በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሳቢያ ከኢትዮጵያ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ የገቡት የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ማለትም ግብፅና ሱዳን፣ ‹‹ፍትሕ ቢኖር ኖሮ የህዳሴ ግድቡን የግንባታ ወጪ መጋራት ነበረባቸው፤›› ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር) በሳምንታዊ መግለጫቸው፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውጤት ሁሉንም አገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ አገሮቹ የግንባታ ወጪውን መጋራት እንደነበረባቸው ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን የሚጠቅመው ጉዳይ አገሮቹ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ተነጋግሮ መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ ማበጀት መሆኑን ጠቁመው፣ ግድቡ ግን መሬት ላይ ያለ እውነታ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም የህዳሴ ግድብ ሙሌት ሒደት በተቀመጠለት ጊዜ የሚከናወን መሆኑን፣ የሚያስፈልገው መፍትሔ ንግግር እንጂ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን አንድ ውኃ የሚጠጡ የዘመናት ትብብር ያላቸው ጎረቤት አገሮች በመሆናቸው፣ የህዳሴው ግድብ ጉዳይ መታየት ያለበት በዚያ መሠረት እንጂ፣ በየሚዲያው እየወጡ መወቃቀስ ለማንም አይጠቅምም ብለዋል፡፡
ስለሆነም ከካይሮ የሚቀርቡ ክሶች ለሦስቱም አገሮች የማይጠቅሙ በመሆናቸው መፍትሔው ተነጋግሮ መተማመን ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ኢትዮጵያ ከሱዳንም ሆነ ከግብፅ ጋር ያላት ግንኙነት ከህዳሴው ግድብ በላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የህዳሴ ግድብን ድርድር ሚዲያ ላይ ማውጣት የሚፈልጉ አካላት ቢኖሩም በኢትዮጵያ በኩል ያለው አቋም ግን በየሚዲያው ላይ በመውጣት አስተያየት መስጠት ሳይሆን፣ ለድርድር በተመረጠ ቦታ ከሚመለከተው አካል ጋር መነጋገርና መደራደር ነው ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ የህዳሴ ግድቡ በዓለም መድረኮች ብዙ የተወነጀለና ፖለቲካዊ ትርጉም የተሰጠው መሆኑን፣ ለኢትዮጵያውያን ግን መብራት፣ ምግብ፣ ተገቢ የትምህርትና የሕክምና አገልግሎት የማግኘት ህልም ያለውና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ መተባበር ብቸኛው አማራጭ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሦስቱ አገሮች በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው የማይስማሙበት ነገር ካለ የተሻለ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል ብለው፣ ከኢትዮጵያ በኩል ጉዳዩን የሚዲያ ፍላጎትን ለማሟላት (Megaphone Diplomacy) የማድረግ ሐሳብ የለም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የውኃውን ሙሌትና አለቃቀቅ በተመለከተ ከግብፅና ከሱዳን መንግሥታት ጋር እያደረገችው ባለው ድርድር፣ በግብፅ በኩል ድርድሩን በአደባባይ ለሚዲያ ክፍት ሆኖ እንዲካሄድ መኖሩ ከመንግሥት በኩል እየተነገረ ነው፡፡ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መገለጹ ይታወሳል፡፡