Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትዓመቱ በስፖርት

ዓመቱ በስፖርት

ቀን:

በኢትዮጵያ የ2015 የውድድር ዓመት በርካታ ስፖርታዊ ክንውኖችን ተስተናግደዋል፡፡ በአገር ውስጥ ከተከናወኑት ባሻገር በአኅጉርና በዓለም አቀፍ መድረኮች በተዘጋጁ የስፖርት ውድድሮች ኢትዮጵያ መካፈል ችላለች፡፡ በአገር ውስጥ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ይጠቀሳሉ፡፡

ዓመቱ በስፖርት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ያነሳው ቅዱስ ጊዮርጊ

የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮችን በተለያዩ ከተሞች ሲያከናውን የቆየው የሊጉ አክሲዮን ማኅበር፣ የመጫወቻ ሜዳ ዕጦት መፈተኑና ክለቦች በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ለተጫዋቾች ደመወዝ መክፈል ያልቻሉበት ዓመትም ነበር፡፡

በሌላ በኩል ለአይቮሪኮስቱ የ2024 አፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በምድብ አራት ከግብፅ፣ ጊኒና ማላዊ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ከምድቡ አለማለፉና በአንፃሩ በምድብ የመጀመሪያው ጨዋታ ግብፅን ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ የዋሊያዎቹ ከምድባቸው አለማለፋቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን ከአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር የነበረውን ውል አቋርጧል፡፡

አሠልጣኝ ውበቱ ዋሊያዎቹን ከተረከበ በኋላ አጠቃላይ 35 ጨዋታዎችን ማድረግ የቻለ ሲሆን፣ አሥሩ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ናቸው፡፡ ዋሊያዎቹ ካደረጉት መደበኛ 25 ጨዋታዎች ስድስቱን ብቻ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ከአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ዋሊያዎቹን ለማሠልጠን ኃላፊነት የተረከበው አሠልጣኝ ውበቱ፣ ምንም እንኳ ወደ 2022 የሞሮኮ የቻን ውድድር ማለፍ ቢችልም፣ ውጤታማ ጊዜ ማሳለፍ ሳይችሉ ቀርቷል፡፡

ለብሔራዊ ቡድኑ ደካማ ውጤት ማምጣት የተለያዩ ጉዳዮች ሲነሱ የሰነበቱ ሲሆን፣ ወጥ የሆነ ቡድን መገንባት አለመቻሉና ብሔራዊ ቡድኑ በስታዲየም እጦት ምክንያት የሜዳ ጨዋታውን በአገር ውስጥ ማድረግ አለመቻሉ ተነስቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ የካፍ ዕውቅና ያገኘ ስታዲየም ባለመኖሩ፣ ብሔራዊ ቡድኑ የምድብ ጨዋታውን በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ማድረጉ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩ በተደጋጋሚ እንደ ምክንያት ሲነሳ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ተሳትፎ

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የአትሌቲክስ ተሳትፎ የምታደርገው ኢትዮጵያ፣ በ19ኛው የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ቡድኗ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በ2022 የኦሪጎን አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጥሩ ውጤት ያመጣው ቡድኑ፣ በዘንድሮም የተሻለ ውጤት ያመጣል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቡድኑ ሁለት የወርቅ፣ አራት የብርና ሦስት የነሐስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡

በዓለም ሻምፒዮናው ቡድኑ ውጤት ማምጣት ላለመቻሉ የተለያዩ ምክንያቶች ቀርበዋል፡፡ በተለይ በቡዳፔስት የነበረው የአየር ሁኔታና አትሌቶች በቡድን መሥራት አለመቻላቸው በዋነኛነት ተጠቅስዋል፡፡ ሌላኛው በሻምፒዮናው የአትሌቶች ምርጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያስተላለፈው ውሳኔ ከፍተኛ ውዝግብ መፍጠሩ ወደ ቡዳፔስት ያመራው አትሌቲክስ ቡድን ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ 

ይህም ውጤቱ ከቡድኑ ዝግጅት ጋር ሲተያይ የተጠበቀውን መሆን ሳይችል ቀርቷል፡፡ ሌላኛው በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ የልምምድ ቦታ መጥፋቱ፣ አትሌቶች በተገቢው መንገድ ልምምዳቸውን እንዳያከናውኑ ሲፈትናቸው ቆይተዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም. የሚካሄዱ ውድድሮችና የኢትዮጵያ ተሳትፎ

በ2015 (2022/23) የውድድር ዘመን ስኬታማ ጊዜ ማሳለፍ ያልቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ከኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በኋላ በተለያዩ አኅጉር ዓለም አቀፍ ውድድሮች ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በጊዜያዊ አሠልጣኝ እየተመራ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ፣ አዲስ አሠልጣኝ ያገኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በኢትዮጵያ የካፍ ዕውቅና ያላገኙ ስታዲየሞች ባለመኖራቸው የሌላ አገር ስታዲየሞችን የሚጠቀመው ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታዎችን በአገር ውስጥ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 በጥር 2016 የአፍሪካ ዋንጫ በአይቨሪኮስት ሲከናወን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባይካፈልም፣ የአፍሪካ ዋንጫው በአብዛኛው እግር ኳስ አፍቃሪ በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንዴት አለፈ?

የ2015 ዓ.ም. የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በርካታ ክስተቶችን አስተናግዶ አልፏል፡፡ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ አዳማና ሐዋሳ ከተሞች የሊጉን ውድድር ሲያስተናግዱ ቆይተዋል፡፡ በአንፃሩ የመጫወቻ ሜዳዎች በዝናብ ምክንያት እየጨቀዩ፣ የሊጉ አክሲዮን ማኅበር በሜዳ ችግር ሲፈተን ቆይቷል፡፡ ከዚሀም በላይ ክለቦች በተለያዩ ከተሞች ተዘዋውረው ውድድር ማድረግ ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋቸው እንደሆነ ሲያነሱ ነበር፡፡ አንዳንድ ክለቦች በሆቴል ውዝፍ ዕዳ ኖሮባቸው፣ የሰርቪስ ተሽከርካሪዎቻቸው የተያዙባቸው ነበሩ፡፡

ከፍተኛ ፉክክር በታየበት የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ (ፈረሰኞቹ) ከባህር ዳር ከተማ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ያለፈበት የውድድር ዘመን ነበር፡፡ ሆኖም ፈረሰኞቹ ለ16ኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ወደ ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ማለፍ የቻለው ለገጣፎ ለገዳዲ በመጣበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርዷል፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክና አርባ ምንጭ ከተማ ከሊጉ የወረዱ ክለቦችም ናቸው፡፡

በምትካቸው ሻሸመኔ ከተማ፣ ሃምበሪቾና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ሊጉ ማደግ ችለዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዳዲስ ጉዳዮችን አካቶ ይከናወናል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከቤቲኪንግ ጋር የነበረውን የስያሜ (ታይትል) ስፖንሰርሺፕ ስምምንት አቋርጦ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አዲስ ውል ማሰሩ ተሰምቷል፡፡ 16 ክለቦች የሚሳተፉበት የሊጉ ውድድር ቀድሞ ሦስት ክለቦች ወርደው፣ ሦስት ክለቦች የሚያድጉ ሲሆን፣ በዘንድሮ ውድድር ግን ሁለት ክለቦች ብቻ ወደ ሊጉ እንደሚያድጉ አክሲዮን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ከሦስት ዓመት በላይ በአዲስ አበባ ሳይከናወን የቆየው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ፣ ዘንድሮ በአዲስ አበባ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታ ሒደት እየተጠናቀቀ መምጣቱን ተከትሎ፣ የ2016 የሊጉ ውድድር በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ለአክሲዮን ማኅበሩ ገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሳይመለከቱ ለዓመታት የቆዩት የአዲስ አበባ ተመልካቾች በካምቦሎጆ እንደገና የመሰብሰብ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡

ከዲኤስቲቪ ጋር ለአምስት ዓመታት ውል ያሠረው የአክሲዮን ማኅበሩ ጨዋታዎችን በቀጥታ ማስተላለፍ መቻሉ እንደ ስኬት የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ በ2016 ዓ.ም. መርሐ ግብርም የሊጉን ጨዋታዎች በቀጥታ የሚያስተላልፍ ይሆናል፡፡

የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታ

በሚቀጥለው ዓመት የሚከናወነው የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ይጠበቃል፡፡ ከየትኛውም የስፖርት ውድድር ቅድሚያ የሚሰጠው የኦሊምፒክ ጨዋታ፣ ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በፈረንሣይ ዋና ከተማ በፓሪስ ይከናወናል፡፡ ከ206 በላይ አገሮች በሚካፈሉበት የፓሪስ ኦሊምፒክ 10,500 አትሌቶች፣ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1956 ጀምሮ በኦሊምፒክ መሳተፍ የጀመረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን፣ ከቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮን በኋላ በፈረንሣይ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡

በዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና የተሻለ ውጤት ማምጣት ያልቻለው የአትሌቲክስ ቡድን፣ ከኦሊምፒክ ጨዋታው ስድስት ወር አስቀድሞ፣ ለመዘጋጀት ማቀዱ ተገልጿል፡፡ አትሌቶችም በዓለም ሻምፒዮናው ማሳካት ያልቻሉትን ውጤት በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመካስ ቃል ገብተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...