዳቦ ብቻ የሚገዛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሐሙስ ዕለት እንደ እኔው ዳቦ ሊገዙ የመጡ አንድ የቤት እመቤት ጭማሪውን ሲሰሙ የደነገጡትን ድንጋጤ በቃላት መግለጽ አልችልም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ያልተቋረጡ ዋጋ ንረቶች ኅብረተሰቡን ምን ያህል እየጎዳውና እያሸማቀቀው ስለመሆኑ በቀላሉ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ እኚህ ባልቴት ዳቦ ቤት የመጡት ስድስት ዳቦ ለመግዛት ይዘዋት በመጡት ሃምሳ ብር ስድስት ዳቦ ገዝተው ሁለት ብር መልስ ለመቀበል ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ ‹‹አሁንም ጨመራችሁ ኧረ ወዴት እየሄድን ነው›› የምትለዋን ቃል አውጥተው ስድስት ዳቦ ለመግዛት የያዙዋትን 50 ብር አምስት ዳቦ ገዝተውበት ብቻቸውን እያወሩ ሄዱ፡፡ የእኔም ስሜት ከእሳቸው የተለየ አልነበረም፡፡ የዋጋ ጭማሪ መጠኑም ሆነ ፍጥነቱ ያስፈራል፡፡ በዚህ ጭማሪ ልክ ወርኃዊ ገበያችን ያለማደጉን ስናስብ ደግሞ ሁኔታው የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡  

በአንድ ዓመት ውስጥ በዚህ ፍጥነት የዳቦ ዋጋ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ የስንዴ ምርቷን ጨምራ ለውጭ አገር ገበያ ጭምር ያቀረበች አገር ውስጥ እየሆነ ያለ አይመስልም፡፡ ከዚህ ባሻገር የዱቄት ዋጋ መጨመርስ የዳቦውን ዋጋ በዚህን ያህል ደረጃ እንዲጨምር ያስገድዳል ወይ እስከማለት የሚያደርስ ነው፡፡ ከሰሞኑ የተፈጠረው አለመረጋጋት የፈጠረው ይሆናል ብዬም አስቤያለሁ፡፡ ችግሩ የስንዴና የዱቄት እጥረት ነው ወይስ የዳቦ ጋጋሪዎቹ የሚልም ጥያቄ አብሮ የሚያያዝ ነው፡፡ ምክንያቱም ምንም ይሁን ምን አሁን ባለንበት ሁኔታ የዳቦ ዋጋ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት መፍትሔ ሊበጅለት ይገባ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ አምስት ዳቦ መግዛት እንችላለን የምንልም ከዚህ በኋላ እኛም አቅም አይኖረንም ማለት ነው፡፡ 

የአምስት ብር ዳቦ ገዝቶ ለልጆቹ በሻይ ነክሮ ለመብላት እንኳን ከማይቻልበት ደረጃ እየተደረሰ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ ዓመት ዕድሜ ውስጥ የዳቦ ዋጋ በመቶ ፐርሰንት ጨምሯል፡፡ የዳቦ ዋጋ ያለ ቅጥ መናር እንደ ቀላል ነገር በዝምታ የሚታለፍ ጉዳይ መሆን የለበትም። ምክንያቱም የዳቦ ዋጋ መናር በተለይም የቀን ሠራተኛውን፣ በጉልበቱ የሚተዳደረውን፣ ሥራ አጡንና በአጠቃላይ የአብዛኛውን ደሃ ማኅበረሰብ ኑሮ እያናጋ ነው። ዳቦ እንደ ሌላው ሸቀጥና ምርት መታየትም የለበትም፡፡ ሌላው ቢቀር ዳቦ በሻይ ለመብላት እንዲቻል መንግሥት የዳቦ ዋጋን ሊቆጣጠር ይገባል፡፡ ችግሩ በእርግጥም የዱቄት መወደድ ከሆነ ይህንን የማረጋጋት ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን መንግሥት መገንዘብ ይኖርበታል፡፡..

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት