Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፈታኝነቱ ያሳሰበው የልብና የደም ቧንቧ በሽታ ሕክምና

ፈታኝነቱ ያሳሰበው የልብና የደም ቧንቧ በሽታ ሕክምና

ቀን:

በዓለም በየዓመቱ 18 ሚሊዮን ሰዎች በልብ በሽታ እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ መሆኑ ችግሩን የበለጠ አጉልቶታል፡፡

ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ እንዲሁም በሕክምና አገልግሎት አሰጣጡ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየነጠቀ ነው፡፡

ችግሮችን ለመፍታት መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ታዝማ የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ማዕከል በዘርፉ የሚታየውን የአሠራር ክፍተት ለመሙላት፣ ሰሞኑን የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንዲሁም የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች በተገኙበት ውይይት አካሄዷል፡፡

የጤና ሚኒስትር ሊያ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በዓለም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እነዚሁ በሽታዎች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ ከእነዚህም ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች መሆናቸውን አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 30 ሺሕ የሚሆኑ ሕፃናት ከልብ በሽታ ጋር አብረው እንደሚወለዱና ከእነዚህ ውስጥም ዘጠኝ ሺሕ የሚሆኑት ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ሊያ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሦስት በመቶ ትምህርት ቤት ያሉ ሕፃናት የ‹ሂውሮማቲክ› የልብ በሽታ ተጠቂ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ምንም እንኳን የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች የሞት ዋና ዋና መንስዔዎች ቢሆኑም፣ አብዛኛዎቹ በተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የማይችሉ መሆኑን ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከመሠረተ ልማት፣ በቂ ባለሙያ ካለመኖርና ከግብዓት አኳያ የሚታዩ ችግሮች ለተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መስፋፋት ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወቱ አብራርተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ሚኒስቴሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከመከላከል ጀምሮ ስፔሻላይዝድ ሕክምናን ተደራሽ ለማድረግ፣ ስትራቴጂ ቀርፆ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

ስትራቴጂው ከሁለት ዓመታት በኋላ እንደሚተገበር የገለጹት ሊያ (ዶ/ር)፣ መንግሥት በቀጣይ በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ከሥልጠና ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስፔሻላይዝ አገልግሎቶች ለመስጠት ብዙ መሥራት እንደሚገባና የግል ተቋሞችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ አስታውሰዋል፡፡

በዓለም ከ620 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወይም ከ13 ሰዎች መካከል አንዱ የልብና ከልብ ጋር ተያያዥነት ባለው በሽታ የሚያዝ መሆኑን፣ የታዝማ የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ታዝማ የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ማዕከል እስከዛሬ ከ450 በላይ ሕፃናትና አዋቂዎች የልብና ሌሎች መሰል ቀዶ ሕክምናዎችን ማከናወን መቻሉን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከልብ ነቀላ ውጪ ሁሉንም ዓይነት የልብ ቀዶ ሕክምናዎች በአገር ውስጥ እንደሚሰጥ ያስታወሱት አቶ አስቻለው፣ የሕክምና አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ የሚያደርገው በኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የልብ በሽታ ገና ከሚወለዱ ሕፃናት ጀምሮ አረጋውያንን ጭምር የሚያጠቃ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑን የልብ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ሲሳይ በቀለ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የልብ በሽታ በተፈጥሮና በሒደት የሚከሰት ሲሆን፣ በአብዛኛው በተፈጥሮ በሽታ የሚጠቁት ሕፃናት እንደሆኑና ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ ሰዎች በበሽታው የሚያዙት ከተጓዳኝ በሽታ ጋር ተያይዞ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የኮሌስትሮል መጨመር፣ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ ከልብ የሚነሱ ትልልቅ ደም ሥሮች የመተለቅ ሁኔታ ሲታይ የልብ በሽታ ሊከሰት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህ ተጓዳኝ በሽታዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡ የልብ ደም ሥር መዘጋትና ከልብ የሚነሱ ትልልቅ ደም ሥሮች መተለቅ ለልብ በሽታ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸው፣ በኢትዮጵያም ለእነዚህ የልብ በሽታዎች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች ጥቂት እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ሕክምና የሚሰጠው በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ገልጸው፣ የልብ ቀዶ ሕክምና ለመስጠት የሚያገለግሉ ግብዓቶች ከፍተኛ እጥረት ስላለ፣ በርካታ ሕሙማን በተገቢው መንገድ ሕክምና እያገኙ አይደለም ብለዋል፡፡

በአብዛኛው ለልብ በሽታ የሚያገለግሉ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸውም፣ በኢትዮጵያ የተፈለገውን ያህል የልብ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ የተነሳ የተለያዩ የልብ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መሥራት ከሚችሉት አቅም በታች እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተሻለ ግብዓት ቢኖር በሰፊው አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ይቻል ነበር ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በልብ ማዕከል ውስጥ ከሕፃናት ጀምሮ እስከ አዋቂዎች ድረስ ከሰባት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሕሙማን የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ወረፋ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት በርካታ ሕሙማን ወረፋ ደርሷቸው ሲደወልላቸው በሕይወት እንደማይኖሩ ገልጸው፣ ይህም በአፍሪካ ደረጃ መኖሩን ሲሳይ (ዶ/ር) ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ባለሙያዎች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውን፣ በዚህም የተነሳ በየተቋሙ በቀን አንድ ሕሙም ብቻ አገልግሎት እንደሚያገኝ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ታዝማ የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ማዕከል በቀን ለሁለት ወይም ለሦስት የልብ ሕሙማን አገልግሎት መስጠት እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

በልብ ነክ በሽታዎች ሰዎች ለሞት ተጋላጭ የሚሆኑበት ዋነኛ ምክንያት ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት፣ በባክቴሪያ አማካይነት የሚከሰት የጉሮሮ ቁስለት፣ የአየር ብክለት፣ የደም ውስጥ ቅባትና የስኳር መጨመር ጋር ተያይዞ የጉሮሮ ሕመምና ጭምር መሆኑን አንድ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ዕድሜያቸው በተለይም ከ30 እስከ 50 ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የዚህ በሽታ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ጤናማ የሆነ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ጭንቀት፣ አደንዛዥ ዕፆችን መጠቀምና አልኮል ነገሮችን ከመውሰድ ጋር ተያይዞም የልብ ሕመም ሊከሰት ይችላል፡፡

የ2015 ዓ.ም. የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ በልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ምክንያት በየቀኑ በአማካይ 170 ሰዎች እንደሚሞቱ፣ ከዚህ ውስጥ 45 በመቶው በልብ የደም ቧንቧ ጥበት፣ 34 በመቶው በስትሮክ፣ እንዲሁም 11 በመቶ በደም ግፊት ለሕልፈት ይዳረጋሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...