Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት በአዲሱ ዓመት ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያስቆም ኢሰመጉ ጥሪ አቀረበ

መንግሥት በአዲሱ ዓመት ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያስቆም ኢሰመጉ ጥሪ አቀረበ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 በወጣው የአዲስ ዓመት መግለጫ፣ በ2016 ዓ.ም. መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣና ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስቆም እንዳለበት ጥሪ አቀረበ፡፡

መንግሥት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ በተገባደደው ዓመት ማኅበረሰቡ ከሕግ አግባብ ውጪ ለሆነ እስር፣ ሞት፣ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተዳርጎ መክረሙን የኢሰመጉ ያወጣው መግለጫ ያትታል፡፡

መንግሥት በአዲሱ ዓመት ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያስቆም ኢሰመጉ ጥሪ አቀረበ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

መንግሥት በ2015 ዓ.ም. በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች፣ በማኅበረሰቡና በንብረት ላይ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በአገር ላይ ከደረሰው ዘርፍ ብዙ ችግር በመማር፣ በቂ ትኩረት በመስጠትና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማወያየት አለመግባባቶች በሰላም የሚፈቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት ብሏል፡፡ በ2016 ዓ.ም. ማኅበረሰቡ በሰላም ተንቀሳቅሶ የዕለት ተዕለት ሥራውን የሚያከናውንበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ፣ በመንግሥት ላይ የተጣለ መሆኑን ኢሰመጉ አስታውሷል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ለማኅበረሰቡም ሆነ ለሰብዓዊ መብቶች ለሚሟገቱ ተቋማትም ከባድ እንደነበር በመግለጫው አትቷል፡፡ ‹‹ኅዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ በሚገኘው የኢሰመጉ ማዕከላዊ ቀጣና ጽሕፈት ቤት አቤቱታ ለማቅረብ ከመጡ 28 አቤቱታ አቅራቢዎች መካከል፣ 22 ያህሉ አቤቱታ አቅርበው እንደወጡ፣ በመንግሥት የፀጥታ አካላት የታሰሩበትና ይህም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸው ሰዎች በነፃነት ለኢሰመጉ አቤቱታ እንዳያቀርቡ ፍራቻን ፈጥሯል፤›› ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም የኢሰመጉ ቢሮ ተሰብሮ የምርመራ ሰነዶች የተወሰዱ መሆናቸውንና ጉዳዩን ከመመርመር ይልቅ ሊያመለክቱ የሄዱትን የኢሰመጉ ባልደረቦች፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ማሰሩን ገልጿል፡፡ ኢሰመጉ መረጃ እንዳያገኝም ከመንግሥት በኩል ፈቃደኝነት አለመኖሩንና በሥራው ላይ እንቅፋት አክሏል፡፡

‹‹ዜጎች በነፃነት የመዘዋወር መብት ያላቸው ሲሆን፣ ባሳለፍነው 2015 ዓ.ም. በተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች በዘፈቀደ የሚፈጸሙ ሕገወጥ እስሮች፣ በመንግሥት አካላት የሚፈጸሙ አስገድዶ መሰወሮችና በተገቢው ጊዜ ፍርድ ቤት ያለ ማቅረብ ድርጊቶች እንዲቆሙ፤›› ሲል ኢሰመጉ በአፅንኦት በመግለጫው ጠይቋል፡፡

በተለይ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግድያና መፈናቀሎች የሰፈኑበት የተገባደደው ዓመት ልምምዶች በአዲሱ ዓመት መደገም እንደሌለባቸው ኢሰመጉ አሳስቧል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹መንግሥት በተለመደና በተሳሳቱ መንገዶች ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በጅምላና በዘፈቀደ ማሰር መቀጠሉን እንዲያቆም፤›› ሲል ጠይቋል፡፡

በተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ በመጠየቅና ለተራዘመ የቅድመ ክስ ጊዜ ለእስር መዳረግ፣ ፍርድ ቤት የዋስትና መብት ሲፈቅድ ፖሊስ አለቅም ብሎ ጋዜጠኞችን ያለ ምንም ክስ አስሮ ማቆየት የመንግሥት ድርጊቶች ሆነው መቀጠላቸውን፣ 35 የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ መኮነናቸው ይታወሳል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ከአምስት ወራት በላይ የቆየና አሁንም በከፊል በተለያዩ አካባቢዎች ኢንተርኔት የተቋረጠ መሆኑን፣ ግጭቶች በተነሱ ቁጥር ለተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች አግባብነት የሌላቸው ፍረጃና ስያሜ መስጠት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገጉ የዜጎች ነፃነትና መብት ላይ የተራዘሙና ጊዜያዊ ጉዳቶች ማድረስ፣ እንዲሁም ያልተመጣጠኑ የኃይል ዕርምጃዎች በመንግሥት በኩል በስፋት እየተወሰዱ መቆየታቸውንና አሁን ሥጋት እንደሆኑ ወደ 2016 ዓ.ም. መሻገራቸውን 35ቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በመግለጫቸው አሳስበው አገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

 ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የሃይማኖት ተቋማት፣ በአገሪቱ እንደ መደበኛ እየተቆጠረ የመጣው ግጭትና ቀውስ በአዲሱ ዓመት መቆም እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በቀጥታ ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመጻፍ፣ በአገሪቱ ያለውን አሥጊ ሁኔታ እሳቸውና ፓርቲያቸው በመረዳት ችግሮች እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በበኩላቸው፣ በአዲሱ ዓመት የመሣሪያ አፈሙዞች በሙሉ ወደ መጋዘን መግባት እንዳለባቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...