Friday, September 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በተሰናባቹ ዓመት የተፈጸሙ ጥፋቶች ወደ አዲሱ አይሸጋገሩ!

አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሊተካ ከሳምንት ያነሱ ቀናት ቀርተዋል፡፡ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዝግጅት ሲደረግ የአሮጌው ዓመት ክራሞቶች ከሁሉም አቅጣጫዎች በቅን ልቦና መታየት አለባቸው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ውስጥ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሮጌውን ሸኝቶ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ሲዘጋጅ፣ መንግሥትም ሆነ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ክራሞታቸውን በሚገባ መገምገም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የቤተ እምነቶች መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ልሂቃን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አመራሮች፣ የሴቶች፣ የወጣቶችና የሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች የአሮጌውን ዓመት ሒሳባቸውን ማወራረድ አለባቸው፡፡ በመደበኛው ሚዲያና በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ውስጥ የተሰማሩ እንዲሁ ሥራቸውንና ያስከተለውን ውጤት ዞር ብለው ማየት ይኖርባቸዋል፡፡ እየተጠናቀቀ ባለው ተሰናባች ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ከባድ የሚባሉ ችግሮች ውስጥ አልፋለች፡፡ ሕዝባችንም እየደረሰበት ካለው የሰላም ዕጦት በተጨማሪ፣ በከባድ የኑሮ ውድነት ሳቢያ ለመግለጽ የሚያዳግት የመከራ ሕይወት እየገፋ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የምትሉ በሙሉ ራሳችሁን ስትገመግሙ፣ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ የድርሻችሁን ኃላፊነት በመቀበል መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ የተሻለ የኑሮ መሻሻል ሲገኝ በኩራት የባለቤትነት ስሜት የሚያሳዩ ሁሉ፣ ለደረሱ ችግሮችና መከራዎችም ተጠያቂነትንም በድፍረት መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ ለመልካም ነገሮችና ስኬት ለሚባሉ ግኝቶች ደረት መንፋት ብቻ ሳይሆን፣ ለውድቀት ጭምር በቀናነት ኃላፊነትን ለመውሰድ ደፋር መሆን ያስፈልጋል፡፡ በመታበይ ስሜት ሌሎች ላይ ጣት ለመቀሰር የሚደረጉ ርብርቦች ያተረፉት ነገር ቢኖር፣ አገርን ወደ ቁልቁለት መግፋትና ሕዝብን መከራውን ማብዛት እንደሆነ ከበቂ በላይ ታይቷል፡፡ እንደ ላባ የቀለለ እዚህ ግባ የማይባል አበርክቶን በሺዎች በማባዛት ራስንና የተጠለሉበትን ቡድን ማጀገን ላይ ከማተኮር፣ በሕዝብ ላይ ለደረሰው መከራና ሥቃይ የግልና የወል ተጠያቂነትን በድፍረት ለመጋፈጥ ግንባር ቀደም መሆን ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ ይልቅ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው በአይረቤ አጀንዳዎች ላይ ጊዜ በማጥፋት፣ ሕዝብና አገርን እያመሱ ለሩቅም ሆነ ለቅርብ ጎረቤቶች ሥጋት መሆን ነው፡፡ የአሮጌው ዓመት ጉዞም ከጦርነት ወደ ጦርነት እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡

ከዛሬ ይልቅ ነገን ተስፋ በማድረግ ብዙ ዕቅዶች ይነደፋሉ፡፡ ተስፋ መሰነቅና ነገን በጉጉት መጠበቅ መልካም ቢሆንም፣ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከሚታሰበው ተስፋ ጋር አልጣጣም እያለ ነው፡፡ ከአገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ተነስቶ በአምስቱም በሮች በሰላም ወጣ ብሎ መግባት ከባድ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ በሰላም ተንቀሳቅሰው ለመሥራትና ንብረት ለማፍራት ቀርቶ፣ ለመዝናናት ወይም ዘመድ ጠይቆ ለመመለስ ካዳገታቸው ሰነባብተዋል፡፡ ሰዎችን አግተው ከሚገድሉ ወይም የማስለቀቂያ ከሚያስከፍሉ ሽፍቶች ጀምሮ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ አንግበው እስከሚፋለሙ ድረስ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብትን አግደዋል፡፡ በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም. በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ግጭት የማስቆም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላም ቢሰፍንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተከሰተው ውጊያና በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች ያሉ ግጭቶችና ጥቃቶች የሕዝባችንን ሕይወት ሲኦል አድርገውበታል፡፡ የአሮጌው ዓመት መከራዎች ወደ መጪው እንዳይተላለፉ፣ ዕቅዶችም ሆኑ ምኞቶች አገርን ማዕከል ያድርጉ፡፡

እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት ለአገር የሚበጁ በርካታ ምክረ ሐሳቦችን ያቀረቡ ድምፆች አዳማጭ አላገኙም፡፡ በአገር ውስጥ ፖለቲካ፣ በጂኦ ፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በሌሎች መስኮች በርካታ ጠቃሚ ሐሳቦች በተለያዩ አገር ወዳዶች ቀርበዋል፡፡ እነዚህ ለአገር የሚጠቅሙ ሐሳቦች በፖሊሲ አውጭዎችም ሆነ በተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ቢደመጡ ኖሮ፣ ወደ አውዳሚ ግጭቶችም ሆነ የማይረቡ እሰጥ አገባዎች ውስጥ ተገብቶ አገር የሥጋት ቀጣና አትሆንም ነበር፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ትምህርት በመቅሰም ግጭትን እስከ ወዲያኛው ማስወገድ የሚቻልበት ዓመት፣ እንደገና ወደ ዕልቂትና ውድመት ተገብቶበት የሚሊዮኖች ተስፋ ሲደበዝዝ እንደ ማየት የሚያም ነገር የለም፡፡ በወርኃ ኅዳር በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ፊርማ ሳይደርቅ ሌላ ዙር ውጊያ አማራ ክልል ውስጥ ሲከሰት፣ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ጥቃት የሚፈጽሙ ሲበዙና በየቦታው ዕገታ ሲስፋፋ መጪውን ጊዜ በተስፋ ለመጠበቅ ምንም ዓይነት ማስተማመኛ አይኖርም፡፡ መነጋገርና መደማመጥ አለመኖሩ ያደረሰው ጥፋት ወደ መጪው ዓመት አይተላለፍ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ለቁጥር የሚያዳግቱ የመከራ ጊዜያት እንዳለፉ አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ አብዛኛው የታሪኳ ክፍል የጦርነትና የውድመት እንደነበረም አይረሳም፡፡ ዘመነ መሣፍንት ተወግዶ የአገረ መንግሥት ምሥረታ ሒደቱ ከተጀመረ ወዲህ፣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ አይደለም እዚህ የተደረሰው፡፡ በጣም በርካታ አድካሚና አሰልቺ ሒደቶች ከመታለፋቸውም በላይ፣ ከፍተኛ መስዋዕትነት ያስከፈሉ ትግሎችና ሽኩቻዎች ተካሂደዋል፡፡ በመጪው ዓመት በወርኃ የካቲት ሃምሳኛ ዓመቱን የሚደፍነው የ1966 ዓ.ም. አብዮት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ዘውዳዊ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቢያስወግድም፣ ከአብዮቱ መባቻ ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር የደረሰው ዕልቂትና ውድመት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ደርግ በኢሕአዴግ ተወግዶ ከሥልጣኑ ከመሰናበቱ በፊት ከቀይና ከነጭ ሽብር ዕልቂት በተጨማሪ ከሶማሊያ ጋር የተደረገው ከባድ ጦርነት፣ እንዲሁም በኤርትራና በትግራይ የተካሄዱ ጦርነቶች ኢትዮጵያንም ሆነ ሕዝቧን መራር ዋጋ አስከፍለዋል፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግም ሆነ ከዚያ ወዲህ ያለው የጥፋት ታሪክ ይታወቃል፡፡ ከዚህ መከራ ውስጥ ነው መውጣት ያቃተው፡፡

ተሰናባቹ 2015 ዓ.ም. ተሸኝቶ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዝግጅት ሲደረግ በሁሉም መስኮች መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ግለሰቦች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለመለወጥ ከሚያዘጋጁት ዕቅድና ከምኞታቸው በላይ፣ መንግሥትና ዜጎች የአገራቸውን ጉዳይ በልዩ ትኩረት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በእጅጉ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአንድ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አብሪ ኮከብ ትታይ የነበረች የዓድዋ ጀግኖች አገር፣ በዚህ ዘመን የግጭትና የድህነት ተምሳሌት ተደርጋ መሳቂያና መሳለቂያ ስትሆን መቆርቆር ይገባል፡፡ ይህ መቆርቆር ኢትዮጵያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከግጭትና ከድህነት የሚያወጣ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በሁሉም አገራዊ ጉዳዮች ላይ በግልጽነትና በኃላፊነት ስሜት ለመነጋገር መዘጋጀት የግድ ይላል፡፡ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካይነት ለሚደረገው ንግግር ከመዘጋጀት ጎን ለጎን፣ በዚህ ወቅት የገጠሙ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ መድረኮችን በቅን ልቦና ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም የታጠቁ ኃይሎች ጋር በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር ሰላም ማስፈን ይገባል፡፡ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን አሁን የተፈጠሩ ችግሮችን መፍታት የግድ ነው፡፡ በተሰናባቹ ዓመት የተፈጸሙ ጥፋቶች ወደ አዲሱ አይሸጋገሩ!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...