አፍሪካ እ.ኤ.አ. ከ2020 ወዲህ ስምንተኛ የሆነውን መፈንቅለ መንግሥት ያስተናገደችው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትን እያስተናገዱ በሚገኙት በተለይም የቀድሞ የፈረንሣይ ቅኝ ግዛት አገሮች መፈንቅለ መንግሥቶቹ በሕዝብ ይሁኝታ የተቸራቸው ናቸው፡፡
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር የተከናወነው መፈንቅለ መንግሥት ዜናው እንኳን ሳይደርቅ፣ በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ጋቦን የተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትም በሕዝቡ ይሁንታን የተቸረው ሆኗል፡፡
በጋቦን ላለፉት 55 ዓመታት በምርጫ እየተሳበበና በቤተሰብ እየተወራረሰ የዘለቀው ሥልጣንም አክትሟል ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ1967 ጀምሮ ለ49 ዓመታት አሁን በቤት ውስጥ ቁም እስር በሚገኙት የፕሬዚዳንት ዓሊ ቦንጎ አባት ኦማር ቦንጎ ስትመራ የነበረችውን ጋቦን፣ ከ2009 በኋላ የተረከቧትም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዓሊ ቦንጎ ነበሩ፡፡

በወቅቱ ከንጉሣዊ የሥልጣን ሽግግር ብዙም የተለየ አልነበረም በሚል ሲተች የነበረውን ምርጫ አሸንፈው ፕሬዚዳንት የሆኑት ቦንጎ፣ ከሳምንት በፊት ነበር ሥልጣን ከያዙ ወዲያ በተደረገው ሦስተኛ ምርጫ ዳግም ማሸነፋቸው የተገለጸው፡፡
ይሁንና የአሁኑ ምርጫ እንደቀድሞው በትችት ብቻ የታለፈ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በምርጫው ውጤት ቦንጎ 64.3 በመቶ፣ እንዲሁም ተቀናቃኛቸውና ከዚህ ቀደም የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት አልበርት ኦንዶ ኦሳ 30.8 በመቶ ድምፅ ማግኘታቸው በተገለጸ በሰዓት ልዩነት ውስጥ፣ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ ተከናውኗል፡፡
አሁን ላይ በቁም እስር የሚገኙት ቦንጎ እ.ኤ.አ. የ2016 ምርጫን ተከትሎ የተከሰተውን ብጥብጥ ለማርገብ የተጠቀሙበትን ዕድል ዛሬ ላይ አላገኙም፡፡ በወቅቱ 50 ሰዎች የሞቱትም የሳቸውን ማሸነፍ ትክክል አይደለም በሚል በተነሳ ተቃውሞ ከፀጥታ አካላት ጋር በነበረ ግጭት ነው፡፡
2019 ለቦንጎ መፈንቅለ መንግሥት ሊገጥማቸው እንደሚችል ያሳየ ሙከራም ተደርጓል፡፡ የ2023ቱ ደግሞ ዕውን ሆኖ በቤተሰባቸው ላለፉት 55 ዓመታት የተያዘው ሥልጣን አክትሟል፡፡
ዘ ስታር እንደዘገበው፣ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ የሕዝቡን ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በተለይ በጋቦን ዋና ከተማ ሊበርቪል የተደረገው የድጋፍ ሠልፍ ለመከላከያው የጀርባ አጥንት ሆኖታል፡፡
ላለፉት በርካታ ዓመታት በሙስና መዘፈቋ የሚነገርላት ጋቦን፣ የዓለም ነዳጅ አምራች አገሮች (ኦፔክ) አባል ናት፡፡ በቀን ከ200 ሺሕ በርሜል ነዳጅ በማምረትም ትታወቃለች፡፡ ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የዘንድሮ መረጃ በጋቦን ካሉት 2.4 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ሲሶ ያህሉ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖሩ ያሳያል፡፡
ጋቦን የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) አባል ባትሆንም፣ በአገሪቱ የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በቀጣናው ውስጥ ሌላ ውጥረት አንግሷል፡፡
ኢኮዋስ በኒጀር የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለመቀልበስና ተፈናቃዩን ወደሥልጣን ለመመለስ ያስችላሉ በሚላቸው መንገዶች ዙሪያ እየመከረ ቢሆንም፣ የማኅበረሰቡ አባል ባልሆነችው ጋቦን የተከሰተው መፈንቅለ መንግሥት እንቅፋት ይሆንበታል ተብሎ ተገምቷል፡፡
ከዚህ ቀደም አምስት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸውን የአፍሪካ አገሮች ከአባልነት ያገደው የአፍሪካ ኅብረት፣ ጋቦንንም አግዷል፡፡ ሆኖም የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል ብራይስ ኢንጉኤማ፣ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ደማቅ በተባለለት ሥነ ሥርዓት የሽግግር መንግሥት መሪ ሆነው ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ተሾመዋል፡፡
ቢቢሲ እንደሚለው፣ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሐላ የፈጸሙት ጄነራሉ፣ በጋቦን ነፃና ግልጽ ምርጫ በማካሄድ ሥልጣኑን ለሲቪል መንግሥት እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡
በጋቦኒ ቴሌቪዥንና በተለያዩ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ ሥርጭት በተላለፈው የኢንጉኤሜ በዓለ ሲመት፣ በተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዘመን ሲያገለግሉ የነበሩ ሚኒስትሮችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለሥልጣናት ታድመዋል፡፡
በቤተ መንግሥት ውስጥ የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የደገፉት የዓሊ ቦንጎ ተቀናቃኝ አልበርት ኦንዶ ኦሳ፣ የሲቪል አስተዳደር በቶሎ ሥልጣን እንዲረከብ ጠይቀዋል፡፡
ከፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች ውስጥ ባለፉት ሦስት ዓመታት ስድስተኛው መፈንቅለ መንግሥት የተከናወነባት ጋቦን፣ ፈረንሣይ ጫናዋን ለማጠናከር ከምትሠራባቸው አገሮች አንዷ ነበረች፡፡
እንደ ተመድ ሁሉ ፈረንሣይም መፈንቅለ መንግሥቱን ያወገዘች ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ፕሬዚዳንት ኢንጉኤማን አስደምሟል፡፡
በዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግርም የውጭ አገሮች የጋቦን መፈንቅለ መንግሥትን ማውገዛቸው ‹‹አስገርሞኛል›› ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡