መንግሥት የጳጉሜን ወር የዘንድሮን ስድስቱን ቀናት የኢትዮጵያን ትናንት፣ ዛሬና ነገን ታሳቢ ያደረጉ ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች የሚዘከሩበት ቀናት እንዲሆኑ ወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት ጳጉሜን አንድ የአገልጋይነት ቀን ሆኖ ይውላል፡፡ በዚሁ ዕለት ከጠዋት ሁለት ሰዓት ተኩል እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ የየሴክተሩ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ሹማምንት ጨምሮ እስከ ፈጻሚ ድረስ ያሉት ሠራተኞች የሕዝቡን ጉዳዮች በጥሩ መንፈስ እየተቀበሉ ዳር ለማድረስና ለማስፈጸም የሚያስችል ቅን አገልግሎት ሲሰጡ እንደሚውሉ ተገልጿል፡፡
የጤና እና የትራንስፖርት ሚኒስትሮች ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ጋር በመሆን፣ በተለይ በጳጉሜን መባቻ ስለሚታሰበው የአገልጋይነት ቀን ነሐሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያን እናገልግል›› የሚል መሪ ቃል ባለው በዚሁ ቀን ምናልባት ከአቅም በላይ የሆነና ሊሠረዝ የማይችል ዓለም አቀፍ ስብሰባ ካልሆነ በስተቀር ምንም ዓይነት ስብሰባ እንደማይካሄድ፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ሹመኞችና አመራሮች ኅብረተሰባቸውን ዝቅ ብለው ማገልገል ምን እንደሆነ በተግባር የሚያሳዩበትም ይሆናል ተብሏል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በወትሮው ክፍያ የሚፈጸምባቸው አገልግሎቶች ሁሉ በነፃ የሚሰጡባቸው ዕለት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ያህል በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፍ የመንግሥት ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና ሌሎችም ተቋማት እንደየፕሮግራማቸው ከክፍያ ነፃ የሆነ አገልግሎት የሚሰጡበት ይሆናል፡፡
በተለይም የመንግሥት ሹማምንትና ኃላፊዎች ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በቢሮአቸው ብቻ ተቀምጠው አቅጣጫ የሚሰጡበት ሳይሆን ወርደውና ፈጻሚውን ተክተው የሚሠሩበት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ይህ ዓይነቱን አገልግሎት በነፃ መስጠት ምን ያህል ክብር እንዳለው በተጨባጭ የሚያሳዩበት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩትን ችግሮች በመረዳት በሚቀጥለው አዲሱ ዓመት መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ግንዛቤ የሚጨብጡበት መሆኑንም አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ደረጃ ልትደርስ የቻለችው ቅን ልቦና ባላቸው አገልጋዮቿ መሆኑን ገልጸው፣ እንደ እነዚህ ዓይነቶቹ አገልጋዮችም በዕለቱ እንደሚዘከሩ፣ ለወደፊቱም ቅን አገልጋዮች እንዲበዙ ለማድረግ የሚያስችል ጥሪ የሚተላለፍበትና ሌሎችም ከዚህ ተሞክሮ ልምድ በመቅሰም ቅን አገልግሎት ለማበርከት የሚነሳሱበት ዕለት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጠቃሚና ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ተቋማት እንዳሉ፣ ከእነዚህም አንዱና ዋነኛ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ዓለም በሩን ዘግቶና ሥራ አቁሞ በተቀመጠበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ አገሮች የወረርሽኙ መከላከያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በማጓጓዝ የሕዝብ መከታነቱን ለዓለም አስመስክሯል፡፡
አየር መንገዱም የሕዝብ መከታ መሆኑን ሊያስመሰክርና በዓለም ስመጥር ሊሆን የቻለው ቅን ልቦና ባላቸውና ምሥጋና ሊቸራቸው በሚገባቸው ሠራተኞቹ ብርታትና ጥንካሬ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
‹‹መልካምና ቅን አገልጋይ ማለት ለማኅበረሰቡ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛነት ያለው፣ የጎደለውን ሞልቶና ከተሰጠውም አልፎ የሚሠራ ነው፤›› ያሉት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደ ሚኒስትሯ አባባል ጳጉሜን አንድ የአልግሎት ቀን ሆኖ እንዲውል ያስፈለገው እስከ መስዋዕትነት ድረስ ቅን አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን ለማመስገን፣ እንዲሁም ቅን አገልግሎት ምን ማለት እንደሆነ በማኅበረሰቡ ዕሳቤ ውስጥ እንዲሠርጽና እንደያድግ ለማድረግ የሚያስችሉ መድረኮችን ለመፍጠር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጳጉሜን አንድ የአልግሎት ቀን በሁሉም ዘርፍ ያሉትን አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ያካተተ፣ በቅንነት እያገለገሉ ያሉት የሚመሰገኑትና በተለያዩ ዘርፎች የሚታዩ ውስንነቶች የሚሻሻሉበትን አካሄድ የሚጠቁምበት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በጤናው ዘርፍ መደበኛውን አገልግሎት በርህራሄ፣ በፍቅርና በመስዋዕትነት የተላበሰ አገለግሎት ከመስጠት ባሻገር በየዓመቱ ‹‹በጎነት ለጤናችን›› በሚል መሪ ቃል ነፃ የምርመራና የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ለ1.4 ሚሊዮን ሰዎች የምርመራና የሕክምና አገልግሎት በነፃ እንደተሰጠ ጳጉሜን 1 ቀንን ደግሞ ቢያንስ እስከ 200 ሺሕ ሰዎች የመስቀል አደባባይን ጨምሮ አማካይ በሆኑ ቦታዎች የምርመራና የሕክምና አገልግሎት በነፃ ለመስጠት እንደታቀደ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበረሰቡ የአልግሎቱ ተቋዳሽ እንዲሆን ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው በአፍላ የዕድሜ ክልል ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በማስተማርና አመራር በመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት የሚወጡ መምህራንና ከ2.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች እንዳሉ አመልክተው፣ ከእነዚህም መካከል በታታሪነታቸውና በቅን አገልጋይነታቸው ሊመሠገኑ ክብር ሊቸራቸው የሚገባቸው እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በአገልግሎት ቀን አጋጣሚ በሚዘጋጀው መድረክ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልጋይነት እንዴት ነው የሚታየው? በጥሩ ሁኔታ የሚሰጡ አገልግሎቶች የት አካባቢ ያሉ ናቸው? መገለጫቸው ምንድነው? አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል ክብርና ምሥጋና ሊቸራቸው የሚገቡ እነማን ናቸው? በኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ እያጋጠሙ ያሉት ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውስ ምንድናቸው? በሚሉ ርዕሶች ላይ ምክክር ይኖራል፡፡
‹‹በመድረኩ ላይም ኢትዮጵያን ለ38 ዓመትና ከዚያም በላይ ያገለገሉና ወደ ጡረታ የተቃረቡ፣ በመልካም አገልጋይነታቸው የሚታወቁ የመንግሥት ሠራተኞች፣ እንዲሁም ወደ ሥራ ለመግባት የተዘጋጁ ተማሪዎች ይታደማሉ፡፡ ወደ ጡረታ ለተቃረቡ ሠራተኞችም ዕውቅና ይሰጣቸዋል፡፡ ክብርና ምሥጋናም ይቸራቸዋል፤›› ብለዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ ፕሮግራም ለአንድ ጊዜ ብቻ ተግባራዊ ሆኖ የሚቀርብ ሳይሆን ቀጣይነትና ዘለቄታዊ እንዲሆን ለማድረግ ከመንግሥታት ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው፣ በዚህም የመንግሥትን አሠራር ለመቀየርና ለማሻሻል የሚያስችል አገር በቀል የሆነ የአገልግሎት ማሻሻያ ፕሮግራም እንደተቀረፀ ከኮሚሽነሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡