Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አሳረኛ ወጎቻችን!

በበዓል ማግሥት የተለመደው አሳረኛ ኑሮ የዕለት እንጀራ ፍለጋ ያሯሩጠናል፡፡ ታክሲ ጥበቃ ሠልፍ ላይ ወሬው በየዓይነቱ ደርቷል፡፡ ከበዓል ዋዜማ ገበያ አቅም በፈቀደው መጠን የታለፈው የየራስ ጎጆ ውሎ ድረስ በምሬትና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ብዙ ይወራል፡፡ አሳረኛው የኑሮ ውድነት የብዙዎችን ጀርባ አጉብጦት በበዓል ማግሥት የሚወራው ሁሉ ለጆሮ ይከብዳል፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ የውጥረቱን ወሬ ረገብ የሚያደርጉ ቀልዶች ይሰማሉ፡፡ አንድ ያደረ ስካር ያለቀቀው የሚመስል ጀብራሬ፣ ‹‹አዳሜ የቅርጫ ቅንጥብጣቢ ላይ ሲራኮት እኔና ቢጤዎቼ ሰርዶ የመሰለ ጠጅ እያወራረድን ስንታዘብ፣ በዓል ያለ ሥጋ እንዳይከበር ሕግ ያወጡ የድሮ ሰዎች ዘራቸው ከአንበሳ ነበር ወይ ብለን እየተሳሳቅን ነበር…›› ብሎ የበለዙ ጥርሶቹን እያሳየን ሲስቅ፣ እኛም ሳንወድ አጅበነው ሳቁን አስነካነው፡፡ ‹‹እውነቱን ነው እኮ፣ የአንዳንዱ ሰው የሥጋ ፍቅርና አበላል ሲታይ የአንበሳ ልደት የሚያከብር ነው የሚያስመስለው…›› እያለች አንዲት ከሲታ ወጣት ጨዋታውን ማድራት ጀመረች፡፡ ቀለል ሊለን ነው መሰል!

አንዲት በዕርጅና ምክንያት ጎስቆል ያለች ሚኒ ባስ መጥታ ተረኞች ተሳፍረን ቦታችንን ያዝን፡፡ ወያላውና ሾፌር ተጠቃቅሰው ታክሲዋን ከጠቀጠቁ በኋላ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ወሬው ሲጀመር ታዳሚ የነበርን በሙሉ የታክሲዋ ተሳፋሪ ሆነን ሠልፍ ላይ የተቋረጠው ወግ ሊቀጥል ግድ ሆነ፡፡ መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየሙ አዛውንት ወደ ከሲታዋ ወጣት ዞር ብለው፣ ‹‹የአንበሳ ልደት ስትይ ምን ትዝ አለኝ መሰለሽ…›› ሲሉ ወያላው ድንገት ጥልቅ ብሎ፣ ‹‹ዕድሜ ልክ የአንበሳ ወኔን እያሞካሸን ነው ከመገዳደል አባዜ መውጣት ያቃተን…›› ብሎ ሌላ አተካራ ማስነሻ ርዕስ አመጣ፡፡ ‹‹አንተ ስለምን እያወራን እንደነበረ ገብቶህ ነው በዚህ ቀሽም ጭንቅላትህ ትንተና የጀመርከው…›› ብላ ከሲታዋ ወጣት ስታንባርቅ፣ ‹‹ልጄ አይዞሽ ተረጋጊ፣ የአሮጌው ዓመት የዞረ ድምር አለቀው ብሎ ነው የሚዘባርቀው…›› በማለት ነገር ሲያበርዱ፣ ‹‹አይ አንቺ አገር፣ ዘንድሮማ ወያላም የፖለቲካ ተንታኝ ሆኖ ሳያስደምመን አይቀርም…›› እያለ አንዱ ከጥግ ነገር ሲያቀሳስር፣ ‹‹ከማንም ተምሬያለሁ ባይ ዘባራቂማ እኛ የበለጠ ባህሪያችሁን ስለምናውቅ ለትንተናው አትሥጋ…›› ብሎ ወያላው ሲስቅ ለጊዜው ውጥረቱ ረገበ፡፡ ይሻላል!

አዛውንቱ ግን የጀመሩት ወግ ቢቋረጥባቸውም እንዲሁ በዋዛ መላቀቅ የፈለጉ አይመስልም፡፡ ‹‹የእኔ ልጅ…›› ብለው ወደ ከሲታዋ ወጣት ዞር ካሉ በኋላ፣ ‹‹…ወጋችን የአንበሳም አልነበር፡፡ ድንገት ዘባራቂው ወያላ ቢያቋርጠንም አጋጣሚውን በመጠቀም አንድ ታሪክ ልንገርሽ፡፡ አንድ ጊዜ አህያና ነብር የሳርን ቀለም አስመልክተው ክርክር  ይጀምራሉ፡፡ አህያ ከጨሌው ሳር ነጨት ነጨት አድርጋ አያ ነብሮ የዚህ ሳር ቀለም እኮ ሰማያዊ ነው ትለዋለች፡፡ አያ ነብርም ምን ነካሽ አረንጓዴ ነው ብሎ ይቃወማል፡፡ ጭቅጭቃቸው ሊያባራ ባለመቻሉ አንበሳ ዘንድ ሄደው ፍርድ ለመጠየቅ ይስማማሉ፡፡ በዚህ መሠረት ጉዞ ወደ አንበሳ ቤተ መንግሥት ሆነ…›› ሲሉ ያ የዞረ ድምር ያለቀቀው ጀብራሬ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ‹‹ፋዘር ይህንን ተረት የሰሙት አንበሳ ማሰሪያ ጠጅ ቤት ነው ወይስ የፒያሳ ልጆች በዚህ በኩል አለፉ ፓስቴ ቤት ነው? የት እንደሆነ እንጃ እንጂ ይህንን ተረት የዛሬ 30 ዓመት የሆነ ቦታ ሰምቸዋለሁ…›› ከማለቱ ያቺ ከሲታ ወጣት፣ ‹‹አንተ የትም ስማው፣ እኛ ወጣቶቹ ምናለበት እዚህ ታክሲ ውስጥ ብንሰማው…›› ብላ የአዛውንቱ ወግ እንዳይቋረጥ ተማፀነች፡፡ እውነቷን ነው!

አዛውንቱ ወጣቷን አመሥግነው ጀብራሬውን በሰያፍ ካዩ በኋላ በተረጋጋ ስሜት፣ ‹‹…ነብርና አህያ አንበሳ ዘንድ ቀርበው የመጡበትን ጉዳያቸውን በየተራ አስረዱ፡፡ መጀመሪያ አህያ ለደኑ ንጉሥ የሚገባውን ክብር ሰጥታ ሳሩ ቀለሙ ሰማያዊ መሆኑን ለነብሩ ደጋግማ ብታስረዳው ሊሰማት እንዳልቻለ፣ እሱ ግን አረንጓዴ እንደሆነ ድርቅ ማለቱን ተናግራ ፍርድ እንዲሰጣት ጠየቀች፡፡ አንበሳም ያለችው በሙሉ ትክክል መሆኑን ገልጾላት በፈገግታ ሲያያት፣ በደስታ እየጨፈረችና ነብሩን እየተሳለቀችበት ተቀምጣ ፍርድ መጠባበቅ ጀመረች፡፡ አንበሳ ነብርን በቁጣ እያየው አህያ ያለችውን ደግሞለት፣ ሦስት ቀን ሙሉ ምግብ የሚባል ነገር እንዳይቀምስ ፈረደበት፡፡ በተሰጠው ፍርድ ያዘነው ነብር ለምን አንበሳ ኢፍትሐዊ ፍርድ እንዳስተላለፈበት ሲጠይቀው፣ የሳሩ ቀለም አረንጓዴ የመሆኑን እውነታ እያወቅህ ለምን ከዚህች ከማይገባት እንስሳ ጋር ተከራክረህ ታሰድበናለህ አለው ይባላል…›› ሲሉ ሙሉ ታክሲዋ በሚባል ሁኔታ ሳቅ በሳቅ፣ ሁካታ በሁካታ ሆነ፡፡ ነገሩ ቅኔ መሰለ!

አንድ ጎልማሳ ምሁር መሳይ ዓይኑ ላይ የደነቀረውን መነጽር ወደ ግንባሩ እየገፋ፣ ‹‹የዚህ የነገሩን ነገር ሞራላዊ ዕሳቤውን ምን ይሆን…›› ሲላቸው፣ ‹‹ወንድሜ ሁሉም በፈለገው ዓውድ ዕሳቤውን የመረዳት መብት አለው፡፡ የእኔን ንገረኝ ካልከኝ ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዘልቆ የገባው ችግር በነበረበት እንዳይቀጥል ከተፈለገ፣ ራሳችንን ከአላስፈላጊ ጭቅጭቆችና ንትርኮች በመራቅ ለዕውቀትና ለክህሎት ከፍ ያለ ቦታ እንስጥ ነው የምለው፡፡ ትልቁ የጊዜና የሀብት ብክነት ምክንያቱ በማያስፈልጉ ተራ ጉዳዮች ላይ መነታረክና ወደ ግጭት ማምራት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ዕውቀት ያላቸው ብሩሆች በመረጃና በማስረጃ የተጠናቀረ ጉዳይ ሲያቀርቡ፣ የመረዳት አቅም ውስንነት ያለባቸው ደግሞ ላለመቀበል ሲያንገራግሩ ችግር ይፈጠራል፡፡ በተለይ በራሳቸውና በመሪዎቻቸው የሚታበዩ ደናቁርት በጥላቻና በክፋት ታውረው፣ ራሳቸውን ብቻ ትክክለኛ አድርገው በማቅረብ ያስፈራራሉ፡፡ አልቀበልም ያላቸውን ደግሞ ከመግደል ወደኋላ አይመለሱም፡፡ ስለዚህ በአዲሱ ዓመት ማድረግ ያለብን በማይረቡ ጉዳዮች ከማይረቡ ሰዎች ጋር መነታረክ ማቆም ነው፡፡ ምክንያቱም ብናስረዳቸውም አይገባቸውም፡፡ እኛ ደግሞ እነሱን ወክለን መረዳት አንችልም…›› ብለው ሲያሳርጉ በመገረም ነበር የተመለከትናቸው፡፡ ግሩም ድንቅ ነው!

የታክሲያችን ጉዞ ቀጥሏል፡፡ ወያላና ሾፌር መንገድ ላይ በወረዱ ተሳፋሪዎች ምትክ ለማሳፈር በየቦታው እያቆሙ ከማስቸገራቸው ውጪ ወጉ ደርቷል፡፡ በዞረ ድምር ከስካሩ ጋር የሚታገለው፣ ‹‹ጎበዝ እንዴት ነው ዘንድሮም እየተዋጋን እንቀጥላለን ወይስ ዕርቀ ሰላም አውርደን ይቅር በመባባል አብረን ተቃቅፈን እንጠጣለን… ማለቴ ያው ከሥራ በኋላ መሸታ ቤት እንደምንገናኘው ከጦፈ ውጊያ በኋላም እዚያ ብንገናኝ ይሻላል ብዬ ነው…›› ከማለቱ፣ ‹‹አንተ ሰውዬ መሣሪያ ያነገቡ ሰዎችን መሸታ ቤት አገናኝተህ የበለጠ ቀውስ ለመፍጠር ነው እንዴ ዓላማህ…›› ብሎ አንድ ወጣት ጥያቄ ሲያቀርብለት፣ ‹‹ይኸውልህ ወጣቱ አትሳሳት፣ እኔ በመሸተኝነት በጣም የዳበረ ልምድ አለኝ፡፡ በ30 ምናምን ዓመታት የመሸታ ቤት ልምዴ ብርሌ በሰው አናት ላይ እንደ ሚሳይል ሲምዘገዘግ ያየሁት ግፋ ቢል ከሦስትና ከአምስት ቀናት አይበልጥም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከመሸታ ቤት ውጪ ባሉ ዓውደ ውጊያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልሚያዎችን አካሂዳ ሚሊዮኖችን ሰውታለች፡፡ ጠላ፣ ጠጅ፣ አረቄ፣ ጂን፣ ቮድካ፣ ውስኪና ሌሎች መጠጦች የሚገኙባቸው መሸታ ቤቶች አልፎ አልፎ በመለስተኛ ጥጋብ ተራ ድብድብ ካልሆነ በስተቀር የሰው ሕይወት የሚነጥቅ ውጊያ አላየሁም…›› ሲል ዝምታ ነገሠ፡፡ ዝም ጭጭ ያሰኛል እኮ!

ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል፡፡ ወያላው የዛሬው የታክሲ ወግ ሰቅዞ ይዞት ነው መሰል ሐሳብ ማጋራት አልፈለገም፡፡ ሾፌሩም የተለመደውን የሬዲዮ ካሴት ዘግቶ ወጉን በጉጉት እየኮመኮመ ነው፡፡ በዚህ መሀል ነበር አንድ ዝምተኛ መሳይ ልጅ እግር ወጣት፣ ‹‹እኔ እኮ ሰካራም ሲባል ቁምነገር ያለው አይመስለኝም ነበር…›› እያለ በመገረም አጠገቡ ላለው ጓደኛው በለሆሳስ ሲናገር ሰማነው፡፡ አዛውንቱ ልጅ እግሩን እያዩት፣ ‹‹አንዳንዴ በዋልድባም ይዘፈናል ይባላል እኮ…›› አሉ፡፡ ጀብራሬው ግን አሁንም የበለዘ ጥርሱን ብልጭ አድርጎ፣ ‹‹ፋዘር እሱ ተረት ለእኔ አይሠራም፡፡ እኔ እኮ ቅድም በነገሩን ተረት ውስጥ ያሉት ደንቆሮ አህያና ጅላጅል ነብር አይደለሁም፡፡ እርስዎ በደንብ ቀምመው እንደ ነገሩን በአንበሳ ፍርድ መሠረት የምመራ የገባኝ የአራዳ ልጅ ነኝ፡፡ ማትሪክ ማለፍ አቅቶኝ ለዲግሪ ባልበቃም እንደ ነገሩ ዲፕሎማ አለችኝ፡፡ ያቺ ዲፕሎማ ደግሞ ከዘንድሮ ፒኤችዲ እንደምትሻል ስነግርዎት በታላቅ ኩራት ነው…›› እያለ ሲነግራቸው፣ ‹‹ወዳጄ አንተ እንደ ልቡ አዳሪ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ምንም እንኳ ባልከው ሙሉ በሙሉ ባልስማማም ንቁ መሆንህን ግን ተረድቻለሁ…›› ሲሉ ታክሲያችን ዳር ይዛ እየቆመች ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎን በሩን ከፈተው፡፡ የአዲስ ዓመት ማግሥት አሳረኛ ወጎቻችን በዚህ መሠረት ተጠናቀው በየተራ እየወረድን ተሰነባብተን ወደ ጉዳያችን እያመራን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት