የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ለአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በ9.6 ቢሊዮን ብር የሚተገበር የአሥር ዓመት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከግብርና ሚኒስቴርና ከክልሉ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የግብርና ስትራቴጂ የመጀመርያ ሰነድ ለውይይት ያቀረበ ሲሆን፣ በቅርቡ ለክልሉ እንደሚያስረክብ ገልጿል፡፡ ክልሉ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ተዘጋጀ የተባለው ስትራቴጂ በእንስሳት ዕርባታና በእርሻ ልማት ዘርፍ አሁን የሚታየውን ሁሉን አቀፍ ችግር በማሻሻል፣ የምርት መጠንና ጥራትን ከእጥፍ በላይ የሚያሳድግ ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ማንደፍሮ ንጉሤ አንደገለጹት፣ በኋላቀር አሠራር የተጠመደውን አጠቃላይ የክልሉን የግብርና ሥራ ከመሠረቱ ሊቀይር የሚችል ስትራቴጂ ነው፡፡ በተጨማሪም የምርት መጠንን በማሳደግ ለገበያ የሚውሉ ምርቶችን ጥራትና ብዛት በልዩ ሁኔታ ይጨምረዋል ብለዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 95 በመቶ ሕዝብ በግብርና ሥራ የተሰማራ ቢሆንም ባለበት የባለሙያ እጥረት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የገበያ ትስስር አለመኖርና የብድር አቅርቦት ውስንነት በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ እየተጠቀመ አለመሆኑን የገለጹት የክልሉ ፕሬዚዳንት ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ለዚህም በዘልማድ የሚተገበረውን የግብርና ሥራ ወደ ሜካናይዝድ በመለወጥ፣ አሁን ያለውን ምርት በብዙ እጥፍ ለማሳደግ ይረዳ ዘንድ የአሥር ዓመቱ ዕቅድ ተዘጋጅቶ በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡
ከቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሕዝበ ውሳኔ ተለይቶ ከተመሠረተ ሁለት ዓመት ያልሞላው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የአገሪቱን የቡናና የሻይ ምርት በትልቅ ድርሻ የሚሸፍን መሆኑ ይነገራል፡፡ ክልል ሆኖ ከተቋቋመ ወዲህ ምንም ዓይነት የገበያ ትስስር ያልተፈጠረለት በመሆኑ የሚመረተው ምርት በተገቢው ሁኔታ ወደ ገበያ እየቀረበ አለመሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ክልሉ በ2015 ዓ.ም. 51 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡን፣ አዲሱ ስትራቴጂ ይህንን ዓመታዊ መጠን ከሁለት እጥፍ በላይ ማድረስ ያስችለዋል ተብሏል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በተደጋጋሚ የሚጥለው ዝናብ 70 በመቶ የሚሆነው መሬት አሲዳማ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ፣ ምርታማነትን እንዳሽቆለቆለው ተገልጿል፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት እንደገለጹት፣ የተዘጋጀውን የግብርና ዕቅድ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ ለማስገባት ታስቧል፡፡ ዕቅዱን ለማስፈጸም የተጠቀሰው ገንዘብ ከባለሀብቶች፣ ከዞንና ከወረዳ የድጋፍ በጀት፣ ከለጋሽ ድርጅቶች፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት፣ ከፌዴራልና ከክልሉ መንግሥት ድጋፍ ይሸፈናል ብለዋል፡፡
ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ቢሮ ከመቀመጥ ወደ ማኅበረሰቡ በመውረድ ቀጥታ አርሶ አደሩን ማነጋገር፣ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ለዕቅዱ መሳካት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡