በርካታ አፍሪካውያን ወጣቶች በአገራቸው ዴሞክራሲያዊ አሠራር እንዲሰፍን ቢፈልጉም፣ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትን የሚመርጡ መኖራቸውን ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው የ‹‹2022 አፍሪካን ዩዝ ሰርቬይ›› አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ጋቦን፣ ጋናና ኬንያን ጨምሮ በ16 አገሮች ከ18-24 የዕድሜ ክልል ለሚገኙ 4507 ወጣቶች የገጽ ለገጽ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሲሆን፣ 74 በመቶ ወጣት አፍሪካውያን የትኛውም መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ቢመጣ እንደሚመርጡ ገልጸዋል፡፡ 39 በመቶው ደግሞ የምዕራባውያን ዴሞክራሲ ዓይነት ሳይሆን አፍሪካዊ መሠረት ያለው ዴሞክራሲ እንዲመጣ የሚመኙ ናቸው፡፡
በጥናቱ ከተሳተፉት 22 በመቶ ያህል ወጣቶች፣ የመከላከያ ሠራዊት አገራቸውን ቢያስተዳድር ይደግፋሉ፡፡ አገራቸው በወታደራዊ አገዛዝ ሥር እንዲሆን ከሚፈልጉት 37 በመቶ የሱዳን፣ 33 በመቶ የጋቦንና 32 በመቶ የጋና ወጣቶች በመሆን ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡
እንደ ሪፖርቱ፣ በርካታ አፍሪካውያን ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ መጀመር የሚፈልጉ ቢሆንም፣ በቂ ገንዘብ የማግኘትና ለኢንተርኔት የመክፈል አቅም የላቸውም፡፡ በአፍሪካ አኅጉር ያላቸው ተስፋም የተመናመነ ነው፡፡
እንደ ሪፖርቱ፣ በርካቶች ለሥራና ለትምህርት ውጭ መሄድ ይመኛሉ፡፡ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ግማሽ ያህሉም፣ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ሌላ አገር ለመሄድ እያሰቡ ናቸው፡፡
ወጣቶች ለአገራቸው ያላቸው አዎንታዊ አመለካከት እየቀነሰ ቢሆንም፣ ለራሳቸው የወደፊት ሕይወት አዎንታዊ ምልከታ አላቸው፡፡
አፍሪካውያን ወጣቶች ዴሞክራሲ በየአገራቸው ሰፍኖ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ በሁሉም ሕዝቦች መካከል እኩልነት እንዲሰፍን፣ የመናገር መብት እንዲከበርና ነፃና ገለልተኛ ምርጫ እንዲከናወን የሚናፍቁም ናቸው፡፡
የአየር ንብረት ለውጥም እንደሚያሳስባቸው በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ ከአምስት አራቱ መንግሥታቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ አሠራሩን ማሻሻል አለበት ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
የንፁህ ውኃ ተደራሽነትን በተመለከተ፣ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ ወጣቶች በየቀኑ ውኃ ለማግኘት እንደሚቸገሩ፣ በጥናቱ ከተሳተፉት ግማሽ ያህሉ ንፁህ ውኃ ለማግኘት ከገቢያቸው አንድ አራተኛውን እንደሚያወጡ ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡
በርካታ ወጣቶች በተለይ ሴት በመሆናቸውና በጎሳቸው ምክንያት መገለል የሚደርስባቸው መሆኑ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ በጥናቱ ከተሳተፉት ግማሽ ያህሉ አገራቸው እኩልነትን አስፍኗል ብለው ሲያምኑ፣ ግማሹ ደግሞ በማንነታቸው ምክንያት አድሎ እንደሚደረግባቸው አመልክተዋል፡፡