Friday, September 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የመንግሥት አገርን በብቃት የመምራት አቅምና የሕዝብ እርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ባልተጣጣሙበት ኩርፊያ፣ ግጭት፣ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሣሉ፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ሲቃኝ ደግሞ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ እምነቶች፣ የፖለቲካ አመለካከቶችና የመሳሰሉት ቢኖሩም፣ እነዚህን ልዩነቶች አቻችሎና አስታርቆ አገርን መምራትና እርካታ መፍጠር የግድ የሚባልበት ጊዜ ውስጥ ነን፡፡ ለዘመናት ሕዝቡ በልዩነቶቹ ውስጥ ሆኖ ያኖራትን አገር በአግባቡ መምራት ሲያቅት፣ ችግሮች ሲፈጠሩ አፋጣኝ መፍትሔዎችን አለመፈለግና ችላ ማለት ለአገር ህልውና አይበጅም፡፡ ለዘመናት በልዩነቶቹ አጊጦ የኖረ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት ነው፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ የሕዝብንና የአገርን ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶችን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ዋና ዋና ጉዳዮችን እንያቸው፡፡

በማናቸውም የዴሞክራሲ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ፓርቲዎች በምርጫ ሥልጣን ይይዛሉ፡፡ ለፖለቲካ ተሿሚዎችና ለባለሙያዎች ኃላፊነቶች ተለያይተው ይሰጣሉ፡፡ በሁሉም ሥፍራ የፖለቲካ ተሿሚዎችን ብቻ በመመደብ አገርን በካድሬ ለማስተዳደር ስለማይቻል፣ ለባለሙያዎች ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከፌዴራል ተቋማት እስከ ወረዳ መዋቅር፣ ከመንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋማት እስከ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ማደራጃ፣ ከጤና ድርጅቶች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሁሉም ቦታዎች ውስጥ የፓርቲ አባላትን መሰግሰግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይልቃል፡፡ ቀደም ሲል በፓርቲ ካድሬዎች ይደርስ የነበረው ጥፋት፣ በኤክስፐርትነትና በአማካሪነት ስም ከፍተኛ ተከፋይ በሆኑ አላዋቂዎች ተባብሶ እንዳይቀጥል መጠንቀቅ ይገባል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማትን ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ለማደራጀት ሲታሰብ፣ በዕውቀትም ሆነ በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ዜጎች እንደ ችሎታቸውና ዝንባሌያቸው አገራቸውን እንዲያገለግሉ ዕድሉ ይሰጣቸው፡፡ የፓርቲና የመንግሥት ሥራ እየተደባለቁ አገር መምራት የሚያቅተው፣ ለዚህ ሥልጡን አሠራር ጀርባ ሲሰጥ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ቦታዎች ሆን ብሎ ችግር መፍጠርና ቸልተኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሷል፡፡ የሚቆጣጠር አካል የለም ወይ እስኪባል ድረስ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ባለመቻሉ ምክንያት ብቻ፣ በየቦታው በጣም የሚያሳፍሩ ድርጊቶች ተንሰራፍተዋል፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ አገልግሎት ሲስተጓጎልበት ቅሬታ ቢያቀርብም አዳማጭ የለውም፡፡ በየቦታው ራሳቸውን ያነገሡ ሹማምንት ማንንም ሳያፍሩ በአደባባይ ጉቦ ይጠይቃሉ፡፡ አልሰጥም ያለውን ያንገላታሉ፡፡ ብልሹ አሠራሮችን በማስፈን የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የደላሎች መፈንጫ አድርገዋል፡፡ ፍትሕ ፍለጋ የሚባዝኑ ዜጎች ዕንባቸውን የሚያብስላቸው በመጥፋቱ ይብሰለሰላሉ፡፡ በወረዳና በክፍላተ ከተሞች፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በሕክምና ተቋማት፣ በግብይት ሥፍራዎች፣ በመንገድና ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች፣ ወዘተ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ቅንጦት ሆኗል፡፡ ለሚዲያ ፍጆታ ሲባል ብቻ ያልተሠራን እንደተሠራ በሐሰት ሪፖርት አንቆለጳጵሶ ማቅረብ ያሳፍራል፡፡ ጳጉሜን በደረሰ ቁጥር በአገልጋይነት ስም መመፃደቅ ነውር ነው፡፡

አስተዳደራዊ በደሎች በበዙ ቁጥር ሕዝብ ይከፋል፡፡ መጠኑ ሲያልፍ ደግሞ አመፅ ይቀሰቀሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ በመጠቀም ለራሳቸውና ለቡድናቸው ዝርፊያ የሚያመቻቹ ሞልተዋል፡፡ በትምህርት፣ በልምድና በክህሎት ያልበሰሉ ራስ ወዳዶች የራሳቸውን ኔትወርክ በመመሥረት ሕዝብን መቆሚያ መቀመጫ ካሳጡ በኋላ፣ ያገኙትን ዘርፈው ሹልክ ማለት ሲፈልጉ ነውጥ እንዲነሳ ያደርጋሉ፡፡ ብሔርን በብሔር ላይ የሚያነሳሱ፣ የአንዱን እምነት ተከታዮች በሌላው ላይ የሚቀሰቅሱና ፀብ የሚያጭሩ በብዛት እየፈሉ ነው፡፡ ከራሳቸው ጥቅም በላይ ለአገር ዘለቄታ ራዕይ የማይታያቸው፣ ከልካይ የሌለባቸው እስኪመስሉ ድረስ ትርምስ ይፈጥራሉ፡፡ ለሕግ የበላይነት ደንታ ስለሌላቸው ሕገወጥነትን እንደ መደበኛ ሥራ ያዩታል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማናቆር የጽንፈኛ ብሔርተኝነት ቁማር ያራግባሉ፡፡ በአንድነትና በሰላም ተከባብሮ ይኖር የነበረን ሕዝብ መሀሉ ገብተው በማይረቡ አጀንዳዎች ያበጣብጣሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት በመጣስ ሲያፈናቅሉና ንብረት ሲዘርፉ፣ የአገርን ክብር ጭምር እያዋረዱ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ካለፉት ጥፋቶች ባለመማር ተደጋጋሚ ስህተቶች ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ በአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ማግለል፣ የሃይማኖት መሪዎችን ማሸማቀቅ፣ የአገር ሽማግሌዎችን ማራቅ፣ ለአገር የሚጠቅሙ ምሁራንና ልሂቃንን አትድረሱብኝ ማለትና ወጣቶችን ተስፋ ማስቆረጥ ለዓመታት የዘለቀ የአገር በሽታ ነው፡፡ አገርን ለመምራት ከብቃትና ከቁርጠኝነት ባሻገር የተለያዩ አስተያየቶችን ማድመጥም የአመራር ችሎታ ማሳያ ነው፡፡ እየታየ ያለው ግን በአንድ አቅጣጫ በተቃኘ አስተሳሰብ የእውነትና የብርሃን መንገድ መሪ ለመሆን መንደፋደፍ ነው፡፡ የጀመሩትን ጉዞ ሳያቋርጡ በየመሀሉ የሌሎች ወገኖችን ምክርና የዕውቀት ተሞክሮ ማዳመጥ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን መልካም አጋጣሚ ወደ ጎን እየገፉ ከስህተት ወደ ስህተት መረማመድ ማንንም አያዋጣም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የታየው ግን ስህተትን በስህተት ለማረም መሞከር ነው፡፡ ከዚህ የሚገኘው ውጤት ደግሞ አንገት ከማስደፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ሕዝብ እርካታ እንዲሰማውና በአገሩ ተስፋ እንዲኖረው ካልተደረገ በስተቀር፣ እያስከፉት በግትርነት መቀጠል ውጤቱ አያምርም፡፡ ለአገር ሰላምም አይበጅም፡፡

በአጠቃላይ በአገር ደረጃ ለመለወጥና ለማደግ የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ግባቸውን የሚመቱት፣ ለዘመኑ የሚመጥን የአመራር ጥበብ መጎናፀፍ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ትናንት የነበረው የአመራር ጥበብ ለዛሬ አይሠራም፡፡ የዛሬውም ለነገ ጥቅም የለውም፡፡ በትናንት ታሪክ እየተኩራሩ የዛሬውን ዘመን በዚያው መንገድ ለመግራት መሞከርም ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ የትናንቱን እንዳለ በማናናቅ መኩራራትም አያስኬድም፡፡ ይህች አገር ምንም እንኳ ለዘመናት በድህነትና በኋላቀርነት ውስጥ ብትዳክርም፣ በአንድ ወቅት ገናና ታሪክ የነበራት ናት፡፡ ለዓለም ካበረከተቻቸው ቅርሶች፣ ሥልጣኔዎችና በልዩነቶች ውስጥ ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌታዊነቷ ጋር የተገመደው ታሪኳ፣ በጥቁር ዓለም ሕዝቦች ዘንድ አንፀባራቂ ያደረጋትን ፀረ ኮሎኒያሊስት ተጋድሎዋን ጭምር ይተነትናል፡፡ ለአገሩ ቀናዒ የሆነው ሕዝቧ ደግሞ ሕግ አክባሪ፣ ሰላም ወዳድና በአግባቡ የሚመራው ካገኘ በርካታ አንፀባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ የሚችል ነው፡፡ ይህንን ኩሩ ሕዝብ በአግባቡ መምራት አለመቻል የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ነው ይህንን የተከበረ ሕዝብና ይህችን የተከበረች አገር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...