Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጠበቆች ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ እንደሚገደዱ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ግብር ከፋይ የፌዴራል ጠበቆች ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ የሒሳብ መዝገብ ካልያዙ ግብር መክፈል እንደማይችሉና የሒሳብ መዝገብ መያዝ ግዴታ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተፈርሞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በወጣው ደብዳቤ መሠረት፣ የደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ግብር ከፋይ ጠበቆች የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ አለባቸው፡፡ እንዲሁም ጠበቆቹ የጥብቅና ገቢን ለማስገኘት፣ ለጥብቅና ሥራው ዋስትና ለማሰጠትና የጥብቅና ሥራውን ለማስቀጠል የሚኖሩባቸው ክፍያዎች በወጪነት እንዲያዙላቸው የሚል ውሳኔም ተሰጥቷል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የተሰጠው አዲስ አቅጣጫ መሠረት ብዙኃኑ የደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች በየዓመቱ የሚከፍሉት የግብር መጠን፣ ምናልባትም በአንድ ወይም በሁለት እጥፍ ሊጨምር እንደሚችል ሪፖርተር ያነጋገራቸው ጠበቃ ተናግረዋል፡፡

የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋይ ዓመታዊ ገቢ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይና የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋይ ከ500,000 እስከ አንድ ሚሊየን ብር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ አብዛኛውን የግብር አከፋፈል ችግር የሚያቃልል መመርያ አውጥቶ የታክስ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶቹ እንዲተገብሩት ማድረጉ ይታወሳል፡፡

 የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው መመርያ በጣም ዘግይቶ የወጣ በመሆኑና አብዛኞቹ የደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ግብር ከፋይ ጠበቃ የሒሳብ መዝገብ አስቀድሞ ያልያዘ በመሆኑ፣ ለከፍተኛ ችግር የተጋለጠ መሆኑን በመግለጽ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከፍትህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡

ከውይይቱ በኋላ የፍትሕ ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የወጣው የአፈጻጸም መመሪያ ሙሉ ለሙሉ ለ2016 በጀት ዓመት የግብር ዘመን ተፈጸሚ እንዲደረግ እና የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች ለ2015 የግብር ዘመን የሒሳብ መዝገብ ያልያዙ ግብር ከፋዮች በሚስተናገዱበት የቁርጥ ወጪ ሰንጠረዥ መሠረት እንዲስተናገዱ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ 

አብዛኛዎቹ የደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ግብር ከፋይ ጠበቆች፣ ቀድሞ በነበረው አሠራር ግዴታቸውን እየተወጡ የነበረው የሒሳብ መዝገብ መያዝ ሳይጠበቅባቸው ነበር፡፡

በዓመት በደረሰኝ ከሰበሰቡት ገቢ ውስጥ 75 በመቶ እንደ ወጪ የሚያዝና በሁለቱ ደረጃዎች የነበሩ ጠበቆች፣ በቀደመው አሠራር በዓመት በደረሰኝ ከሰበሰቡት ገቢ 25 በመቶ የተጣራ ትርፍ ላይ 35 በመቶ ብቻ ግብር እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር፡፡

በቀጣዩ የግብር ዘመን የጠበቆች ዓመታዊ ወጪ በእጅጉ ሊቀንስ ስለሚችል፣ የጠበቆቹ የተጣራ ትርፍ ምናልባትም ጠበቃው በዓመት በደረሰኝ ከሰበሰበው ገቢ እስከ 75 በመቶ ሊሆን እንደሚችል፣ ይኸውም ጠበቆች ግብር የሚከፍሉበትን የተጣራ ትርፍ መጠን በመጨመር የሕግ ሥራ ዕድገትን ሊያዳክም ይችላል ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ጠበቆች ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች