Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበሺዎች የሚቆጠሩ ያለቁበት የሞሮኮ ርዕደ መሬት

በሺዎች የሚቆጠሩ ያለቁበት የሞሮኮ ርዕደ መሬት

ቀን:

ዓርብ ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሞሮኳውያን በተለይም በጥንታዊቷ የሞሮኮ የቱሪስት መዳረሻ ማራካሽ ከተማ አቅራቢያ ለሚኖሩት ጥሩ ቀን አልነበረም፡፡

በዕለቱ የተከሰተውና ባለሙያዎች 6.8 ማግኒቲውድ ነበረው ያሉት ርዕደ መሬት፣ ከ2,000 በላይ ሰዎችን ገድሏል፡፡ ከ2,400 በላይ ሰዎችን ደግሞ ለጉዳት አጋልጧል፡፡

ከማራካሽ ደቡብ ምዕራብ 72 ኪሎ ሜትር ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ላይ የተከሰተው ርዕደ መሬት፣ የመኖሪያ አካባቢዎችን፣ መሠረተ ልማቶችንና የቱሪስት መስህብ የሆኑ ጥንታዊ ቅርሶችንም ወደ ፍርስራሽነት ቀይሯል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ይገኙበታል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ያለቁበት የሞሮኮ ርዕደ መሬት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ከማራካሽ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘውና በተራራ ላይ የተመሠረተው ታፍጋጌት መንደር ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከወደሙ ሥፍራዎች አንዱ ነው፡፡

በዓል ሐውዝ ግዛት የሚገኘው አሚዝሚዝ አካባቢ የርዕደ መሬቱ እምብርት ሲሆን፣ በዚህና በታፍጋጌት ብቻ ከ1,300 በላይ ሰዎች አስከሬን ተገኝቷል፡፡

በአል ሐውዝ ብቻ ከ18 ሺሕ በላይ ቤተሰቦች ከሥፍራው የተፈናቀሉ መሆኑንም የሞሮኮ ቴሌቪዥን መዘገቡን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የቱሪዝም እምብርት በሆነችው የሞሮኮዋ ጥንታዊት ከተማ ማራካሽን የከበበው ‹‹ሬድ ዎል›› በርዕደ መሬቱ ከተጎዱ ቅርሶች አንዱ ነው፡፡

‹‹እስከ ፖርቱጋልና ስፔን ስሜቱ ነበር›› የተባለው የርዕደ መሬት ከሕፃናት እስከ አዋቂ ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ በርካታ ቤተሰቦችን እንዲለያዩ አድርጓል፡፡ የዕርዳታ ሠራተኞች ከፍርስራሽ ሥር አስከሬኖችን በማውጣት ሥራ ተጠምደዋል፡፡ በርካታ ቤተሰቦችም በአንድ ላይ ባሉበት ሞተዋል፡፡

የሞሮኮ ብሔራዊ ጂኦ ፊዚክስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ናስር ጃጉር፣ የሰሜን አፍሪካ አገሮች እ.ኤ.አ. ከ1900 ወዲህ እንዲህ ያለ ከባድ ርዕደ መሬት አስተናግደው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ በ1960 የተከሰተውና 5.8 ማግኒቲውድ የተመዘገበው ርዕደ መሬት መከሰቱንም ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፡፡

በ12ኛው ምዕት ዓመት እንደተሠራ የሚነገረውና በማራካሽ የሚገኘው ኮቱቢያ መስጊድ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ይህ የማራካሽ መገለጫ የሆነው መስጊድ፣ የማራካሽ ጣራ ‹‹ዘ ሩፍ ማራካሽ›› የተባለ 69 ሜትር ርዝመት ያለው የአዛን (የጸሎት) ጥሪ ማድረጊያ ያለው መስጊድ ነው፡፡

ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ከስድስት ማግኒቲውድ በላይ የሆነ ርዕደ መሬት ከዚህ ቀደም አስተናግዳ አታውቅም፡፡ ይህም አገሪቱ ጠንካራ የግንባታ ሕግ እንዲኖራት አድርጎ ለዓመታት ቆይቷል፡፡ በ1960 የተከሰተውና 5.8 ማግኒቲውድ ያስመዘገበው ርዕደ መሬት፣ በሞሮኮዋ አጋዲር በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቀጠፈና መኖሪያዎችንና መሠረተ ልማቶችን ካወደመ በኋላ፣ አገሪቱ ጠንካራ የግንባታ ሕግ ብታወጣም ይህ በአግባቡ እንደማይተገበር የአገሪቱ ሚዲያዎች ይገልጻሉ፡፡

በሞሮኮ የሚገኙ በርካታ ሕንፃዎች በተለይም በገጠር የሚገኙት በሕጉ መሠረት እንደማይገነቡም ይናገራሉ፡፡

በ2004 በሜዲትራኒያን የባህር ዳርቻ ከተማዋ አል ሆሲማ የተከሰተው ርዕደ መሬት፣ ከ600 በላይ ዜጎችን መግደሉንም ለግንባታ ጥራት መጓደል እንደ ለአብነት ያነሳሉ፡፡  

እስካሁን ድረስ ርዕደ መሬቱ የተመዘገበው የሞቱ ቁጥር በመሬት 2,122 የደረሰ ሲሆን፣ የተጎዱት ደግሞ 2,421 እንደነበሩ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ዘገባ ያመለክታል።

የሟቾች ቁጥር በሐውዝ 1,351፣ በትራውዳንት 492፣ በቺቻውዋ 201  በማራካሽ ደግሞ 17 ደርሷል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በሞሮኮ በደረሰው ርዕደ መሬት ሐዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የዕርዳታ ድርጅቶችና ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ዕገዛ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፣ አሁንም ዕገዛ ማድረግ የጀመሩ አሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...