Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንመራረቅ!

ሰላም! ሰላም! አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሊተካ ዋዜማ ላይ ነን፡፡ እነሆ እዚህ ላደረሰን ፈጣሪ ምሥጋና ይድረሰው። ስንቱን ውጥረትና ክፉ ነገር አልፈን እንዳንል ገና የለየለት ነገር ባለመኖሩ፣ አሁንም ፈጣሪ ይመሥገን በማለት እንኳን አደረሳችሁ እያልኩ አዲሱን ዓመት በተስፋ እንቀበል ዘንድ መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ። እንግዲህ ምን ያህሎቻችን ተቀይረናል? ምን ያህሎቻችን ተቀያይሮብናል? የሚለውን ቤት ይቁጠረው። የበዓል ዋዜማም አይደል ማንጠግቦሽ እንደ ነገሩ ቤቱን ሞቅ ሞቅ ለማድረግ ደፋ ቀና ስትል አያታለሁ። በምናብ በዓል መስሎኝ ‹ቡና ቀራርቧል። ዳቦ ተዘጋጅቷል፡፡ መብራት የለም። ጠላ ቀርቧል፡፡ ውኃ ሄዳለች› እያልኩም የተነገ ወዲያውን በዓል ውሎ እቃኛለሁ። ‹‹በተገኘው መጠቀም ነው ይኼንንስ ማን አየብን?››› ትለኛለች በዓሉን ከወዲሁ በሥጋት ለመቀበል ወዲያና ወዲህ የምትለው ውዷ ባለቤቴ። እኔ ደግሞ በዚህ ሰዓት ምንም የሌላቸውን፣ አግኝተው ያጡትንና የተቸገሩትን አስባለሁ። በአገር ላይ የደረሰውን መከራ እያሰብኩም እተክዛለሁ፡፡ በሌላ በኩል ጉቦ ካላመጣችሁ፣ ጥቅማ ጥቅም ካላቀረባችሁ፣ ተራራውን ሜዳ ሸለቆውን አቀበት ካላደረጋችሁ እያሉ ወገኔን ቀንበር የሚጭኑበትን አስባለሁ። ይህ ሁሉ እየታሰበ ለአዲስ ዓመት አቀባበል ሽር ጉድ ይባላል፡፡ ወግ ነውና!

ታዲያ ከማሰብ ሌላ ምን ተረፈን? ሐሳብ ገንዘብ ቢሆን ኖሮ ይኼኔ በደካማ የቁጠባ ባህላችን ባልታማን ነበር፣ እውነቴን እኮ ነው። ዳሩ በዚህ ዘመን በአደላቸው አገሮች (የታደለም ቢሆን ሠርቶ ነው) ችግር የሆነው የሐሳብ እጥረት ሆኗል ይላሉ። ይኼው ለአንድ ወሳኝ ቢዝነስ ከአንድ ወዳጄ ጋር አውሮፓ ድረስ መለስ ቀለስ ማለት ጀምሬላችሁ ብዙ ነገር ታዝቤ ነበር። ጊዜና ዕድሉን ለጠበቀ የበረሃ ብቻ ሳይሆን የውኃም መንገድ አለ። ምን ታዘብክ ብትሉኝ? እዚያ ሁሉ ነገር ሞልቶ ሐሳብ አጥሯል። ሐሳብ ከማጠሩ የተነሳ ሲገኝ በገንዘብ ይተመናል። የሐሳብ ባንክም ደህና ጆሮም አላቸው። ሰምቼ ሳይሆን ዓይቼ ነው የማወራችሁ። መንገድ እንግዲህ የማያሳየን የለም፡፡ ዘንድሮ በዓይናቸው ሳያዩ በጆሮ ብቻ እየሰሙ የሚናገሩ በዝተዋልና አደራ ጠንቀቅ በሉ። ‹‹በል ተነሳ እንጂ የቅርጫ ሥጋ ከፍለህ ና…›› ፈረንጅ አገር ደርሼ መጣሁ ብለህ ባህሉን ልተወው ነው?›› ትለኛለች ማንጠግቦሽ። እግዜር ይስጣት ማንጠግቦሽ የእኩልነት አስተሳሰቧ ምኅዳር ሰፊ ነው። ከመስፋቱ የተነሳ አንዳንዴ ጨቋኝ ባል እያስመሰለችኝ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ አማክረው ነበር። እሱም፣ ‹‹ፈጣሪ መርቆ ሰጥቶሃል እጅ ነስተህ ኑር…›› ብሎኝ ዝም ይላል። እውነቱን ነው!

ከዘመናት የምድር ቆይታዬ በኋላ እንዳልኳችሁ መንገዱን ጨርቅ አድርጎልኝ አውሮፓን በጨረፍታ ስቃኝ፣ የበግ ግዥና የቅርጫ ሥጋ ነገር ፈፅሞ እንደማይታወቅ አየሁ። ሁሉም የፈረደበት ሱፐር ማርኬትና ሞል ውስጥ ነው ፍሪጅ ውስጥ ታጭቀው ያሉት፡፡ በዚህ በኩል እንኳን እኛ የምንሻል መሰለኝ፡፡ በዓላችን እንደ ጥንቱ ወጋችን የኩበቱ፣ የከብቱ፣ የበጉና የፍየሉ ሽታና ውካታ ስላለበት ንፍቅ ይላል፡፡ እዚያ ግን በራሳቸው ዛቢያ ላይ ብቻ እየተሽከረከሩ ካለመነካካት ጥጋቸው፣ ካለመደራረስ ችሎታቸው፣ ከመከባበርና ከሥልጣኔያቸው ብዛት እያንዳንዱ ሰው በራሱና በኑሮው ዙሪያ የሚሽከረከር ፕላኔት ሆኗል። እናም የማንጠግቦሽን የቅርጫ ሥጋ ሒሳብ መክፈል ትዕዛዝ ስጠብቅ በመብት የተቃኘና በፍቅር የተቃኘ እኩልነት ለውጡ ኩልል ብሎ ታየኝ። ብቻ በዓል በመጣ ቁጥር ድንቅ የሚለኝ ወጋችንና ባህላችን ነው፡፡ በደህናው ጊዜ ሰላም የማይባባለው ሳይቀር፣ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ…›› ሲባባል ከማየት የበለጠ ፈውስ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህንን ደስ የሚል ባህል ለወትሮው ኑሮአችን ጭምር ብንጠቀምበት ኖሮ አገራችን ኢትዮጵያ የበረከት ምድር ትሆንልን ነበር፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሰፊው ሕዝብማ በአዘቦቱም እኮ እንዲህ ተዋዶና ተደጋግፎ ነው የሚኖረው፡፡ ተምረናል የሚሉት ጀብራሬዎች ናቸው እኮ የሞራል ልሽቀት ውስጥ ሆነው አገር የሚያስቸግሩት…›› ይለኛል፡፡ ይህም አይካድም!

ዘመንና ቁጥር ታሪክ ተናጋሪውን አድማጭ፣ አድማጩን ተናጋሪ ማድረጉ ሳያንስ ቁልቁልና ሽቅብ እያስተያየን ሄዶ የሚመጣው መስከረም ራሱ መቼ ይታክት ይሆን እያልኩ ተነስቼ፣ የመዋጮ ሥጋ ክፍያ ወደ የሚሰበስቡት የተከበሩ አዛውንት ቤት ሄድኩ፡፡ እናላችሁ ይኼው አዲስ አበባን ጨርሼ ዓለም ማዳረስ የጀመርኩበት ሥራዬ ገና በእንጥልጥል ቢሆንም ከአጀማመሩ አጥጋቢ ይመስላል። ደንበኛዬ እዚህ አገር ጭኖ አምጥቶ መሸጥ የፈለገው ማሽን አየር ላይ ጣጣው በማለቁ ኮሚሽኔ እጄ ገብቷል። ‹‹አንበርብር ብር አላዋጣው ብሎ በዩሮ ማሰብ ጀምሯል ይሉሃል..›› ሲሉኝ ነበር አዛውንቱ ባሻዬ። ምቀኛ አታሳጣኝ ብዬ እኔም አደብ ገዝቼላችኋለሁ። እንኳን ለደላላ ለተደላይ አደብ መግዛት ጭንቅ በሆነበት ጊዜ አደብ መግዛቴን በበኩሌ ዱባይ መሬት ከመግዛት ለይቼ አላየውም፣ የምሬን ነው። ይኼን አስቤ ለብቻዬ ፈገግ አልኩ። በዚህ ጨፍጋጋ ዘመን አንዳንዴ ፈገግ ማለት መልካም መሆኑን አዋቂ ነን ባዮች ሲናገሩ እሰማለሁ፡፡ የፊት ጡንቻ በፈገግታ ወጠርና ፈታ ሲል ከድብርት ያላቅቅ እንደሆነ ግን እስካሁን አልሰማሁም፡፡ የመዋጮ ሥጋ ሒሳቤን ከፍዬ ወደ ሥራዬ ላቀና መራመድ ስጀምር፣ ‹‹አቶ አንበርብር ምንተስኖት አውሮፓ እንዴት ነበር እባክህ…›› የሚል አሽሙር ያዘለ ሳቅ ያለበት ድምፅ ሰማሁ፡፡ ዞር ብዬ ሳይ ለካ አንዱ ሥራ ፈቶ ድንጋይ ሲያሞቅ የሚውል ተረበኛ ነው፡፡ ‹‹አውሮፓማ ድንጋዩን ለልማት ተጠቅመውበት መቀመጫ አጥቼ ቶሎ መጣሁ እኮ…›› ስለው በመጣበት እግሩ ሸብለል ብሎ ተመለሰ፡፡ ወሬኛ ለካፊ!

የአዲስ ዓመት ዋዜማም አይደል ድንገት ሥራ ጠብ ቢልልኝ ብዬ ስልኬን በእጄ ይዤ ስራመድ ወዲያው ጮኸ፡፡ አንስቼ ገና፣ ‹‹ሃሎ ማን ልበል…›› ከማለቴ፣ ‹‹አንበርብር አንተን አይደለም እንዴ በእግር በፈረስ የምፈልገው…›› እያለ አንዱ እንደ መትረየስ ተንጣጣብኝ፡፡ በፍጥነት ራስ ሆቴል እንድመጣ ቀጥሮኝ ስልኩን ዘጋው፡፡ እኔም ጊዜ አላጠፋሁ ራይድ ይዤ ተፈተለኩ፡፡ ራስ ሆቴል በራፍ ላይ ወርጄ በረንዳው ላይ ከመድረሴ፣ ‹‹አቶ አንበርብር ወዲህ ና…›› የሚል ድምፅ ሰምቼ ወደ ቀኝ ዞር ስል፣ አንድ መልከ ቀና ጎልማሳ የበፊት ደንበኛዬ ከሦስት ልዕልት ከመሳሰሉ ቆንጆዎች ጋር ተቀምጦ በእጁ ምልክት ሰጠኝ፡፡ እኔ ድንገት ባየሁት ወደር የሌለው የወይዛዝርቱ ቁንጅና እየተደመምኩ ደርሼ ሰላምታ ስሰጥ ፈዝዤ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ከወይዛዝርቱ ልብስ ላይ ወደ አፍንጫዬ የሚተመው የውድ ሽቶዎች መዓዛ ልብ ያጠፋል፡፡ ወንበር ተጋብዤ ምን እንደምጠጣ ስጠየቅ ቀልቤ ከእኔ ጋር አልነበረም ብላችሁ አታምኑኝም፡፡ ይህንን ሁኔታዬን ውዴ ማንጠግቦሽ ብታይ ኖሮ የጋብቻችን ሰማኒያ የሚቀደደው ራስ ሆቴል በረንዳ ላይ ይሆን ነበር፡፡ ወይ ውበት እንዲህ አጠናግሮ አቅሌን ያስተኝ ወይ? አደራ ያጋጥማል እንዳትሉኝ!

በዓመቱ መጨረሻ ላይ የገጠመኝ ልክፍት በተጋበዝኩት ጥቁር ማኪያቶ ለጊዜው ገለል ባይልልኝ ኖሮ፣ ደንበኛዬ ራሱ ወዲያውኑ የፈለገኝን ምክንያት ሰርዞ በቀይ ካርድ ያባርረኝ ነበር፡፡ ግና በዓመት አንዴ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ሲያጋጥም ‹‹ለበጎ ነው›› ብሎ ማለፍ መልካም እንደሆነ የነገረኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ደንበኛዬ ለእነዚህ ውብ ልዕልቶች አዲስ ሥራ መጀመሪያ ቦሌ ውስጥ አንደኛ ደረጃ ከሚባሉ ሕንፃዎች በአንዱ አሪፍ ሰፊ የቢዝነስ ቢሮ እንዳፈላልግ ትዕዛዝ ሰጥቶኝ፣ ከወዲሁ ለበዓል እንደ ስጦታ ይሁንህ ብሎ ሁለት የታሸጉ ባለሁለት መቶ ብር እስሮች ሲሸጉጥልኝ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ከውቦቹ አንዷ ደግሞ ከቦርሳዋ ውስጥ አውጥታ፣ ‹‹ይህ ደግሞ የእኛ ስጦታ ነው…›› ብላ ተመሳሳዩን እጄ ላይ አስቀምጣ ጀርባዬን ቸብ ቸብ ስታደርገው ሰማዩና ምድሩ ዞረብኝ፡፡ ለምሥጋና የሚሆኑ ቃላትን ለመቀመር ስታገል ሰላምታ ሰጥተውኝ በችኮላ እየሳቁ ወደ ውዶቹ መኪኖቻቸው ሲያቀኑ እንደ ሕልም ነበር የሚታየኝ፡፡ ጎበዝ ለሰጪ የሚሰጠው አይጣ እያልኩ በልቤ፣ ፈጣሪ ካሰጠኝ በረከት ላይ ደግሞ ለምስኪኖች የሚሰጠው ምን ያህል እንደሚሆን ከውዷ ባለቤቴ ጋር ለመማከር ወደ ቤቴ በረርኩ፡፡ እንዲያ ነው መሆን ያለበት!

በሉ እንሰነባበት። ዘመን እንደሆነ ያሰነባብታል እንጂ አይሰናበትም። ቋሚና አላፊም ቢሰነባበቱ አይታክቱም። ቸር ተመኝተን በቸርነቱም እዚህ ደረስን። አሥራ አምስትን ሽረን አሥራ ስድስት ለማለት ደረስን። ይኼን ጊዜ ነው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹እንግዲህ ከቁጥር ራስ ላይ ተነስተን የራሳችን ጉዳዮች፣ ጥንካሬዎች፣ ድክመቶች፣ ጥረቶች፣ ስንፍናዎች፣ መልካምነቶች፣ ክፋቶች፣ ድፍረቶች፣ ፍርኃቶችና ሌሎች ተቆጥረው የማያልቁ አባዜዎቻችንን መመርመር ይጠበቅብናል፡፡ አዲሱን ዓመት ስንቀበል ከሱስ ለመላቀቅ፣ የተሻለ ሥራ ለማግኘት ወይም ለመክፈት፣ ትዳር ለመያዝ፣ በቂ ቁጠባ ለማድረግ፣ ወዘተ. ከምንገባቸው ቃላት በላይ አገራችንንና ሕዝባችንን የሚበድሉ ክፉ ድርጊቶችን መተው፣ በሐሰትና በአሉባልታ አለመተማማት፣ መልካም ንግግርን በመግፋት መተላለቅን ማስቀረት፣ ያለ አድልኦ ሁሉንም ማገልገል፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ ጠበቃ መሆን፣ ከጎሰኝነትና ከአክራሪነት አስተሳሰቦች መላቀቅ፣ ለሰብዓዊነትና ለርኅራኄ ልብን ክፍት ማድረግ ካልቻልን ዓመት ተለወጠ አልተለወጠ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ወዳጄ መጪው አዲስ ዓመት ከምንሸኘው ካልተለየ በጉጉት መጠበቁ ምንም አይፈይድም…›› ብሎኝ ነበር፡፡ አይደለም እንዴ!

አዛውንቱ ባሻዬ ደግሞ፣ ‹‹አበባ አየሽ ወይ ለምለም…›› እያሉ ልጃገረዶቹ በከፍተኛ ተስፋ የሚያቀነቅኑለት በዓል… ባልንጀሮቼ ግቡ በተራ እንጨት ሰብሬ ቤት እስክሠራ… የሚሉት ዓላማ የሕይወት ውሉና ግቡ እየተምታታበት፣ አገሩን ትቶ ወደ ሰው አገር የሚሰደድ ጥገኛ ትውልድ ማፍራቱን አንተም አትስተውም። ‹እንጨት ሰብሬ› ያሉት ማንም ተነስቶ ለገዛ ጥቅሙና ዓላማው የሚማግዳቸው እንደ እንጨት የሚሰበሩ ዜጎች ተኩ። ‹ቤት እስክሠራ› ያሉት ይኼው እስከ ዛሬ የእናት የአባቶቹን ቤት የመሥራት ሕልም ያላሳካ ትውልድ ተፈጥሮ፣ በዓይናቸው እያዩ የእርጅና ዘመናቸውን በፀፀት አገባደው አለፉ። በአጠቃላይ ‹አደይና የብር ሙዳይ› እንደ መስቀል ወፍ በዓመት አንዴ የሚዘፈኑ እንጂ የሚጨበጡ አልሆነም። ይኼም የዕድገቱ ውጤት ይሆናል ብለን እንገምት፣ እስኪ የከርሞ ሰው ይበለን፡፡ ምናልባት እየተፈራረቀ ቢለዋወጥ የማይታክተው ዓመትን ትተን፣ ራስን ለመለወጥ ራሳችን ላይ ተግተን እንገናኝ ይሆናል። ውጥረቱን አላልተን፣ ኩርፊያውንና ንትርኩን ትተን፣ በአንድነት የጋራ መሶቡን የምንቋደስበት ዓመት ይሆንልን ዘንድ እየተመኘን አዲሱን ዓመት ብንቀበልስ?›› ነበር ያሉኝ፡፡ በአዲሱ ዓመት መልካም ምኞት መለዋወጥ እንጂ አንገት ደፍቶ መቆዘም ተገቢ አይደለም ነው የአዛውንቱ ባሻዬ መልዕክታቸው፡፡  ስለዚህ እንመራረቅ! መልካም አዲስ ዓመት! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት