Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት 1.5 ሚሊዮን ፓስፖርቶችን ከፈረንሣይ ሊገዛ ነው

ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት 1.5 ሚሊዮን ፓስፖርቶችን ከፈረንሣይ ሊገዛ ነው

ቀን:

ከአንድ ወር በፊት የቀድሞዎቹ ተነስተው አዳዲስ ኃላፊዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙለት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ያጋጠመውን ‹‹የፓስፖርት ቀውስ›› ለመፍታት የ1.5 ሚሊዮን ፓስፖርቶች ግዥ ከፈረንሣይ ማዘዙን አስታወቀ፡፡

በባለፉት ስድስት ወራት ፓስፖርት የመስጠት ሥራ በመቋረጡ ከ300 ሺሕ በላይ የተጠራቀመ ጥያቄ ያለ ሲሆን፣ አዲሱ አስተዳደር በ2016 ዓ.ም. ለሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡

ከፈረንሣይ ከሚገዙ ፓስፖርቶች ወደ አገር ውስጥ 190 ሺሕ ፓስፖርቶች መግባታቸውን፣ በቅድሚያ አንገብጋቢ ለሆነባቸው ዜጎች መስጠት መጀመሩን ይፋ አደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት 16,712 ፓስፖርቶች በመካከለኛው ምሥራቅ ችግር ላይ ላሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እንዲደርስ መደረጉን፣ በተመሳሳይ ከ4,000 በላይ ፓስፖርቶች አፍሪካ አገሮች ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን መላኩ ተገልጿል፡፡

‹‹ፓስፖርት ማግኘት ስላልቻሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን በዓረብ አገሮች ከሥራቸው ተፈናቅለው ችግር ላይ ወድቀዋል፡፡ ለእነሱ ቅድሚያ የሰጠን ሲሆን፣ በቀጣይ ደግሞ አመልክተው ከስድስት ወራት በላይ ለሆኑት ቅድሚያ ሰጥተን ከዚያ ሁሉንም እናስተናግዳለን፤›› ሲሉ አዲስ የተሾሙት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፣ ከተሾሙ ወዲህ በ30 ቀናት ውስጥ ያከናወኑትን ሪፖርት ዓርብ ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ሲያቀርቡ ተናግረዋል፡፡

የተጠራቀመውን የፓስፖርት አገልግሎት ችግር በአጭር ጊዜ ለማቃለል ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ በየቀኑ እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት ድረስ ሠራተኞች አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መጀመሩን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡ የኦንላይን የፓስፖርት ቀጠሮ ያመለጣቸው ከእንግዲህ ቅዳሜ ቅዳሜ መገልገል እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡ እንደደረሱ ቪዛ (Visa on Arrival) አገልግሎትም ከመስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚሰጥ ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡ አገልግሎቱ የውጭ አገር ዜጎች ቪዛ ሳይዙ በአውሮፕላን ቲኬት ብቻ መጥተው አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ቪዛ የሚያገኙበት ሥርዓት ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በደኅንነት ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ እንዳሉት፣ የዚህ አገልግሎት መቋረጥ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከባድ ጉዳት አስከትሏል፡፡

አዲስ የተሾሙት ዋና ዳይሬክተር የፓርላማ አባልና ቀደም ብሎ የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ የነበሩ ሲሆን፣ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች አውጥተው እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ በራሱ ሠራተኞችና በውጭ ህቡዕ የሙስና መረቦች ተተብትቦ ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ የሌብነትና የብልሹ አሠራር ዘገባዎች ምሳሌ ሆኖ ቆይቷል ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹ሠራተኞች ዶክመንት ሰርቀው ያወጣሉ፡፡ ከውጭ ደግሞ የውሸት ፓስፖርት ተቀብለው የሚሸጡ ደላሎች አሉ፡፡ ይህ የሌብነት መብ ለአገራዊ ደኅንነትም ሥጋት ደቅኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ የሙስና መረብ ውስጥ የሚሳተፉትን በሙሉ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ዝርዝራቸውን ሰጥተናል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከላይ ያሉትን ኃላፊዎች ብቻ በመለወጥ ተቋሙን መለወጥ አይቻልም፡፡ እስከ ታች ድረስ መለወጥ አለበት፡፡ ችግሮቹን በሙሉ ለይተናል፡፡ በአንዴ ለመፍታት ግን ከባድ ነው፡፡ መጥፎ ሠራተኞች የመኖራቸውን ያህል ቀን ከሌሊት የሚሠሩ ሠራተኞችም አሉ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሌላው ተቋሙ ተደቅኖበት የነበረው አደጋ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መሆኑን፣ ችግሩን በመገንዘብ መንግሥት መፍቀድ መጀመሩን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ አሁንም እየተፈጸሙ ካሉት ውስብስብ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች መጠንቀቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የተቋሙን በይነ መረብ አስመስለው በመሥራት ጭምር የኦንላይን ምዝገባ እያደረጉ ገንዘብ የሚቀበሉ እንዳሉ ይታወቃል ብለዋል፡፡ የተቋሙ ሠራተኞች በዜጎች ላይ ያደርሳሉ የተባሉትን ማመናጨቅ በተመለከተ፣ ለሠራተኞቹ የተሻለ ደመወዝ በመክፈልና የሥራ ከባቢ ሁኔታውን በማሻሻል ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...