- በሌሊት ስለደወልኩኝ ይቅርታ፡፡
- ችግር የለውም ክቡር ሚኒስትር፣ ምን ልታዘዝ?
- አንድ የአውሮፓ ባለሥልጣን ነገ በጠዋት ወደ አዲስ አበባ ይገባል።
- እሺ።
- ሌሎች የመንግሥት አመራሮች ስላልቻሉ እርስዎ መንግሥትን ወክለው ቦሌ ኤርፖርት እንዲቀበሉት መወሰኑን ላሳውቅዎት ነው።
- ጥሩ፣ እንዳሉት አደርጋለሁ ክቡር ሚኒስትር።
- መልካም በሌሊት ስለረበሽኩዎት ይቅርታ፣ ጉብኝቱ እንደሚኖር ያሳወቁን በመጨረሻው ሰዓት ስለሆነ ነው።
- አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፣ ይልቅ እያየሁት የነበረው ህልምና የእርስዎ መደወል መገጣጠሙ አስገርሞኛል።
- እንዴት? ከህልም ነው የቀሰቀስክዎት?
- በእርግጥ ስልኩ ነው የቀሰቀሰኝ፣ የተገረምኩት ሳየው የነበረው ህልምና አሁን ያወሩኝ ነገር መገጣጠሙ ነው።
- እንዴት? በህልምዎ እንግዳ ሲቀበሉ ነበር?
- አይደለም።
- ታዲያ ምንድነው?
- አሁን ካለሁበት ፓርቲ ለቅቄ ገዥው ፓርቲን ስቀላቀልና ለሌላ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ስሾም እያየሁ ነበር።
- ታዲያ ምን አገናኘው?
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- እርስዎ ዘንድ የደወልኩት እኮ እንግዳ እንዲቀበሉ መወሰኑን ለመንገር ነው፡፡
- እሱንማ ሰምቻለሁ… እ… ግን እርስዎም ስለነበሩበት ልንገርዎት ብዬ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ምኑ ላይ ነው እኔ የነበርኩት?
- ህልሙ ላይ፡፡
- አስቸጋሪ ናችሁ።
- እነማን ክቡር ሚኒስትር?
- እናንተ ተቃዋሚዎች።
- እንዴት?
- ትንሽ ጊዜ በካቢኔ አባልነት ስትቆዩ ህልም ትወዳላችሁ።
- ምን ማለትዎ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ትረሱታላችሁ ለማለት ፈልጌ ነው።
- ምኑን?
- መቃወሙን።
- ተኝቼ ያየሁት ህልምና የእርስዎ የስልክ ጥሪ መገጣጠሙ አስገርሞኝ እንጂ እኔ ከፓርቲዬ ዓላማ ውጪ የመንቀሳቀስ ፍላጎቱ የለኝም፣ በተጨማሪም…
- በተጨማሪ ምን?
- የተቃዋሚ ፓርቲ አባልና አመራር ብሆንም በምክንያታዊ ተቃዋሚነት እንጂ በሌላ አላምንም።
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- ምን?
- በሌላ አላምን ያልከው?
- የ‹‹ዕብደት በኅብረት›› ፖለቲካ አራማጅ አይደለሁም ማለቴ ነው።
- ለማንኛውም በጥያቄ መልክ ይዤዋለሁ።
- ምኑን?
- ህልሙን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከግብፅ ድርድር መልስ ከምሁራንና ከተደራዳሪ ቡድኑ አባላት ጋር እየተወያዩ ነው]
- እንደሰማችሁት ተቋርጦ የነበረው ድርድር በአዲስ መልክ ሰሞኑን ተጀምሯል፣ እኛም በመጀመሪያው ዙር ድርድር ላይ ተሳትፈን ነው የተመለስነው።
- ክቡር ሚኒስትር ድርድሩ በአዲስ መልክ ከመጀመሩ በፊት እንደተለመደው በጉዳዩ ላይ ከሚመራመሩ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር ምክክር ተደርጎ የጋራ አቋም አለመያዙ ትክክል አልመሰለኝም፣ አብዛኞቻችንንም ሥጋት ውስጥ ከቶናል።
- እኛም ይህንን ስህተት ለማረም ነው የዛሬውን ምክክር የጠራነው፣ ውሳኔው አስቸኳይና ከመንግሥት የመጣ ስለነበር ምክክር ለማድረግ ጊዜ ባለማግኘታችን ነው፣ ይህንን እንድትረዱ እንፈልጋለን።
- ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን በጀመራችሁት አዲስ ድርድር ላይ በጋራ ያልመከርንበትና ከዚህ በፊት ያልነበረ አዲስ አቋም ይዛችሁ መቅረባችሁን የሚጠቁም ተባራሪ መረጃ መስማታችን እውነት ለመናገር በእጅጉ አስደንግጦናል፣ እውነት የሚባለው መረጃ ትክክል ነው?
- ምንድነው የሰማችሁት?
- ለአጭር ዓመታት የሚቆይ አሳሪ ስምምነት ለመፈረም በእኛ በኩል ፈቃደኝነት መንፀባረቁን ነው የሰማነው ክቡር ሚኒስትር፣ ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት ያልመከርንበትና ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፎ የሚሰጥ ነው።
- እርግጥ ነው የተባለውን ፈቃደኝነት አሳይተናል፣ ነገር ግን ይህንን ያደረግነው ከሌላኛው ወገን ልናገኝ የምንችለውን ምላሽ በማስላት ነው፣ ያገኘነውም ምላሽ እንዳሰብነው ነው።
- ክቡር ሚኒስትር ምን እንዳሰላችሁ ሊያስረዱን ይችላሉ?
- ለአጭር ዓመት የሚቆይ አሳሪ ስምምነት ላይ ለመድረስ ፈቃደኛ መሆናችንን በመግለጽ በተቃራኒው ወገን ላይ ዲፕሎማሲያዊ ግብ ማስቆጠር ነው፣ ይህንን ያደረግነው ደግሞ እንደማይቀበሉት ስለምናውቅ ነው።
- ቢቀበሉትስ?
- አንደኛ አይቀበሉትም።
- እሺ ሌላውስ?
- ሌላው ለአጭር ዓመት የሚቆይ አሳሪ ውል ለመፈራረም ፈቃደኛነት ብናሳይም፣ በሌላ በኩል ይህንን መቀበል እንዳይችሉ አድርገን አስረነዋል።
- እንዴት?
- አሳሪ ውሉ የሚፀናበት ጊዜ በማብቃቱ አስቀድሞ በተፋሰሱ አገሮች መካከል የተቀረፀው የውኃ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ማዕቀፍ ተጠናቆ ወደ ትግበራ መግባት እንዳለበት የሚገልጽ አሳሪ አንቀጽ እንዲገባ ጠይቀናል።
- ይህንን ባይቀበሉስ?
- ይህንን ካልተቀበሉ እኛም ወደ አሳሪ ውል አንገባም።
- ክቡር ሚኒስትር ሌላ አንቀጽ በመጨመር አሳሪ ውል ላለመግባት ያደረጋችሁት ጥረት የተፈጠረብንን ሥጋት ለጊዜው የሚቀርፍ ነው፣ ነገር ግን… የከፈትነው ቀዳዳ ጥሩ አይደለም።
- እንዴት?
- ለጊዜው የከፈትነውን ቀዳዳ ለመሸፈን የሞከርነው የተፋሰሱ አገሮች አቋም ከእኛ ጋር የሚስማማ እንደሆነ በመተማመን ነው፣ አይደለም?
- ልክ ነው።
- ነገር ግን እነዚህ አገሮች ከተፋሰሱ የሚያገኙት ጥቅም አነስተኛ በመሆኑ ከእኛ ጋር የሚስማማ አቋም ይዘው እስከ መጨረሻው ለመፅናታቸው መተማመኛ የለንም።
- እንዴት በአቋማቸው ሊፀኑ አይችሉም?
- ምክንያቱም ከተፋሰሱ ከሚያገኙት ጥቅም የገዘፈ የኢኮኖሚ ድጋፍ ከምዕራባውያኑ ቃል ከተገባላቸው በቀላሉ አቋማቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ፣ ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ደግሞ አይመችም።
- ምንድነው የማይመቸው?
- መውቀስም መቀልበስም!