Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የ5ጂ ከፍተኛ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ተለይተው አገልግሎቱ መሰጠት ተጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም በተመረጡና ከፍተኛ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በሚገኙባቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎች፣ የአምስተኛውን ትውልድ ሞባይል ኔትወርክ (5ጂ) አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ በአዲስ አበባና በአዳማ ከተማ በሙከራ ላይ የነበረው የ5ጂ ኔትወርክን ነው መንግሥታዊው የቴሌኮም ተቋም፣ በአዲስ አበባ ለሚገኙት ደንበኞቹ ለገበያ እንዳቀረበላቸው፣ ቅዳሜ ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በወዳጅነት አደባባይ ባካሄደው ፕሮግራም ያስታወቀው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በዋና ከተማዋ በሚገኙ የተመረጡ ቦታዎች 145 የሞባይል ጣቢያዎች የ5ጂ ኔትወርክ ዘርግቶ፣ በተለያዩ የጥቅል ዓይነቶችና ከ4ጂ ከፍ ባለ ዋጋ ለደንበኞቹ አገልግሎቱን አቅርቧል፡፡

ከመስቀል አደባባይ በመነሳት ወደ አያት በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ባሉ አካባቢዎች፣ እንዲሁም ወደ ሰሚት በሚወስደው መንገድ ላይ የ5ጂ አገልግሎት የሚያገኙ ቦታዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪም ከመስቀል አደባባይ ወደ አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ፣ እንዲሁም ከመስቀል አደባባይ በመነሳት በዋናው ቦሌ መንገድ ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና የቦሌ አካባቢዎች በሙሉ የ5ጂ ኔትወርክ ያገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል ከመስቀል አደባባይ በመነሳት ወደ ሜክሲኮና ሳር ቤት አካባቢዎች፣ በልደታና ብሥራተ ገብርኤል አካባቢዎች፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር በቸርችል ጎዳና ወደ ለገሃር በሚወስደው መንገድ ላይም አገልግሎቱ እንደሚገኝ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የእነዚህን ቦታዎች ኔትወርክ 5ጂ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት፣ በዋናነት ከፍተኛ የኢንተርኔት ዝውውርን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ በእነዚህ መስመሮች ላይ ያሉ ተቋማትም ከፍተኛ የሆነ የኢንተርኔት ፍላጎት እንዳላቸው ተረድተናል፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ቦታዎቹ የተመረጡበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

ማስፋፊያው በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነና በተያዘው በጀት ዓመት ዕቅድ መሠረት፣ ከአዲስ አበባ ውጪ የ5ጂ ማስፋፊያው እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ካሉት ወደ 34 ሚሊዮን የሚጠጉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መካከል፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገው የ4ጂ ማስፋፊያ አማካይነት 66 በመቶው የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በ4ጂ እንደሚጠቀሙ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ 630,000 ያህል የ5ጂ ኔትወርክን ሊቀበሉ የሚችሉ የኢንተርኔት መጠቀሚያ ስልኮች ሊኖሩ እንደሚችሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ቁጥርም ከኔትወርኩ መኖር ጋር ተያይዞ ሊያድግ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

የአምስተኛው ትውልድ (5ጂ) ሞባይል ኔትወርክ ተጠቃሚ ደንበኞች በሰከንድ እስከ አሥር ጊጋ ቢት የሚደርስ የኢንተርኔት ፍጥነት መጠቀም እንደሚችሉ የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ ያሳወቁ ሲሆን፣ ‹‹በአንድ ካሬ ሜትር ውስጥ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል›› እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ በአሁኑ ጊዜ 16 አገሮች የ5ጂ ቴክኖሎጂን እየተጠቀሙ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2026 የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች በብዛት 115 ሚሊዮን ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በዓለም ላይ 254 የሚሆኑ የቴሌኮም ኩባንያዎች የ5ጂ ቴክኖሎጂን ለደንበኞቻቸው እንደሚሰጡ፣ በ110 አገሮችም አገልግሎቱ እየተዳረሰ 1.3 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች