Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘመኑን የዋጀ የሕንፃ ዲዛይን ያስፈልጋል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የረዥም ሕንፃ ዲዛይን እያደገ፣ እየዘመነ መምጣቱን፣ የሕንፃ ዲዛይን ሥራ ከገንዘብ ጨረታ ውጪ፣ በውድድር ጥራት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ተገለጸ፡፡ ይህ የተገለጸው ቅዳሜ ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ‹‹ግሎባል ኢትዮጵያ ባንክ›› በአዲስ አበባ ከተማ የፋይናንስ ተቋማት መንደር እየተባለ በሚጠራው ሠንጋ ተራ አካባቢ የሚያስገነባውን ከ50 ወለል በላይ ያለው መንትያ ሕንፃ ዲዛይን አሸናፊ ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ ነው፡፡

ባንኩ የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ ለመገንባት የሚያስፈልገውን ዲዛይን ተወዳዳሪዎች እንዲመርጥ የተሰየመው የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርክቴክቸራል መምህር ዘገየ ቸርነት (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፣ በአሁኑ ወቅት የአገራችን አርክቴክቶች የሕንፃ ዲዛይን ሥራ ዕድገት እየታየበት ነው፡፡  

‹‹በዚህ ውድድር እንዳስተዋልነው የረዥም ሕንፃ ዲዛይን ጥበብ በአገራችን እያደገ መምጣቱን ለመገንዘብ ችለናል፤›› በማለት እንደ ባለሙያ አስተያየታቸውን የሰጡት ዘገየ (ዶ/ር) አያይዘውም፣ ስለሕንፃና ስለከተማ ልማት ያለውን አስተሳሰብ እየተሞረደና እያደገ እንደመጣ በተለያዩ የውድድሮች መታዘብ እንደተቻለና የሕንፃ ዲዛይን ሥራ እየተሻሻለና እያደገ መምጣቱን፣ በዚህ ውድድር ላይም ማስተዋላቸውንም አመልክተዋል፡፡ በአጠቃላይ እንደ አገር ሲታይ በሕንፃ ጥበብ ገና እየተንደረደርን ያለን ብንሆንም፣ በፍጥነት እያደገ የመጣው የከተሜነት ሁኔታውን እየለወጠ መምጣቱን፣ ነገር ግን  የግንባታ ጥበብን በፍጥነት ማሳደግ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ዲዛይን ለመሥራት በወጣው ጨረታ፣ ለመወዳደር 18 ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ እነዚህ ኩባንያዎች ይዘው የቀረቡት ዲዛይን አሁን ያለውን የኢትዮጵያውያን የዲዛይን ሥራ አቅም ያሳየና ተስፋ ሰጪ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የዋና መሥሪያ ቤት የሕንፃ ዲዛይን ሥራ ጨረታን በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት አወዳድሮ የመጨረሻውን አሸናፊ ለመለየት የዳኞች ኮሚቴ ብዙ ስለመፈተኑም ዘገየ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ትልልቅ የሕንፃ ግንባታዎች ገለልተኛ በሆኑ በዘርፉ ምሁር እንዲዳኝ በማድረግ ባንኩ የተወጣውን ኃላፊነት ያደነቁት ባለሙያው፣ የሕንፃ ዲዛይኖችን እንዲህ ባለው ሁኔታ አወዳድሮ መምረጥ ለአገሪቱ የኮንስትራክሽን ግንባታ ጥራትና ደረጃ መጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በዓለም ላይ በተለይ ባደጉት አገሮች መሠረታዊ በሚባል መንገድ ትልልቅ ሕንፃዎችና የሕዝብ መገልገያ ሕንፃዎች ዲዛይን መረጣ በውድድር ብቻ የሚካሄድ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያም ይህ እንዲሆን በተደጋጋሚ ሐሳብ ሲቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራርም በግዴታ ሊተገበር ይገባል የሚለውን እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

ባንኩ በሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት እሳቸው የሚመሩት የዳኞች ኮሚቴ ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ሚስጥራዊነቱን ጠብቆ ባካሄደው ምዘና የግሎባል ኢትዮጵያ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ዲዛይን ሥራ ጨረታን ያሸነፈው አማካሪ ድርጅት በዕለቱ ይፋ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በዳኞች ግምገማ ጨረታውን በማሸነፍ አንደኛ የሆነው ኢንላፍ አማካሪ ድርጅት ነው፡፡  

በሁለተኛ ደረጃ የተመረጠው ዲዛይን ደግሞ ኤል አውቶ ኢንጂነሪነግ ያቀረበው ዲዛይን ሲሆን፣ ሦስተኛ ደረጃ በመውጣት ዕውቅና የተሰጠው ደግሞ በጅዳው ኮንሰልቲንግ ያቀረበው ዲዛይን ነው፡፡

በዕለቱ አሸናፊ የሆነው ኢንላፍስ ኮንሰልቲንግ ከተቋቋመ ከ10 ዓመታት በላይ ሲሆን፣ እንዲህ ያለውን ግዙፍ የሕንፃ ዲዛይን ሥራ ሲያሸንፍ የመጀመርያው ነው፡፡

የዚህ ዲዛይን ዋና አርክቴክቸር የሆኑትና የሆሴ የኢንላፍስ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማናጀር ፍቅረ ሥላሴ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተማ  በግንባታ ላይ የሚገኙ የተለያዩ የሪል ስቴትና ትልልቅ ሕንፃዎችን ዲዛይን ሠርቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሆሴ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማኅበር የሚያስገነባው ከምድር በታች አምስት ከምድር በላይ ደግሞ 23 ፎቆች ያሉት ሕንፃ (አሁን በግንባታ ላይ) አንዱ ነው፡፡ ከእነዚህም ሌላ የፀሜክስ አፓርትመንት፣ የግራንድ ቪው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የንፋስ ስልክ ሕንፃ ዲዛይኖችም በዚሁ አማካሪ ድርጅት የተሠሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በባለሙያዎች ዳኝነት የታገዘ እንዲህ ያለው የሕንፃ ዲዛይን ሥራ ጨረታ መበረታታት ያለበት ስለመሆኑ የገለጹት ፍቅረ ሥላሴ፣ እንዲህ ባለው ውድድር አሸናፊ ሆኖ መውጣት እጅግ አስደሳች መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

በውድድር ላይ የተመሠረተ የዲዛይን ሥራ እጅግ ጠቃሚ ስለመሆኑም ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡን ፍቅረ ሥላሴ (ኢንጂነር)፣ በተለይ ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በማስቀረት ረገድም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ለሕዝብና ለትውልድ ደኅንነት አስበህ መሥራት ካስፈለገ ውድድር ሊያበረታ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ወሳኝ ጉዳይም ቢሆን ውድድር ያስፈልጋል ያሉት ፍቅረ ሥላሴ፣ መለመድና በሕግም ሊደገፍ የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ስለዚህ ወሳኝ የሚባሉ ፕሮጀክቶችን ገንዘብ ከጨረታ ከአካሄድ ወጥተን ወደ ውድድር መምጣትን በዲዛይን ጨረታ መልካም የተባለው ዲዛይን አሸንፎ የሚሠራበት አግባብ መኖር አለበት፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ሕንፃ አስገምጋሚዎችም እየተገነቡ ያሉት ሕንፃ ረዣዥም ነው፡፡ ረዣዥም ሕንፃዎች ሲሠሩ ደግሞ ብዙ ነገሮች ስለሚመሳሰሉ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍም ውድድር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ውድድርን መሠረት አድርገው የሚሠሩ ሥራዎች ደግሞ በዋጋም ሆነ በግልጋሎት ትርፋማ የሚያደርግ ስለመሆኑ የገለጹት ፍቅረ ሥላሴ (ኢንጂነር)፣ ስለዚህ አሠሪዎች ከመንግሥት ጀምሮ የግልም ሆነ የኮርፖሬት ድርጀቶች ውድድር እንዲያዳብሩ እንመክራለንም ብለው፣ በኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበርም በኩል ቢሆን ውድድርን በጣም እንዲበረታታ የሚያደርግና የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ትልልቅ ፕሮጀክቶች የዲዛይን ውድድር አስገዳጅ እንዲሆን ቢደረግስ ለሚለው ጥያቄ ተገቢ ስለመሆኑም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የግሎባል ኢትዮጵያ ሕንፃ ዲዛይን ከሌሎች የፋይናስ ተቋማት ለየት ብሎ ተሠርቷል በሚል ከሚጠቀሱለት መካከል አንዱ ሕንፃው የሒሊኮፕተር ማሳረፊያ እንዲኖረው ተደርጎ ተሠርቷል፡፡

በዚህ ሕንፃ ላይ የሔሊኮፕተር ማሳረፊያ ተካትቶ የተሠራው እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ አቶ ፍቅረ ሥላሴ ገልጸዋል፡፡ ይህንንም የዲዛይኑን ሥራ ሕግጋቶችን ታሳቢ በማድረግ በዲዛይኑ እንዲካተት የተደረገ መሆኑ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ሕንፃዎች የግድ የሒሌኮፕተር ማሳረፊያ እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡ ይህም ዋነኛ ጠቀሜታው ከሕንፃዎች ርዝማኔ አንፃር አደጋ ቢደርስ በሕንፃ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በሔሊኮፕተር ለማጓጓዝ እንደሚያመች ነው፡፡ ባንኩም ለራሱ አገልግሎት ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋነኛ ጠቀሜታው ከደኅነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚሁ የሔሊኮፕተር ማሳረፊያ ጋር በተያያዘም ሰዎች እስኪጓጓዙ ድረስ በልዩ ሁኔታ የሚቆዩበት ቦታዎችም አብረው በዲዛይኑ መካተታቸውንም ከማብራሪያቸው ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

በዚህ ጨረታ ሒደት ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ጥራት ያለው ነገር ለመሥራት እንዲህ ያለውን መንገድ መጠቀማቸውን ነው፡፡ የዲዛይን መረጣው በሕንፃ ዲዛይን ግምገማ ሰፊ ልምድና ዕውቀት ያላቸውን ገለልተኛ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ዳኞችና አማካሪዎች በማደራጀት መካሄዱ በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

ባንኩ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ከአዲስ አበባ አስተዳደር በተረከበው 5,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሕንፃው የሚገነባ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ግንባታውም መንትያ ሕንፃ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡

ባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የምድር ወለልን ጨምሮ ከ50 ወለሎች በላይ እንደሚኖረው ታስቦ የተሠራ ሲሆን፣ ሁለተኛው ሕንፃ ደግሞ 12 ወለሎች ይኖሩታል፡፡ በሕንፃ ግንባታ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ግንባታው በሚጠቀማቸው የሕንፃ ቴክኖሎጂዎች፣ እንዲሁም በሚሰጧቸው አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንደሚሆን እርግጠኞች ነን ብለዋል፡፡

ባንኩ ባለፉት 11 ዓመታት ብዙ ውጣ ውረድ ያሳለፈ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው፣ ሕንፃው በተመረጠው ዲዛይን መሠረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ግንባታ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙትና ለዲዛይኑ አሸናፊ ኩባንያ ሽልማት የሰጡት የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ መስፍን ነገዎ (ኢንጂነር) ለየት ባለመንገድ የተካሄደውን የዲዛይን ውድድርና የመረጣ ሒደት አድንቀዋል፡፡

ለኢኮኖሚ ዕድገት የፋይናንስ ዘርፉ አንድ ምሰሶ መሆኑን የገለጹት ሚኒስቴር ደኤታው፣ የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የሕንፃ ግንባታ ሒደት የፋይናንስ ተቋማት መንደር እንዲመሠረትና የፋይናንስ ተቋማት በአንድ ዲስትሪክት ሥር እንዲካተቱ መንግሥት የጀመረው ጥረት አካል ሲሆን ሒደቱንም የሚያፋጥን ነው ብለዋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ አጠቃላይ የባንኩን ወቅታዊ የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፣ ባንኩ በተለያዩ የሥራ መስኮች የጣላቸው መሠረቶች በአሁኑ ወቅት ፍሬ እያፈራ በመምጣቱ ባንኩ በፈጣን ዕድገት ላይ የሚገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ያለዚያም በምሳሌነት የጠቀሱት ባንኩ በተጠናቀቀው 2015 የሒሳብ ዓመት 820 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ያገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በ2016 የሒሳብ ዓመትም ባንኩ ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለማትረፍና የባንኩ የተከፈለ ካፒታል አምስት ቢሊዮን ብር እንደሚሆን የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በዕለቱ በመድረኩ ላይ ከተገኙት የባንኩ ዋና መሥራቾች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳት የነበሩት አቶ አባተ ኪሾ እንዳመለከቱትም፣ ዘንድሮ ባንኩ ያተረፈው ትርፍ አይተነው የማናውቀው ነው ብለውታል፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ መሆኑን የገለጹት አቶ አባተ፣ የሕንፃው ግንባታ በቶሎ እንዲካሄድ የሁላችንንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ሌላው መሥራችና የባንኩ ከፍተኛ ባለአክሲዮን የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው፣ የሕንፃ ግንባታውን ለማካሄድ የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ባንኩ በአገር ብቻ ሳይወሰን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል የሚያስችለውን የካፒታል የማሰባሰብ ሥራውንም አጠንክሮ መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል፡፡   

በሌሎች የባንኩ ቁመናን የሚያመለክተው የዋና ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ፣ ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ የሀብት መጠኑ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡ የባንኩ ደንበኞች ቁጥርም ከአንድ ሚሊዮን በላይ መድረሱንም አመልክተዋል፡፡

የባንኩን አቅም ለማሳደግና በአዲስ አሠራር ተወዳዳሪነቱን ለመጨመር ከወሰናቸው ውሳኔዎች መካከል የባንኩን ስያሜና መለያ በመቀየር ወደ ሥራ መግባቱ ነው፡፡ ‹‹ቀድሞ ሲጠቀምበት የነበረውን፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ ወደ ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ባንክ ቀይሯል፤›› ያሉት ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ባንኩ ከሚሰጣቸው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ አገልግሎት አንፃር የሚመጥንና ባስቀመጡት ስትራቴጂ ዓላማ አንፃር አብሮ የሚሄድ የምልክት ለውጥ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

ይህንንም ማሳካት መቻላቸው ‹‹ዛሬ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም የያዘ የመጀመርያው የግል ባንክ ለመሆን ችለናል፤›› በማለት፣ ‹‹ከምንወዳት አገራችን ስያሜ ከመጠራት በላይ ምን የሚያስደስት ነገርስ ይኖራል? ከስምም ባሻገር ከእንዲህ ባለው ጉዟችን የአገራችንንም ትልቅነትና ከፍታ በሚመጥን መልኩ እንዲሆን ጥረት አናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡ 

ይህ ባንኩ ካካሄዳቸው ሁለንተናዊ ለውጦች ባንኩን በአዲስ ገጽታ፣ በአዲስ ቀለምና የንግድ ምልክት ወደ ገበያ ገብቶ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ፣ በኅብረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው፣ ከጊዜው ጋር በመዘመን የለውጥና የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳሉ ማሳያም መሆኑን ዋናው ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

ግሎባል ኢትዮጵያ ባንክ በአሁኑ ወቅት ከ2,300 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን በመላ አገሪቱ የከፈታቸው ቅርንጫፎች 152 ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች