Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማዕድን ላኪዎች ‹‹የደኅንነት ውል ስምምነት›› ሳይፈራረሙ ማዕድን እንዳይልኩ የሚያስገድድ ትዕዛዝ ተላለፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ላኪዎች ማዕድን መላክ አልቻልንም ብለዋል

የማዕድን ሚኒስቴር አዲስ ባወጣው ሕግና ለሁሉም ማዕድን ላኪዎች በላከው አስቸኳይ ደብዳቤ፣ ማንኛውም ማዕድን ላኪ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ‹‹የደኅንነት ውል ስምምነት›› ሳይፈራረሙ ማዕድን መላክ እንደማይችሉ አስገዳጅ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

የትዕዛዝ ደብዳቤው የተጻፈው ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲሆን፣ ባለፉት ቀናትም ላኪዎች ማዕድን ለመላክ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

በተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት በአውሮፕላን በመጠቀም ማዕድን ወደ ውጭ የሚልኩ ላኪዎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ውሉን መፈራረም ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ በባቡርና በሌሎች መንገዶች የሚልኩትም ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር መፈራረም አለባቸው፡፡

‹‹ማንኛውም በማዕድን ሥራ ላይ የተሰማራችሁ ድርጅቶችም ሆናችሁ ግለሰቦች ከዛሬ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የደኅንነት ውል ስምምነት መፈራረማችሁን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እስካላቀረባችሁ ድረስ፣ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ፈቃድ (Export Permit) የማንሰጥ መሆኑን እናሳውቃለን፤›› ይላል የማዕድን ሚኒስቴር ደብዳቤ፡፡

በተላለፈው ትዕዛዝ ላይ በቂ ማብራሪያና ማስረጃ የሚሰጥ አካል አለመኖሩን የሚናገሩት ላኪዎች በተላለፈው ውሳኔ ግራ መጋባታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹የደኅንነት ውል ስምምነት›› የተባለው ከደኅንነትና ከሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ጋር የተገናኘ ሲሆን፣ ማዕድናት በተገቢው መንገድ ከአገር ወጥተው ገዥው ዘንድ መድረሳቸውን ለማረጋገጥ የታለመ ነው፡፡ የሚያፈራርመው ተቋም ግን በማዕድን ቁጥጥር ላይ ሕጋዊ ኃላፊነት የሌለበት ቢሆንም፣ በስምምነቱ መሠረት የደኅንነት መሥሪያ ቤት ክትትል ያደርጋል ተብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ስምምነቱን ለመፈራም ወደ ተባሉት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወዲያውኑ የሄዱ ማዕድን ላኪዎች ለመፈራረም ሳይችሉ መቅረታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ላኪዎች በአውሮፕላን የሚልኩ ሲሆኑ፣ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማምራታቸውን ይናገራል፡፡

‹‹ባለሥልጣኑ የሚሞላ ፎርም ሰጠን፡፡ ግን እስካሁን መፈራረም አልቻልንም፡፡ በዚህ ምክንያት ሊላክ መንገድ ላይ የነበረ ማዕድን ለአራተኛ ቀን ቆሟል፡፡ ባለሥልጣኑ የተለያዩ ሰነዶች አምጡ እያለ እያመላለሰ አዘገየብን፡፡ እኛ ደግሞ ክፍያ ቀድመን ተቀብለን ውጭ ያለው ገዥ እየጠበቀ ነው፡፡ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስቀድሞ አሟልተን መምጣት ያለብንን ሰነዶች ቀድሞ ስላላሳወቀን በሄድን ቁጥር አዳዲስ ነገር ይጠይቀናል፡፡ መረጃውን በደንብ የሚያውቅና የሚያስረዳንም አካል የለም፤›› ሲሉ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ማዕድን ላኪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ላኪዎች ስምምነቱን ለመፈራረም የብቃት ማረጋገጫ፣ ማኅተምና ሌሎች ሰነዶችን ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ ስምምነቱን የሚፈራረመው ግን የላኪው ድርጅት ዋና ኃላፊ፣ ባለቤት ወይም ሥራ አስኪያጅ ካልሆነ አይቻልም መባላቸውን ነው ያስረዱት፡፡

‹‹የደኅንነት ውል ስምምነቱ ሁለት ዓላማ አለው፡፡ አንደኛው ላኪዎችን ለመክሰስ እንዲያመች ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ላኪዎች ኃላፊነት ተስምቷቸው ከተለያዩ ሕገወጥ ድርጊት እንዲቆጠቡ ነው፤›› ሲሉ የማዕድን ላኪው ያስረዳሉ፡፡

የመላኪያ ፈቃድ (Export Permit) ለማግኘት ከዚህ ቀደም ላኪዎች የሚልኩትን ማዕድን ዝርዝር፣ ቀንና የሚላክበት አገር ማስመዝገብ ብቻ በቂ ነበር፡፡ አሁን ግን የደኅንነት ውል ማሰር ግዴታ ሆኗል፡፡ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ለማግኘት የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች