Saturday, June 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገርን ጥቅም አሳልፎ የሰጠው ማን ነው?

በጊደና መድሕን

‹‹ባንዳ›› የሚባለው ቃል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ታዋቂና ረዥም ዕድሜ ያለው፣ አብሮን የኖረና በኢትዮጵያውያን የተጠላ እርጉም ቃል ነው። የአማርኛ መዝገበ ቃላት ማግኘት ስላልቻልኩኝ በእግሊዝኛ ተቀራራቢ ትርጉም ያለውን ‹‹RENEGADE›› የሚለውን የእግሊዝኛ ትርጉሙን መዝገበ ቃላት እንዲህ ፍቺ ሰጥቶታል።  A Disloyal Person Who Betrays or Deserts His Cause, Religion, Political Party, Friend, etc. ሲተረጐም ባንዳ ማለት ዓላማውን፣ ሃይማኖቱን፣ ፖለቲካ ፓርቲውንና ጓደኛውን ወዘተ የሚክድ እምነተ ቢስ ሰው ነው ማለት ነው።

ዛሬ ይኸንን ባንዳ የሚለው ቃል ለማንሳት የተገደድኩት በብዛት የነብሰ በላው ሕወሓት ካድሬዎች፣ ጭፍን ደጋፊዎችና ተከፋይ አክቲቪስቶች፣ እኔን ጨምሮ የሕወሓትን አጥፊ መንገድ ተረድተው የሚቃወሙትን፣ በ2013 ዓ.ም. ኅዳር ወር ጀምሮ የለውጥ ሒደቱን በመደገፍ፣ የትግራይ ሕዝብ ያገለገሉትን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር አባላትን በተደጋጋሚ ‹‹ባንዳ›› ብለው ሲሰድቡንና ከአራት ጊዜ በላይም በዚህ ስም የሚጠሩ ነጠላ ዜማ ለቀው ከሕዝባችን እንድንነጠል፣ ጥቃት እንዲደርስብንና ሞራላችን እንዲወድቅ ከፍተኛ የተቀናጀ ዘመቻ ተካሂዶብናል። በዚህም ምክንያት የፈንቅሉ ትንታግ መሪ መምህር የማነ ንጉሥንና እምብዛ ታደሰን (ኢንጂነር) ጨምሮ 53 የሚደርሱ ጓዶቻችን ተገድለውብናል፡፡ በተወሰነ መልኩም ከቤተሰብና ወዳጅም መገለልን ደርሶብናል።

 አሁን ከላይ ከተሰጠው ትርጉም ውስጥ ለተነሳሁበት ጉዳይ ሌላውን ትቼ ‹‹ዓላማ››፣ ‹‹ፖለቲካ ፓርቲ›› እና ‹‹ጓደኛ›› የሚሉትን ብቻ ልውሰድ። በ1967 ዓ.ም. ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ (ተሓሕት)  ተብሎ የተቋቋመውና በኋላም ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ተብሎ የተሰየመው ድርጅት፣ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ እስከ የመንግሥት ሥልጣን ድረስ ላለፉት 47 ዓመታት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ፣ በአፍሪካና በዓለም የፖለቲካ ምኅዳር ስሙን የተከለ ድርጀት ነው፡፡ አብዛኛው ነገሩ ክፋት ቢሆንም!

ታዲያ ሕወሓት እና ደጋፊዎቹ እኛ ዴሞክራሲን፣ እኩልነትን፣ ማኅበራዊ ፍትሕን፣ ነፃነትን፣ ልማትን፣ የሕዝብ ወሳኝነትን የጠየቅን ሰዎችን፣ በምን መለኪያ ነው የሕወሓት መሪዎች እያሉ እኛ ‹‹ባንዳ›› የምንባለው? እስኪ በሦስቱ የባንዳ መለኪያ ብያኔዎች ሕወሓትን እንመልከተው፡፡ ይኸንን ስንል ሕወሓት፣ የ100 ሺሕ የትግራይ ወጣቶች ሕይወትን እንዲጠፋ፣ የ120 ሺሕ ወጣቶች አካል እንዲጎድልና አገሪቱ በተለይም የትግራይ ሕዝብን በጦርነት እንዲጠበስ ማድረጉን አንርሳ። 

  1. ዓላማውን የሚክድ

ሕወሓት ወደ በረሃ ሲሄድ እንደ ዓላማ ይዞት የሄደው የትግራይ ሕዝብን ከመደብና ብሔር ጭቆና ነፃ አውጥቶ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት፣ ፍትሐዊና የበለፀገች አገረ ኢትዮጵያን መመሥረት ነበር። እና ካለመው አንፃር ሕወሓትን ስንገመግመው ሕወሓት በጎልማሳው ዕድሜው እነዚህን ዓላማዎች ባለማሳካቱና በመክዳቱ ባንዳ ቢባል አይበዛበትም። 

  1.  ፖለቲካ ድርጅቱን የሚክድ

አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ዋና ሀብቱና መገለጫው አባላቱ ናቸው። ሕወሓት ከተወለደበት ቀን ጀምሮ መሪዎቹ ድርጅቱንና አባላቱን በመካድ የግል ንብረታቸው አድርገውታል። ፓርቲው፣ የፖሊት ቢሮ አባላት ገፋ ሲልም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የግል ንብረት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። በተለይም ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ የጥቂት ሰዎች ንብረት እንዲሁም ባፈጠጠ መልኩ ከ1993 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊና ጥቂት አሽከሮቻቸው ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ሆኖ ነበር። በመሆኑም ፖለቲካ ፓርቲውን በመካድ የግል ድርጅታቸው ስላደረጉት ‹‹ባንዳ›› መባል ያለባቸው የሕወሓት መሪዎች ናቸው።

  1. ጓደኞቹን/ጓዶቹን የሚክድ

የሕወሓት መሪዎች በዚህ ጉዳይ ብዙ ወንጀል አለባቸው። በሕወሓት ታጋዮች ዘንድ ጓዳዊነት (Comradeship) ትልቅ ትርጉም አለው። የአንድ ታጋይ የመጨረሻ መሃላውም ‹‹ሥጋ ብፆት›› (እርም የሆነውን የጓዴን ሥጋ ልብላ) የሚለው ነው። ነገር ግን የሕወሓት መሪዎች ጓዶቻቸውን እየበሉ ነው የመጡት፡፡ ለአብነት ሌላውን ትተን አራት ኩነቶችን እናንሳ።

  • 1969 .ም.

‹‹ሕንፍሽፍሽ›› (Political Crisis) በዚህ ጊዜ አውራጃዊነትንና የሕወሓት መሪዎች ተለይተው ኢዴሞክራሲያዊ መንገሥን የተቃወሙት የእንደርታ፣ የተንቤን፣ የራያና የዓጋመ ታጋዮች በሕወሓት ጓዶቻቸውና መሪዎች በጭካኔ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ለዘግናኝ እስርና ስቃይ ተዳርገዋል።

  • 1977 ዓ.ም.

የመለስ ዜናዊ፣ የስብሓት ነጋ፣ የአባይ ፀሐዬና የሥዩም መስፍን ቡድንና አሽከሮቻቸው የጦር አዛዡን አረጋዊ በርሄን (ዶ/ር) እና ምክትል ሊቀመንበሩን ግደይ ዘርአፅዮንን መትቶ ወደ ሥልጣን ለመውጣትና ማሌሊትን ለመመሥረት ባካሄደው ኩዴታ ብዙ ታጋዮች ለእስር፣ ለስቃይና ለሞት ተዳርገዋል። እነዚያ በግፍ በጓዶቻቸው የተረሸኑት፣ የታሰሩትና ለስቃይ የተዳረጉት ታጋዮች እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕን ስለጠየቁ ነበር።

  • 1985 .ም.

የሕወሓት መሪዎች ለሥልጣን ያበቁዋቸው ታጋዮችን በገፍ ያባረሩበት፣ ያሰሩበትና የገደሉበት ወቅት ነበር። በተለይም በሆለታ እስር ቤቶች ማቀው የሞቱትና ተባረው ለመሳፈሪያ እንኳን አጥተው ሰውነታቸውን ለመሸጥ የተገደዱት ሴት ታጋዮች መቼም አይረሱም።

  • 1993 .ም.፣

አገረ መንግሥቱን እየመሩ በነበሩበት ጊዜ ነበር ያጋጠመው፡፡ ታዲያ እነዚያ በ1977 ዓ.ም. እነ አረጋዊ በርሄን ከመለስ ዜናዊ ቡድን ጋር አብረው እንዲባረሩ ያደረጉት ታጋዮች ዕጣ ደርሶዋቸው በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ  ለመባረርና ለስቃይ (ለክስና ሥራ መባረር) ተዳረጉ። የሕወሓት መሪዎች ጨካኞች መሆናቸውን የተገነዘብኩበትና ያዘንኩበት ጊዜ ነበር።

በነዚህ አብነቶች ሲታይም እኛ ሳንሆን ‹‹ባንዳ›› መባል ያለብን ከማሰር፣ ከማሰቃየትና ከመግደል ውጭ የማያቁትን የሕወሓት ቁንጮዎች ናቸው ‹‹ባንዳ›› መባል ያለባቸው።

ሌላው የትግራይ ሕዝብስ ምን አገኘ?

ይኸ ሕዝብ ከላይ እንደተጠቀሰው ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ልማትና አንድነት ያጎናፅፉኛል ብሎ ከፍተኛ መስዋዕት የከፈለላቸው የሕወሓት መሪዎች ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ምን ፈየዱለት? ኪሳራ!

የሕወሓት መሪዎች  ሦስት ትልልቅ ጦርነቶች የትግራይ ሕዝብ ደጁ ድረስ ጎትተው አምጥተውበታል። ከጎረቤቶቹና ሌሎች ኤትዮጵያውያን ጋር አጣልተውታል። በውሸት ሪፖርት ሳይለማ እንደለማ፣ ሳይጠግብ እንደጠገበ እንዲታይ አድርገውታል። በእነሱ በነቀዘ ባህሪ፣ በኢትዮጵያዊ ወገኑ የትግራይ ሕዝብ እንዲጠረጠርና እንዳይታመን አድርገውታል። በእነሱ ነብሰ በላ የፖለቲካ አመራር ዘይቤና የሙስና ታሪክ፣ ተጋሩ እንዲሰቃዩ፣ እንዲታሰሩና እንዲገደሉ ምክንያት ሆነዋል።

አሁንም ራሳቸው በቀሰቀሱት ጦርነት፣ ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ የትግራይ ወጣቶች እንዲገደሉና አካል ጉዳተኛ እንዲሆኑ፣ የትግራይ ሕዝብ በዘመኑ አይቶት ለማያውቀው ስቃይና ችግር አጋልጠውታል። 

የትግራይ ሕዝብ ልጆቹና ራሱ በከፈሉት መስዋዕትነት ወደ ሥልጣን የወጡት የሕወሓት መሪዎች የትግራይ ሕዝብ በአገሩ ኢትዮጵያ የነበረውን (ሊኖረው የሚገባውን) ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሕጋዊ መሠረቱንና ተጠቃሚነቱን በስግብግበነታቸው ምክንያት እንዲያጣ አድርገውታል።

የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት ያለ ጡረታ በመበተን፣ መበታተንን እንጂ አንድነትን የማያበረታታው ሕገ መንግሥት በማፅደቅ፣ በአባቶቻችንና አያቶቻችን ጥበብና ብልኃት ያገኘነውን የባህር በር በማሳጣት፣ ብዙ ዜጎች ያለቁበትን የባድመ ግዛት ያለ በቂ ክርክር እንዲፈረድብን በማድረግ፣ የኢትዮጵያን ሀብትና ገንዘብ በመዝረፍና በማሸሽ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ያሳነሱና ሉዓላዊ ግዛቷን አሳልፈው የሰጡ ታሪክ ይቅር የማይላቸው ‹‹ባንዳዎች›› ናቸው።

በመሆኑም ባንዳ የሚባለው ስም አገሬ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በድዬ ለማላውቀው፣ የአገሬን ጥቅም አሳልፌ አልሰጥም ላልኩት፣ ሕወሓትና አሽከሮቹ የትግራይ በተለይና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአጠቃላይ ጠላት ናቸው ብዬ ለተቃወምኩት፣ የትግራይ ክልልና ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነው ላልኩት፣ የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት የተሻለ አመራር ያስፈልገዋል ብዬ በፅናት ለቆምኩት፣ የሕወሓት መሪዎችና አሽከሮቻቸው ፖለቲካዊ ኃጢዓትና ሌብነት ለተቃወምኩት መሰጠት ያለበት ስም አይደለም፡፡ ታዲያ ለማን? ትርጉሙ ካልተቀየረ በስተቀር ከላይ በትንሹ ባስቀመጥኩት ሥነ አመክንዮና ጥሬ ሀቅ መሠረት ‹‹ባንዳ›› የሚለው ስም ከነ ሙሉ ክብሩ፣ ጥቅሙና ኃላፊነቱ የሚገባው ለነብሰ በላዎቹ የሕወሓት መሪዎችና አሽከሮቻቸው ነው። 

ምክንያትዊነት ይለምልም!

የደቦ አስተሳሰብ አይጠናወተን!

ወጣቱ አትሸወድ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles