Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዋዜማው የገበያ ድባብ

የዋዜማው የገበያ ድባብ

ቀን:

አሮጌውን ዓመት ሽኝቶ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዝግጅቱ ከወዲሁ ተጧጡፏል፡፡ ርዕሰ ዓውደ ዓመት ከሌሎች በዓላት ለየት ከሚልባቸው ውስጥ ዘር፣ ቀለም እንዲሁም ሃይማኖት ሳይለይ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ በድምቀት መከበሩ ነው፡፡

አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ልብስ፣ አዲስ አስተሳሰብና አዲስ ተስፋ አብረው ይመጣሉ።

መጪው 2016 ዓ.ም. ደግሞ ምን ይዞ እንዲመጣ ትመኛላችሁ? ሲባሉ ብዙዎች እንደ እህልና ውኃ የተራቡትንና የተጠሙትን ሰላም አንድነትና ፍቅርን  ይዞላቸው እንዲገባ  ምኞትና ጸሎታቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ሰላምና መረጋጋት ወጥቶ የመግባት፣ ለብሶ የማጌጥና በልቶ የመጥገብ መሠረት ነውና፡፡

‹‹አንተ ደህና ትውል ዘንድ ጎረቤትህ ደህና ይዋል›› እንደሚባለው በአንድ አካባቢ የሚሰማውና የሚታየው ጦርነት  ሌላውን አካባቢ መረብሽና ማስጨነቁ አይቀርም፡፡

ልጅ በጦርነት ቀጣና ውስጥ ሆኖ እናት ብቻዋን የምታከብረው የዕለቱን በዓል ሳይሆን፣ ያለፉ መልካም ትዝታዎችን ወደኋላ በማሰብ እንዲሁም ከአሁን አሁን ምን እሰማ ይሆን? በማለት በቆፈን ተከባ በእንባ ታጅባ ነው፡፡

በሌላ በኩል ከዕለት ወደ ዕለት  ከዓመት ወደ ዓመት በፍጥነት እየጨመረ ያለው የኑሮ ውድነት በተለይ ደግሞ በዓልን ተንተርሶ ይብስበታል፡፡

ኅብረተሰቡ አዲሱን ዓመት 2016 እንደ ወትሮው ሁሉ መልካም ምኞትን በመሰነቅ  በተስፋ ለመቀበል ከላይ ከታች ማለቱ አልቀረም፡፡ እንደወትሮው ሁሉ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የገበያ ማዕከላትና የመሳሰሉት ቦታዎች በሰዎች ሲጨናነቁ ይስተዋላሉ፡፡

‹‹ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይሆንም›› እንደሚባለው ሁሉም ሰው እንደ አቅሙ በዓሉን ለመቀበል ከወዲሁ እየተሰናዳ ነው፡፡ 

ወ/ሮ ፀሐይ አባተ (ስማቸው የተቀየረ) በመገናኛ አካባቢ ለዓመት በዓል ገበያ ለመገብየት ሲዘዋወሩ ያገኘናቸው እናት ናቸው፡፡ ደረቅ የሱዳን ሽንኩርት በስድሳ ብር መሸመታቸውን የተናገሩት እናት የፈረንጅ እንቁላል በአሥር ብር  እንደገዙ አክለዋል።

በሌላ በኩል ጥሩ ያሉትን ለጋ ቅቤ አንድ ኪሎ በ800 ብር ገዝተው እንዳስቀመጡና ሌሎች የበዓል ግብዓቶችን ከወዲሁ እያሟሉ እንደሆነም ተናግረዋል።

 የዶሮና የበጉን ገበያ ገና እንዳላዩት የሚናገሩት ወ/ሮ ፀሐይ፣  ነገር ግን ምን መግዛት እንዳለባቸው  ኪሳቸው ከወዲሁ ሳይነግራቸው አልቀረም፡፡

ሃቻምና ለበዓል ጥሩ የሚባል በግ ገዘተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር  በመልካም ሁኔታ አሳልፈው እንደነበር አስታውሰው፣ ዓምና ደግሞ በዚያው ገንዘብ ከዓይንም ሆነ ከጥርስ የሚገባ በግ በማጣታቸው ሁለት ዶሮዎቸን ገዝተው እንደዋሉ ያስታውሳሉ።

‹‹ብናማርረውም እየባሰ መሄዱ አልቀረምና ተመስገን ማለቱ ይሻላል፤›› የሚሉት ወ/ሮ ፀሐይ፣  ዘንድሮ ደግሞ ከዓምናው ሁለት ዶሮ ወደ አንድ ዶሮ ዝቅ እንደሚሉ  ከወዲሁ ተናግረዋል፡፡

ከቤት ኪራይ ጀምሮ በላይ በላያቸው ላይ እየጨመረ ያለው የዕለት ፍጆታዎች  ዋጋ  መናር፣ ኑሮ እነሱ ባሉት ሳይሆን  እሱ ባለው መንገድ እያስኬዳቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት ሀብታምና ደሃ በሚባለው መካከል ያለው ልዩነት በጣም ከመስፋቱ የተነሳ መካከለኛ የሚባለው ደረጃ ጠፍቷል የሚሉት ወይዘሮዋ፣ የተሳካለት ወደ ማይደረስበት ሀብታምነት ሲመነደግ ያልሆነለት መካከለኛ ደግሞ ወደ ለየለት ድህነት   በመውረድ  የዕለት ጉርሱን ለመሸፈን ሲጣጣር ይታያል ሲሉ ያስረዳሉ።

የበግ ዋጋ ሦስትና አራት ሺሕ ብር በነበረበት  ወቅት ገዝተው  ያሳለፉት እናት፣ በዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል ግን ከተገኘ የቅርጫ ሥጋ ይህ ካልሆነ ደግሞ  ልኳንዳ ቤት በመሄድ እንዳቅማቸው በኪሎ በመግዛትና አንድ ዶሮ በመጨመር ለመዋል  እንዳሰቡ ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በበኩሉ መጪውን አዲስ ዓመት በማስመልከት የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር የተለያዩ ባዛሮችን ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

ከነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በ25 ዋና ዋና የከተማዋ አደባባዮች  የተለያዩ ምርቶች በስፋት መቅረባቸውንና ኅብረተሰቡም ወደ ባዛሮቹ በመሄድ  የሚፈልገውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ መት መሸመት መጀመሩን፣  የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

ባዛሮቹም ከክልሎችና ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት በቂ የሆነ የበዓል ምርቶችን ማቅረባቸውን አክለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ 172 የእሑድ ገበያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በእነዚህ ገበያዎች የተለያዩ የበዓል ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እንደሚሆኑ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የእሑድ ገበያዎቹ በዋነኛነት ቅዳሜና እሑድ ብቻ ይሰጡ እንደነበር ገልጸው በአሁኑ ወቅት ግን በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከእሑድ እስከ እሑድ ክፍት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ የሚገኙ 152 የኅብረት ሥራ ማኅበራት በየወረዳው እንደ ሽንኩርት፣ ጤፍ፣ ስንዴና ሌሎች ግብዓቶች እንዲያቀርቡ ተደርገዋል የሚሉት ዳይሬክተሩ ሰባት እነሱ መካከል ትላልቅ የገበያ ማዕከላት አምስቱ የቁም እንስሳ ማዕከላት ናቸው ያሉ ሲሆን፣ ብርጭቆ የሚባለው የበግና የፍየል መሸጫ፣ እንዲሁም ሸጎሌ የዳልጋ ከብት ገበያ ማዕከል፣ ቄራ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል ይገኙበታል ብለዋል፡፡

እንዲሁም መሳለሚያ አካባቢ የሰብል ምርት ማዕከላት መቅረባቸውን አክለዋል። በእነዚህ ማዕከላት ከ1.2 ሊትር በላይ የምግብ ዘይት እንዲሁም ወደ 25 ሺሕ ኩንታል  የዳቦ ዱቄት መቅረቡን የተናገሩት አቶ ሰውነት፣ 52,803 ኩንታል ጤፍ የቀረበ ሲሆን፣ 39 ሺሕ ኩንታል ቀይ ሽንኩርት በተመሳሳይ 1,048 ኩንታል ነጭ ሸንኩርት መቅረቡን አብራርተዋል።

በእነዚህ የገበያ ማዕከላት የቀረቡ ምርቶች በተሻለ መጠን ከመደበኛው ገበያ ጋር በዋጋ ሲነፃፀሩ በተሻለ ደረጃ  የዋጋ ቅናሽ  እንዳላቸው  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በማዕከላቱም እንቁላል በዘጠኝ ብር፣ እንዲሁም ቀይ ሽንኩርት ከ47 ብር ጀምሮ እስከ 50 ብር እየተሸጡ መሆናቸው አክለዋል።

ሪፖርተር በትናንትናው ዕለት በአንዳንድ የገበያ ማዕከላት በመዘዋወር  የነበረውን ግብይት ተመልክቷል፡፡ ንግድ ቢሮው  ከከፈተው ባዛር መካከል ሳር ቤት አካባቢ  ያለው አንዱ ነው፡፡

በዚህ ባዛር ከኦሮሚያ ክልል ከአሰላ አካባቢ ምርታቸውን ያቀረቡ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች በብዛት ይገኛሉ።

የጦሳ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር ዩኒየን የማርኬቲንግ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሁሴን አማን፣ ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒየኖች ለከተማዋ ነዋሪዎች ምርታቸውን በስፋት እንዳቀረቡ ተናግረዋል።

ከመቶ ሺሕ በላይ እንቁላሎችን እንዳቀረቡ የሚናገሩት አቶ ሁሴን፣ የፈረንጅ  የቄብ ዶሮ እንቁላል በዘጠኝ ብር ዋጋ እየሸጡ መሆኑን ለመታዘብ ችለናል።

በተመሳሳይ መልኩ የስንዴ ዱቄት በኩንታል 7,200 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ ይህ የስንዴ ዱቄት ከባዛር ውጭ ባለው ገበያ እስከ ዘጠኝ ሺሕ ብር ይሸጥ እንደነበር አቶ ሁሴን አክለዋል።

ከ11 ሺሕ እስከ 12 ሺሕ ብር ይሸጥ የነበረውን ጤፍ ከ7,500 እስከ 9,000  ብር  እንደየ ምርቱ ጥራት ለመሸጥ መዘጋጀታቸውን አክለዋል።

በሌላ በኩል የሰላሌ ነጭ ማኛ ጤፍ በኪሎ 105 ብር፣ ሠርገኛ ጤፍ 92 ብር  በትናንትናው ዕለት እየተሸጠ የዋለ ሲሆን፣ የቡኖ በደሌ ቅቤ 650 ብር በኪሎ ሲሸጥ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

በወቅቱ የበዓል ገበያን በባዛሩ ሲገበያዩ የነበሩ ነዋሪዎች በአቅርቦቱ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ዋጋቸው ከዚህ የተሻለ ቢሆን ጥሩ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ አየለ ጀባ ባለፈው ሰኞ በመገናኛ አካባቢ የእሑድ ገበያ ላይ በርከት ያለ ሽንኩርት ይዘው ሲሸጡ ነበር ያገኘናቸው፡፡

ከሰሞኑ በሱዳን በኩል የሚገባው ሽንኩርት የተወሰነ በመቀነሱ፣ ቅዳሜና እሑድ ከነበረው ገበያ አንፃራዊ ጭማሪ ቢያሳይም፣ በቀጣይ ግን በዓሉ እየቀረበ አቅርቦቱ እንደሚጨምር አቶ አየለ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡

በወቅቱም በኪሎ 70 ብር የነበረው የሱዳን ቀይ ሽንኩርት በ55 ብር እየተሸጠ የዋለ ሲሆን፣ ነጭ ሸንኩርት 250 ብር በኪሎ፣ እንዲሁም የፈረንጅ እንቁላል በአሥር  ብር ሲሸጥ እንደነበር መታዘብ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...