Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢትዮጵያ ቁልፍ ችግር

የኢትዮጵያ ቁልፍ ችግር

ቀን:

በታከለ ታደሰ (ዶ/ር/ተባባሪ ፕሮፌሰር)

በአሁኑ ወቅት በሚታየው ስለኢትዮጵያ ቁልፍ ችግር ጉዳይ የሚሰማኝን ለመግለጽ ነው ይህችን አጭር ጽሑፍ ልጽፍ የፈለግሁት፡፡ ይህንን ከባድ ችግር አንስቼ ለመናገር ያበቃኝ ምን እንደሆነ ልንገራችሁ፡፡ በራስ መተማመኑን ያገኘሁት ጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ ከተማርኩት የትምህርት ዓይነት ነው፡፡ እንግሊዝኛን እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋ ለማይናገሩ ሰዎች እንዴት አንግሊዝኛን ማስተማር ይቻላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችም የትምህርት ዓይነቶች ይሰጡ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ለእኔ የጠቀመኝ “Sociolinguistics” (ማኅበራዊ ሥነ ልሳን) የሚባለው የትምህርት መስክ ነበር፡፡ አገራችን የልሳነ ብዙ አገር ስለሆነች ይህ የትምህርት መስክ ጠቃሚ ነው፡፡ እሱ ነው ያደፋፈረኝ፡፡ በዚህ ላይ ፖለቲካ አልባ ነኝ፡፡ ይህም ማለት ሥልጣን የሰውን ልጅ ሁሉ ለመጥቀም ካልተሠራበት በአፍንጫዬ ይውጣ የሚለውን መርህ ነው የምከተለው ማለት ነው፡፡

የማኅበራዊ ሥነ ልሳን ትምህርት በሁለት ይከፈላል፡፡ በንዑስና በዓብይ፡፡ እንግዲህ ዕውቀት ያለው ያስፋፋው፡፡ ለአሁኑ በምሳሌ ለማሳየት ያህል ችግር ከሌለ በስተቀር በንዑሱ ደረጃ አንድን ባለሥልጣን አባት እንኳን ቢሆን አደባባይ ወጥቶ ሥልጣን ላይ ያለ ልጁን ነገሮች ሁሉ በሥርዓት ከተሟሉ “አንተ“ ብሎ ለመጥራት አይችልም፡፡ የማኅበራዊ ሥነ ልሳን ሕግ ያስገድደዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምናልባት ልጅ የታሪካዊት ታላቅ አገር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን ይችላልና፡፡ እንዲሁም እኔን የ87 ዓመት ሰው አንድ የ18 ዓመት ወጣት ባለጌ ካልሆነ በስተቀር “ታኬ” ብሎ ሊጠራኝ አይችልም፡፡ በጣም በጣም ካላቀረበኝ በስተቀር፡፡ የዚህን ሐሳብ ጥልቀትና ስፋት መዝኑት፡፡ የንዑሱ ክፍል  በዚሁ ይብቃኝና ወደ ዓብዩ ክፍል ልሂድ፡፡

ዓብዩ የሥነ ልሳን ክፍል የሚመለከተው አገርን ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የልሳነ ብዙ አገር ናት፡፡ በደርግ ዘመን በተጠናው ጥናት መሠረት 75 ቋንቋዎች የሚነገሩባት አገር ናት፡፡ ይህችን አገር ለማስተዳደር የሚቻለው እያንዳንዱን ቋንቋ ተናጋሪ ነገድን በማያስቀይም መንገድ ለቋንቋው የሥራ ቦታ መሰጠት አለበት፡፡ ቦታውም የተሰጠበት ምክንያት አሳማኝ በሆነ ሥርዓተ ቃል መብራራት አለበት (ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ብሔረሰብም ብሔርም አይደሉም፣ ነገዶች ናቸው)፡፡ ሁሉም ቋንቋዎች  ግን አንድ እየወሰነች ቦታ ላይ ለሥራ ተግባር መቀመጥ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ እኔ አሁን ቤቴ ሆኜ ነው የምሠራው፡፡ ትክክለኛ ቦታዬ ነው፡፡ ነገር ግን መገናኛ ሄጄ መኪኖች በሚርመሰመሱበት አደባባይ አስፋልት መንገድ ላይ ሆኜ ጠረጴዛዬን አስቀምጬ ሥራዬን ብቀጥል ምን እባላለሁ?! መልሱን እስቲ አስቡበትና ጥያቄው ለምን እንደ ተጠየቀም አሰላስሉ፡፡

ስለዚህ ቋንቋ ሥራ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ፡ አንድን የመጀመርያ ቋንቋ ተናጋሪ ኅብረተሰብ፣ ከሌላው  ቋንቋ ተናጋሪ ለይቶ ያሳያል፡፡ ይህም የመከፋፈልና የመለያየት ተግባር ያከናውናል ማለት ነው፡፡ በአገራችን በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በትግራይ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በወላይታ እያለ ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን ሁላችንንም ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስረን ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ሁላችንንም ለመነጋገር የሚያስችለን ደግሞ አማርኛ ነው፡፡ አገራችን እዚህ የልሳን ልዩነቶች የፖለቲካ ማጥ ውስጥ ከገባች ሰንብታለች፡፡ ታዲያ ጥሩ አይሆንም፡፡ ሳትሰምጥ ቶሎ መውጣት አለባት እላለሁ፡፡ በተፈጥሮ ልሳንን መበላለጥ አይቻልምና፡፡ መነሳት ያለብን የአገራችን የኢትዮጵያ መሬት ለሁላችንም እኩል አንጡራ ሀብት ናት ብለን ነው፡፡ ከዚህም በመቀጠል በውስጧ የሚኖሩት 75 ዓይነት ቋንቋ ተናጋሪዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው የሚለውን መቀበል አለብን፣ እውነታም ስለሆነ፡፡

እንግዲህ አሁን ከላይ የተጠቀሱትን እውነታዎችን ጥሶ ኢትዮጵያን የሚያምሳት ቋንቋ ነው፡፡ ለምን ቢባል ኅብረተሰባችንን ከመለያየቱም በላይ በኅብረተሰባችን ውስጥ ቋንቋዎቹ የሚሰጡት ተግባርና የሚይዙት ቦታ ምን ይሁን? የሚለው ጥያቄ በሥነ ሥርዓት ታስቦበት ስላልተመለሰ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በአገራችን ውስጥ አንጃ ግራንጃ የፈጠረው የአማርኛ የብሔራዊ ቋንቋ መሆን ነው እላለሁ፡፡ ይህም ማለት በድፍን ኢትዮጵያ ውስጥ እሱ ብቻ የመንግሥት ሥራ (ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ ማዘጋጃ ቤት፣ አገር አስተዳደር፣ ወዘተ.) በጽሑፍ ውሎ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ መሥራቱ ብቻ ይመስለኛል፡፡

ለእኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቋንቋ ልዩነት አንደ ነጭና ጥቁር ሰው ዓይነት የዘር ልዩነት ሆኖ አይታየኝም፡፡ ኢትዮጵያውያን የምንለያየው ትንሽ በቆዳ ቀለምና በትልቁ ደረጃ በቋንቋ ነው፡፡ ስለቋንቋ ምንነት ለማወቅ ከባድ ቢሆንም የኢትዮጵያ ቁልፍ ችግር መሆኑን ያስረዳሁበት፣ “የኢትዮጵያ ቁልፍ ችግር” የሚለውን መጽሐፌን አንብቡት እላለሁ፣ ዕውቀት አይናቅም፡፡ የኢትዮጵያ ቁልፍ ችግር ቋንቋ ነው አልኩ፡፡ ግን እንዴት? ለሚለው በትንሹ ልጀምር፡፡

ለምሳሌ ከቃላት አጠቃቀም ልጀምር፡፡ “ብሔር” የሚለውን ቃል ሳር ቅጠሉ ይጠቀምበታል፡፡ ግን መሠረታዊ ሐሳቡ አልተጨበጠም፡፡ “ብሔር” የሚለው ቃል ሰውን አያመለክትም፡፡ የሚያመለክተው መሬትን፣ ቦታን፣ ጠቅላላ ፍጥረትን ነው፡፡ ለምሳሌ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘ ብሔረ ቡልጋ በሚለው አነጋገር ውስጥ ተስፋ ገብረ ሥላሴ የተወልዱት ቡልጋ ተብላ በምትጠራበት ቦታ ነው ማለት ነው፡፡

“እግዚአብሔር” በሚለው ቃል ውስጥ ደግሞ ሁለት ቃላት አሉ፡፡ “እግዚእ” እና “ብሔር”፡፡ “እግዚእ” የሚለው ቃል “ጌታ”፣ “አምላክ” ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ “እግዚአ  ብሔር”  ማለት  የጠቅላላ ፍጥረታት ሁሉ ጌታ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል እንዲያመልክት የተደረገው ቀደምት ምሁራን እንዳሰቡት የእንግሊዝኛውን “Nation” የሚለውን አንድን ሉዓላዊ አገርን እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ፈረንሣይና ኢትዮጵያን የመሳሰሉ አገሮች ነው እንጂ አማራን፣ ኦሮሞን፣ ትግሬን፣ ወዘተ. ለማለት አይደለም፡፡ እኛማ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የአንድ ሉዓላዊ አገር ኢትዮጵያ ሕዝብ ነን፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች መናገሩ ኢትዮጵያዊነትንም፣ ኢትዮጵያዊነቱንም አይለውጠውም፡፡ ችግርም አይፈጥርበትምም፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአደሬ እስከ ዛይሴ (ከሀ አስከ ፐ) ድረስ ያሉትን ልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ሁሉም በእኩልነት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው፡፡ ቋንቋዎቹም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሀብት ናቸው፡፡ ዋናው ጉዳይ ያለው በአስተሳሰባችንና በልሳን አጠቃቀማችን ላይ ነው፡፡

ለምሳሌ እንደ ገና በቃላት አጠቃቀም ደረጃ “ልሒቃን” የሚለው የሁለተኛውም ቃል የአጠቃቀም ችግር አለበት፡፡ ቃሉ በግዕዝ “አዛውንት” ማለት ነው፡፡ ነጠላ ቁጥሩ “ልሒቅ” ነው፡፡ ስለዚህ የተፈለገውም መባል ያለበትም “ሊቃውንት” የሚለው ቃል ይመስለኛል፡፡

  “ሊቃውንት” የሚለው ቃል በጥንቱ ትምህርት የሚያመለክተው ድጓ፣ ፆመ ድጓ፣ ቅኔ፣ ዜማ፣ ትርጉምና ንባብ አዋቂዎችን ነው፡፡

እንግዲህ “ልሂቅ” በአሁኑ ጊዜ የሚያመላክተው ባለማወቅ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩትን (Educated Elites) የተባሉትን (ተብዬዎችን እንበላቸው?) ለማመልከት ይመስለኛል፡፡ ሊቃውንት ቢባሉ ትክክል ነው ብያለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት ቃላት በመገናኛ ብዙኃን ሲነገሩ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳባቸውን ስለሚለቁ፣ ከአሁን ጀምሮ ሊታረሙ ከቻሉ ትልቅ ዕርምጃ ነው እላለሁ፡፡

ዕውቀት ይከበር፣ ቃላት በቋንቋ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ቋንቋ ተግባሩ ወይም ሥራው ተጣርቶ ይታወቅ፡፡ የውጭውንም የአገሩንም የቋንቋ አዋቂዎችን እንጠቀምባቸው፡፡ ነጭ አምላኪ አንሁን፡፡ ሌላው ቃል “ጎሳ” የሚለው ነው፡፡ ቃሉ የሚያገለግለው ለኦሮሚኛ ተናጋሪዎችና ለሶማሌ ተናጋሪዎች (በአብዛኛው) ሲሆን፣ በሌሎችም ቋቋዎች ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ በኦሮሞ ጋለዪ፣ ሴቶ፣ ጉለሌ፣ ዱሌሌ፣ ወዘተ. ጎሳዎች ይኖራሉ፡፡ ለብዙ ዘመን ቀርተው ነበር፡፡ አሁን ሊመለሱ ያሰቡ ይመስላል፡፡ ይህ ቃል መተካት ያለበት “ነገድ“ በሚለው ቃል መሆን አለበት እላለሁ፡፡ ነገድ የሚለው ቃል ቀደም ሲልም ለምሳሌ ነገደ ዮቅጣን፣ ነገደ እስራኤል፣ ወዘተ.  እየተባለ ይሠራበት ነበር፡፡

ስለቃላት አጠቃቀም ሦስት ተጠቅሰዋል፣ ሌሎችም ብዙ አሉ፡፡ እነሱም በአዋቂዎች ይጠኑ፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ሙሉው የቋንቋ አጠቃቀም እንሂድ፡፡ አገራችን ውስጥ 75 ቋንቋዎች አሉ ተብሏል፡፡ ከዚህ ቁጥርም ሊበልጡ ይችላሉ፡፡ አሁን ጥያቄው 75ቱም ቋንቋዎች የኢትዮጵያ “ብሔራዊ ቋንቋ” ይሁኑ? የሚለው ነው፡፡ ይህም ማለት ‘ብሔራዊ’ የሚለው ቃል እዚህ ላይ ትርጉሙ አገር አቀፍ የመንግሥትን ሥራ በሙሉ እስከ ውጭ አገር መገናኛ ድረስ የሚሠራበት ማለት ነው፡፡ ግን መታወቅ ያለበት በቋንቋዎቻችን እንደ ፈለግን አድርገን ብንጠቀምባቸው ማን ያዘናል? ሥራችንን ለማቀላጠፍ እስከረዱን ድረስ፡፡

እዚህ ላይ በአስተሳሰብ ችግር ምክንያት አማርኛ የእኔ ቋንቋ አይደለም፣ ኦሮሚኛ የእኔ ቋንቋ አይደለም፣ ትግርኛ የእኔ ቋንቋ አይደለም በማለት 75ኑም ቋንቋዎች የእኛ አይደሉም እያልን ከካድን፣ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? እስቲ በሥርዓት አስቡበት፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያዊነትን በሥርዓት አለመረዳት ይመስለኛል፡፡

እዚህ ጣጣና ችግር ማጥ ውስጥ ገብተን ከመስጠምና አገሪቱንም እንዳትኖር ከማድረግ ይልቅ፣ በመጀመሪያ ደረጃ 75ቱንም ቋንቋዎች በአፍ መፍቻነት ተናጋሪዎቻቸው ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን በተግባር ያረጋግጡ፡፡ ለመድገም ያህል በሁለተኛ ደረጃ ስለቋንቋ ምንነት እንወቅ፡፡ ብዙ አዋቂዎች አሉ፡፡ የሥነ ልቦና፣ የታሪክ፣ የቋንቋ፣ የመልክዓ ምድር፣ የፍልስፍና፣ በሌሎችም መስኮች ጥናቶች የሚረዱ በውጭም በአገር በውስጥም አሉ፡፡ ምንድነው ችግሩ? ችግሩን በቃላት ውርወራ አንጂ በመድፍ ውርወራ ለመፍታት አንሞክር፡፡ ቀዝቃዛውም እሳቱም ጦርነት ይቁም እላለሁ፡፡ የሚሰማኝ ባገኝ፡፡

ይህ ጉዳይ ችግሩ ከ1983 ዓ.ም. ከተከሰተ በኋላ እየተቆለለ ስለመጣ ተንዶ ሁላችንንም ሳይቀብረን፣ በእኔ ሐሳብ ለዘላቂው መፍትሔ የመጀመሪያው ዕርምጃ ወደ 1983 ታሪካችን እንመለስና ያንን ሁሉ ቀውስ ያመጣውን የፓንዶራ ሳጥን ከፍቶ የለቀቀብን ነገር ምን እንደሆነ እንመርምርና ችግሩን እንረዳ እላለሁ፡፡

በአሁኑ ወቅት ችግራችን የመጀመሪያው ችግር በመጀመሪያ መታየት ያለበት አማርኛ ከአፄ ቴዎድሮስና ከዚያም በፊት ጀምሮ በአገራችን ትልቁን ሚና ስለተጫወተ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ምን ጉዳት አደረሰ? የሚለውን የቤት ሥራ መሥራት ነው እላለሁ፡፡ ይህ የቤት ሥራ ተሠርቶ ካለቀ ሌላው ቀላል ነው እላለሁ፡፡ ለማንኛውም በቋንቋ አጠቃቀም ላይ አተኩሬ ላጠቃል፡፡

አማርኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ይቀጥል፡፡ እንዲህ ከሆነ ኢትዮጵያ ታሪኳን ሳትለቅ እንደ ታወቀች ቦታውን ይዛ ከመስመሯ ሳትወጣ ትቀጥላለች፡፡ ሕዝቡን በቋንቋ ለያይተን በቋንቋ ተናጋሪው ብዛት የኢትዮጵያን መሬት ሸንሽነን ለእያንዳንዱ ቋንቋ ተናጋሪ እንደየድርሻው እንስጠው ብለን ብንነሳ፣ በድንበር ተጋጭተን እንተላለቃለን እንጂ ኢትዮጵያ ለማንም አትሆን እላለሁ፡፡

በመጨረሻ አሁን በ2015 ዓ.ም. ማጠናቀቂያ ላይ ኢትዮጵያ አገራችን ላለችበት ሁኔታ ቀላልና ቀናው መፍትሔ ምንድነው? ለመግቢያ ያህል አሁን በኢትዮጵያ ብሔር ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ቀላሉ መንገድ የሚከተሉትን ወሳኝ ዕርምጃዎች መውሰድ ነው እላለሁ፡፡

  1. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሉዓላዊት ኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ስለሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ አንዲሰማራ የተደረገው የጦር ሠራዊት አለ የሚባለው ነገር ስለሌለ፣ ይህን ሠራዊት በአስቸኳይ መልሶ በመከላከያ ጦር ሠፈሩ እንዲሰፍር ማድረግ ነው እላለሁ፡፡
  2. የኢትዮጵያ ፓርቲ እንጂ የነገድ ፓርቲ አለመሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፣ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለውን አዋጅ አውጆ፣ በነጋሪት ጋዜጣ አንዲወጣ ማድረግ ነው እላለሁ፡፡ አዋጁም አንደ ሚከተለው ይሁን እላለሁ፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የመከላከያ ሠራዊት የሚታጠቀውን ማናቸውንም የመሣሪያ ዓይነት በእጁ ላይ ከተገኘ በአስቸኳይ ለመከላከያ ሚኒስቴር መንግሥት በሚያወጣው መመርያ መሠረት አምጥቶ እንዲያስረክብ ይገደዳል፡፡

  1. ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ዕርምጃዎች ተወስደው ከተፈጸሙ በኋላ በሚቀጥለው ምርጫ ወቅት፣ ሕዝቡ የሚመርጠው ፓርቲ ሥልጣኑን እስከሚረከብ ድረስ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ሥራውን በነፃነትና በሰላም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል እንዲያከናውን እንዲችል መደረግ አለበት እላለሁ፡፡ ይህን ተግባር የሚያውክ በሕግ እንዲታገድ መደረግ አለበትም እላለሁ፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ዕርምጃዎች ያለ ማወላወል ተፈጻሚ ቢደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ተቀባይነት ይኖራቸዋል፡፡ እንዲያውም ሌላም ሽልማት ሊያስገኝላቸውም ይችላል እላለሁ፡፡

ነገር ግን አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የራሱ የሆነ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የማይመለከት የተለየ ዓላማ ኖሮት ከላይ የተጠቀሱትን ቀላል ዕርምጃዎች እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ በማሰብ ቸል ብሎ፣ አሁን የተያያዘውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ቢሞክር ሒደቱ የሚያስከትለውን ውጤት ከአሁኑ አስቀድሞ በሰከነ አዕምሮ ማመላለስ ይጠይቃል እላለሁ፡፡ ያለ መሸማቀቅ የተሰጠ ምክር ነውና አይጣልብኝ እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...