Monday, December 2, 2024

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው ፈጣኑ የ5ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት ነው፡፡ በታላቅ ጉጉት ይጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ፕሮጀክት የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት መሳካቱ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚ አገሮች አንዷ የሚያደርጋት ፈጣኑ የ5ጂ አገልግሎት ዕውን መሆን መጀመር አዲሱን ዓመት በተነቃቃ መንፈስ ለመጀመር ይረዳሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ መልካም ዕሳቤም ሆነ ተስፋ ግን በበርካታ ሥጋት ፈጣሪ ወጀቦች የተከበበ መሆኑ ደግሞ ያሳስባል፡፡ እንደተለመደው ‹‹መልካም አዲስ ዓመት›› ተብሎ አዲሱ ዓመት በተስፋ ቢጀመርም፣ ብርቱ የሰላም ዕጦትና የከፋ የኑሮ ውድነት ወዲህና ወዲያ የሚያላጋቸው ኢትዮጵያውያን ሥጋት ውስጥ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያን ውሎና አዳር የሚከታተሉ የቅርብ ጎረቤት አገሮችም ሆኑ፣ ሌሎች በርቀት ያሉ ወዳጆች ጭምር የኢትዮጵያ ሰላም ማጣት ያሳስባቸዋል፡፡ የአገራቸውን ጉዳይ የሚከታተሉ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጭንቀትና ሥጋትም እየከበደ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ ሆና በዓለም አደባባይ ስትታይ ከስኬት በስተጀርባ የመሸጉ ችግሮች ገመናዋን ያጋልጣሉ፡፡ ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት ሲያቅታቸው ሕግና ሥርዓት እንደሌለ ጉልህ ማስረጃ ይሆናል፡፡ በየቦታው ሰዎችን እያገቱ የሚገድሉ ወይም ከአቅም በላይ የሆነ ክፍያ የሚጠይቁ ሕገወጦች ሲበዙ፣ የሕግ የበላይነት የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ማላገጫ ነው የሚሆነው፡፡ ዜጎች ከሕግ አግባብ ውጪ ሲያዙም ሆነ ሲታሰሩ፣ በየቦታው ግጭት ሲስፋፋና ሰላም ሲጠፋ፣ በሰላም ዕጦት ምክንያት የምርቶች አቅርቦት ሲስተጓጎልና የኑሮ ውድነቱ ከሚቋቋሙት በላይ ሲሆን፣ በመንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ዜጎች በአግባቡ መስተናገድ ሲያቅታቸው፣ የአገርና የሕዝብ ሀብት የሚዘርፉ ሌቦች ጠያቂ አጥተው አገር ሲያራቁቱ፣ ጉቦ በግላጭ መጠየቅ በየቦታው እንደ ወረርሽኝ ሲስፋፋ፣ ሕገወጦችና ሥርዓተ አልበኞች የመንግሥት ተቋማትን ሲፈነጩባቸው፣ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ደንታ የሌላቸው ሲበዙና ሌሎች እኩይ ድርጊቶች በስፋት ሲተስተዋሉ ስለሕግ የበላይነት ለመነጋገር እያዳገተ ነው፡፡

አገር በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች ጥልቅ በሆኑ ምርምሮች ታግዛ በአዋጭ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ስትመራ ከ120 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ሕዝብ ምርታማ ማድረግ እንደሚቻል ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የብሔርና የእምነት ልዩነቶችን በፀጋ በማስተናገድ፣ አንድ አገርና አንድ ሕዝብ በመሆን በአንድነት ሠርቶ ማደግ እንደማያዳግትም ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በተለይ ከ70 በመቶ በላይ ወጣት የሰው ኃይልና በበርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች አገር ሆና፣ ዕርባና ቢስ በሆኑ ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች ምክንያት ብቻ የሰላምና የምግብ ደሃ መደረጓ ያስቆጫል፡፡ ከሥልጣንና ከሚያስገኘው ጥቅም በላይ የአገር ብሔራዊ ደኅንነትና የሕዝብ ሰላም ቅድሚያ ሊሰጠው ሲገባ፣ በአይረቤ ፖለቲካዊ ዕሳቤዎች ምክንያት የማደግ ትልቅ ተስፋዋ እየደበዘዘ ነው፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በታላቁ የህዳሴ ግድብና በቴሌኮም ዘርፍ የሚታየው ብሩህ ተስፋ፣ በሌሎች ዘርፎች በስፋትና በጥልቀት ከተሠራ ትልቅ ዕምቅ አቅም እንዳለ በግልጽ ያመላክታል፡፡ ነገር ግን በጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት ውስጥ በመቀርቀር ሰፊውን አገራዊ ራዕይ ለማየት አለመፈለግ ከባድ ኪሳራ እያስከተለ ነው፡፡

ለአገር የሚጠቅሙ ታላላቅ ምሁራን ተመጣጣኝ ክፍያ ስለማያገኙ በድህነት ተቆራምደው ይኖራሉ፡፡ አጋጣሚውን ያገኙ ደግሞ ለአገር የሚጠቅም ዕውቀታቸውን በተሻለ ክፍያ ለባዕዳን አገሮች ይሸጣሉ፡፡ በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚመረቁ ወጣቶች ውስጥ በጣም ብዙዎቹ በጉልበት ሥራዎች ውስጥ ተሰማርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሾፌርነት፣ በጥበቃ፣ በተላላኪነት፣ በአስተናጋጅነት፣ በሊስትሮነትና በመሳሰሉት የተሰማሩ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ አገር በሌለ አቅም አስተምራ ለወግ ማዕረግ ያበቃቻቸው ወገኖች በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲገኙ፣ ምን ያህል ዕውቀት እየባከነ እንደሆነ ለመረዳት አዳጋች አይሆንም፡፡ ውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሊገኝ የሚችለው የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ባክኖ ቀርቷል፡፡ በርካታ የእስያ፣ የላቲንና የአፍሪካ አገሮች ከሃዋላ ገቢ በተጨማሪ በዳያስፖራዎቻቸው ዕውቀት የት እንደደረሱ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ የተማረ የሰው ኃይሏን ሳትጠቀምበት በግዥ ቴክኖሎጂ ብቻ የትም መድረስ አትችልም፡፡ በሳይንስና በቴክኖሎጂ በዳበረ የተማረ የሰው ኃይል ሳይጠቀሙ ያደጉ አገሮችም የሉም፡፡ ሰላም በማስፈን ይህንን የተማረ ኃይል በፍጥነት ማስተባበር ካልተቻለ ችግሩ የከፋ ይሆናል፡፡

በአገር ጉዳይ ሁሉም ዜጎች እኩል ተሳታፊ አለመሆን የሚያስከትለው ቅራኔ አድጎ ወደ ግጭት ሲያመራ፣ አገር የማያበሩ ችግሮች መፈልፈያ እንደምትሆን ከኢትዮጵያ በላይ እማኝ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ዜጎች በሕግና በተፈጥሮ የተረጋገጡላቸውን መብቶቻቸውን ከሚያጣጥሙባቸው መንገዶች አንዱ፣ ሐሳብን በነፃነት መግለጽና በፈለጉት የፖለቲካ ፓርቲ መደራጀት ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰጪና ከልካይ ሳይኖር ሁሉም ዜጎች በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ መብቱን ማጣጣም የሚፈልግ ማንም ዜጋ ሕግ የማክበር ግዴታም እንዳለበት ይረዳል፡፡ መብትና ግዴታ ተመጣጣኝ ሆነው በሰላም መኖር የሚቻለው፣ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ሁሉም ዜጎች አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ሲኖራቸው ነው፡፡ በዜግነትም ሆነ በብሔር መደራጀት የዜጎች መብት ሲሆን፣ አንዱ ለሌላው መብት ዕውቅና ሰጥቶ በነፃነት የሚፎካከሩበት ምኅዳር መፍጠር ይጠቅማል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው የጉልበት መንገድ አገርን የግጭት አውድማ ነው የሚያደርጋት፡፡ ከግጭት ውስጥ መውጣት ሳይቻል መልማትም ሆነ ማደግ አይቻልም፡፡ ብልጭ ድርግም የሚል የዕድገት ማመላከቻ ካለም አሳሳች ነው፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ አውራ ጎዳና ባለሥልጣንና መሰል በብቁ አመራሮችና ባለሙያዎች የተደራጁ መንግሥታዊ ተቋማት እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ እነዚህ ተቋማት በአፍሪካ አኅጉር ጭምር ምርጦች እንደበነሩም አይዘነጋም፡፡ ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት የእነሱን ፈለግ ተከትለው ምርጥ ለመባል ይተጉ እንደነበር ይነገራል፡፡ አሁንስ ሲባል በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን በማትረፍ በየዓመቱ ሽልማቶችን ከሚያገኘው አየር መንገዳችን በስተቀር፣ የሌሎቹ ተከድኖ ይብሰል ቢባል ይቀላል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢትዮ ቴሌኮም አበረታች እመርታ እያሳየ ቢሆንም፣ የሌሎቹን ግን በነበር ከመተረክ ውጪ ዝም ማለት ይቀላል፡፡ አገር ሰላም አግኝታ ወደ ቀደመ ክብሯ መመለስ የምትችለው፣ ያለፈውን በማጣጣልና በማራከስ እንዳልሆነ ከዘመነ ደርግ ወዲህ ያለው የጥፋት ታሪክ ይመሰክራል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ብቻ እንደሆነ ይታወቅ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ስክነትና መደማመጥ ከጎደለው ፖለቲካ መላቀቅ የግድ ነው

በአስረስ ስንሻው ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች ስንል ምክንያት አለው፡፡...

የአዲስ አበባ አስተዳደር ለትራንስፖርት ችግር ጩኸታችን ጆሮ ይስጥ!

የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግር ደጋግመን እንድናነሳ ግድ የሚሉ...

የሕግ የበላይነት የመጨረሻው ምሽጋችን ይሁን

በገነት ዓለሙ የሕግ የበላይነት ማለት ዛሬ ጭምር አልገባን እያለ የሚያስጨንቀንን...

ካፒቴን መሐመድ አህመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ እመርታ የመሩ (1924-2017)

ኢትዮጵያ ወደ ምዕት ዓመት የሚጠጋ የካበተ የንግድ አቪዬሽን ታሪክ...

ባንኮች በሚሰጡት ዓመታዊ ብድር ላይ የተጣለው ገደብ ሊሻሻል ነው

ባንኮች የሚያቀርቡት ዓመታዊ የብድር መጠን ከ14 በመቶ እንዳይበልጥ ገደብ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግጭት ቀስቃሽ አተካሮዎች አገር እያደሙ ነው!

ኢትዮጵያ ማባሪያ ካጣው ግጭት ውስጥ በፍጥነት የሚያወጣት መፍትሔ ማፍለቅ እንደማያዳግት ማንም በቀላሉ የሚገነዘበው እውነት ነው፡፡ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› እንደሚባለው፣ ለብዙዎቹ ግጭቶች ምክንያት የሆኑ...

ሰላማዊ ዜጎችን ከጥቃት መከላከል ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው!

በሰላማዊ ዜጎች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ ንብረት ማውደም፣ ዕገታና መሰል ድርጊቶች በተፃፃሪ ጎራ ለተሠለፉ የፖለቲካ ተቀናቃኞች ሠርግና ምላሻቸው እየሆኑ ነው፡፡ በሴራ...

በጥናት ላይ ያልተመሠረተ ዘመቻ ብልሹውን የግብይት ሥርዓት አያፀዳውም!

ብልሹው የግብይት ሥርዓት ውስጥ ያለው ውጥንቅጥ የሚስተካከለው በሰዶ ማሳደድ ዘመቻ ሳይሆን፣ በሙያዊ ክህሎት በዳበረ ጥናት ላይ የተመሠረተ አሠራር ብቻ ነው፡፡ ይህንን ጥንቅቅ ያለ አሠራር...