በየዓመቱ በአሜሪካ ዋሺንግተን ከተማ የጎዳና ሩጫን የሚያሰናዳው ኖቫ ኮኔክሽን፣ ለተማሪዎች ድጋፍ ለማድረግ ከበጎ አድራጎት ድርጅት በጋራ መሥራት መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የታላቅ አፍሪካ ሩጫ (ግራንድ አፍሪካ ራን) ከአርቲስት ቻቺ ታደሰ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር ‹‹አንድ የትምህርት ቤት ቦርሳ ለአንድ ተማሪ›› የሚል መርሐ ግብር በይፋ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ በሚከናወነው አምስተኛው የታላቅ አፍሪካ ሩጫ የአርቲስት ቻቺ ታደሰ ሶርቱ ሰክሰስ (SOUR TO SUCCESS) ከተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት አጋር ሆነው ለመሥራት መስማማቱ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት ዕገዛ ለሚሹ ታዳጊ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች አስፈላጊውን የትምህርት ቁሳቁሶችና የትምህርት ቤት ቦርሳዎችን ለማቅረብ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡
ለዚህም ዓላማ መሳካት፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚካሄዱ በርካታ የመዝናኛ ሩጫ ዝግጅቶች በስፋት የተለመደውን ተሞክሮ በመውሰድ፣ በጥቅምቱ የአምስት ኪሎ ሜትር ዝግጅት ላይ የሚመዘገቡና ፍላጎቱ ያላቸው ተሳታፊዎች ድጋፉን ለማሰባሰብ መታቀዱ ተብራርቷል፡፡
በዚህም መሠረት ኪውጂአይቪ ‹(Qgiv) በተባለና አዘጋጆቹ ባቀረቡት ድረ ገጽ ላይ የራሳቸውን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ገጽ በመክፈት፣ ሊንኩን ለቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸውና ወዳጆቻቸው በመላክ በመዝናኛ ሩጫው የሚኖራቸው እያንዳንዱን ሜትር ወይም ኪሎ ሜትር ዕርምጃ አስቀድመው ስፖንሰር እንዲያደርጉዋቸው በመጠየቅ ዕገዛ የሚያሰባስቡበት ይሆናል ተብሏል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ አንዳንድ ተሳታፊዎች በግላቸው ለማሰባሰብ ያስቀመጡትን ግብ ሊያሳክላቸው በሚችል መልኩ፣ በያንዳንዱ የጎዳና ሩጫ ርቀት አማካይነት ስፖንሰር የሚያደርጓቸው ወዳጆቻቸውን አፈላልገው ገንዘብ ሊያሰባስቡ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ሌሎች ተሳታፊዎች ዝግጅቱ በሚሸፍነው አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በእያንዳንዱን ኪሎ ሜትር አምስት ወዳጆቻቸው ስፖንሰር እንዲያደርጓቸው በመጠየቅ እገዛውን ሊያሰባስቡ የሚችሉበት አማራጭም ቀርቧል፡፡
በዚህም መሠረት ተሳታፊዎቹ የሚያሰባስቡት ዕገዛ 10 ዶላር፣ 50 ዶላር፣ ወይም ከዚያ በላይ ቢሆን፣ ተሳታፊዎች በዝግጅቱ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ከመዝናኛ ሩጫም በላይ ትርጉም እንደሚኖረው ተቋሙ ገልጿል፡፡
ከተሳታፊው የሚሰበሰበው ገንዘብም በዋናው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ድረ ገጽ ላይ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ የሚሰበሰበው ገንዘብ በቀጥታ ወደ ቻቺ ታደሰ ‹‹ሶር ቱ ሰክሰስ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚገባ ይሆናል፡፡
የተሰበሰበው ገንዘብ የትምህርት ቁሳቁስ የያዙ የትምህርት ቤት ቦርሳዎች ግዥ የሚውል ሲሆን ዕገዛ ለሚሹ ታዳጊ ተማሪዎች ይቀርባል ተብሏል፡፡
የታላቅ አፍሪካ ሩጫ ‹‹አብሮነት መሻል ነው›› በሚል መሪ ቃል በየዓመቱ በአሜሪካ እየተሰናዳ ይገኛል፡፡ ዓመታዊ ውድድሩ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብ፣ የመጀመርያው ትውልድ ልጆችን ከባህላቸው ጋር የበለጠ ማቀራረብና ለተለያዩ በጎ ሥራዎች ገቢ ማሰባሰብን ዓላማው አድርጎ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በዓመታዊ የጎዳና ሩጫው በሺዎች የሚቆጠሩ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት እንደሚሳተፉም ተጠቁሟል፡፡