Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዓለም ሻምፒዮን ማራቶንን ያቋረጠው ታምራት ቶላ በግል ውድድር ድል ቀንቶታል

በዓለም ሻምፒዮን ማራቶንን ያቋረጠው ታምራት ቶላ በግል ውድድር ድል ቀንቶታል

ቀን:

  • ሞ ፋራ የሩጫ ሕይወቱን በግማሽ ማራቶን ቋጭቷል

በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን በወንዶች ማራቶን ውድድር በእክል ማጠናቀቅ ያልቻለው ታምራት ቶላ፣ የኒው ካስትል የግማሽ ማራቶን ውድድርን አሸንፏል፡፡

እሑድ ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በኒው ካስትል ታላቁ ሰሜን ግማሽ ማራቶን (Great North Run Half Northern) በተካሄደው ውድድር 59፡85 ደቂቃ በመግባት አሸንፏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2022 በኦሪጎን ዓለም ሻምፒዮን በወንዶች ማራቶን ወርቅ ማሳካት የቻለው ታምራት፣ በዘንድሮ የቡዳፔስት የማራቶን ውድድር ከ38 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ አልቻለም ነበር፡፡

ታምራት በኦሪጎን የነበረውን ብቃት ተከትሎ፣ በዘንድሮ ሻምፒዮና እንደገና ድል ይቀዳጃል የሚል ግምት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ ውድድሩን ግን ማጠናቀቅ ሳይችል ቀርቷል፡፡ አትሌቱ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት መሠረት፣ ከ38 ኪሎ ሜትር በኋላ የጨጓራ ሕመም ገጥሞት ለማቋረጥ እንደተገደደ ገልጾ ነበር፡፡

በሌላ በኩል በ5000 ሜትር የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮናው ሙክታር እድሪስ 61፡45 በሆነ ሰዓት የግሬት ኖርዝ ግማሽ ማራቶን ሦስተኛ የወጣ ሲሆን፣ ቤልጂማዊው በሽር አብዲ 61፡20 በሆነ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

የአራት ጊዜ የኦሊምፒክና የስድስት ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮኑ ትውልድ ሶማሊያዊ እንግሊዛዊ ሞ ፋራህ ግማሽ ማራቶኑን 63፡28 በሆነ ጊዜ አራተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡

የትራኩ ድምቀት ሰርሞ ፋራህ የአትሌቲክስ ሕይወቱ በዚህ ግማሽ ማራቶን መቋጨቱን አስታውቋል፡፡ ሞ ፋራህ በአትሌቲክሱ የነበረው ስኬታማ ጊዜ በዓለም አትሌቲክስ አፍቃሪያን ዘንድ እንደሚዘከር ተጠቁሟል፡፡ የአትሌቱ ቀጣይ ምዕራፍ ምን እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል የአትሌክስ ፈርጧ፤ የሦስት ጊዜ የኦሊምፒክና የአምስት ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮኗ ጥሩነሽ ዲባባ በግማሽ ማራቶን ውድድሩ እንደምትካፈል ቢገለጽም፣ በመጨረሻው ሰዓት እንደማትካፈል ተገልጿል፡፡ በትራክ ውድድሮች የደመቀችው ጥሩነሽ፣ በጥቂት የማራቶን ውድድሮች ላይ መካፈል ብትችልም በጎዳናው ውድድር ላይ እምብዛም ልትታይ አልቻለችም፡፡

በሴቶች ግማሽ ማራቶን ኬንያዊቷ ፕሬስ ጄብቼር 1፡06፡45 በሆነ ጊዜ አሸንፋለች፡፡ ሻሮን ሎኪዲ 1፡07፡43 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ስትወጣ፣ እንግዛዊቷ ቻሮሌቲ ፐርዱ በ1፡09፡36 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

እ.ኤ.አ. ከ1981 ወዲህ የጀመረው የግሬት ኖርዝ ሩጫ 60,000 ተሳታፊዎች ይካፈሉበታል፡፡ በዚህም ምክንያት ትልቁ የሰሜን ግማሽ ማራቶን ውድድር የሚል ስያሜን አግኝቷል፡፡

ውድድሩ በአካባቢው ደመቅ ያለ ድጋፍ ያለው ሲሆን, ከመሃል ከተማዋ ተነስቶ፣ የባህር ዳርቻውን ይዞ ይከናወናል፡፡ በውድድሩ ለመካፈል በከተማዋ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሁም በኒው ካስትል ከተማ አቅራቢያ ያሉ አጎራባች የኅብረተሰብ ክፍሎች በሰፊው ይሳተፋሉ፡፡

የግማሽ ማራቶኑን ላሸነፉ አዋቂ አትሌቶች በሁለቱም ፆታ አንደኛ ለወጣ 1,500 ፓውንድ፣ ሁለተኛ ለወጣ 1,250 ፓውንድ፣ ሦስተኛ ለወጣ 750 ፓውንድ፣ አራተኛ ለወጣ 500 ፓውንድ፣ እንዲሁም አምስተኛ ለወጣ 300 ፓውንድ እንደ ደረጃቸው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ውድድሩ በተለይ ከትራክ ሩጫ ወደ ጎዳና ሩጫ መሻገር ለሚፈልጉ ጀማሪ አትሌቶች ልምድ ማዳበሪያ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዘው በርካታ አትሌቶች ከትራክ ይልቅ ወደ ጎዳና ውድድሮች እየዘነበሉ መምጣታቸውን ተከትሎ፣  በተለያዩ ከተሞች የሚከናወኑ የጎዳና ውድድሮች፣ የሽልማታቸውን መጠን በማሻሻል ታዋቂ አትሌቶችን እየጋበዙ ይገኛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...