Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበመጀመርያው የዓለም የጎዳና ሻምፒዮና የኦሊምፒክ አሸናፊዎች ይጠበቃሉ

በመጀመርያው የዓለም የጎዳና ሻምፒዮና የኦሊምፒክ አሸናፊዎች ይጠበቃሉ

ቀን:

  • የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዝርዝር ይፋ ሆኗል

ለመጀመርያ ጊዜ በሚከናወነው የጎዳና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ስድስት የዓለም ሻምፒዮኖችና አምስት የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቶች ይወዳደራሉ።

መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በላቲቪያ ሪጋ ከተማ የሚከናወነው የአምስት ኪሎ ሜትር ግማሽ ማራቶንና የማይል የጎዳና ውድድር የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናዎችን ጨምሮ፣ ከ347 በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

በማይል ውድድሩ የወቅቱ የሁለት ርቀቶች የዓለም፣እንዲሁም የኦሊምፒክ ሻምፒዮኗ ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዮንግ በጎዳና ሻምፒዮናው ከሚጠበቁ አትሌቶች ቀዳሚዋ ናት፡፡

ከሳምንታት በፊት በቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና በ5000 ሜትርና 1500 ሜትር ሁለት ወርቅ ያጠለቀችው አትሌቷ፣ በማይል ውድድሩ ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ተጠቅሳለች፡፡

በአንፃሩ ኬንያዊቷ በማይል ውድድሩ በቀላሉ ሊሳካላት እንደማይችልና ከፍተኛ ፉክክር እንደሚጠብቃት ተጠቁሟል፡፡

ምክንያቱም በዓለም ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ በ1500 ሜትር የብር ሜዳሊያን ያጠለቀችው ድርቤ ወልተጂና ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ፍሬወይኒ ኃይሉ ከፍተኛ ፉክክር ያሳያሉ ተብሏል፡፡

ሌላዋ በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ክብረ ወሰን የጨበጠች ውቢት ሪሲቾፕከቼ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ነች፡፡ ሒሩት መሸሻ በሴቶች በማይል ውድድር ከድርቤና ፍሬወይኒ ጋር የምትሠለፈው ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ናት፡፡

የዓለም አትሌቲክስ በሻምፒዮናው የሚካፈሉ አትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በወንዶች የማይል ውድድር መልኬ ነህ አዘዞና ታደሰ ለሚ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ናቸው፡፡

በሴቶች የአምስት ኪሎ ሜትር ውድድር የቡዳፔስት 10 ሺሕ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቷ እጅጋየሁ ታዬ፣ ለምለም ኃይሉና መዲና ኢሳ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ናቸው፡፡

በወንዶች 5 ኪሎ ሜትር ውድድር በሪሁ አረጋዊ፣ሐጎስ ገብረ ሕይወትና ዮሚፍ ቀጄልቻ እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት በቡዳፔስቱ ደካማ ውጤት ያመጡት አትሌቶች በዚህኛው ሻምፒዮና ውጤቱን ይቀለብሳሉ የሚል ግምት አለ፡፡

በዓለም ሻምፒዮናው በሞቃታማው የአየር ሁኔታ ምክንያት ውጤቱን ማምጣት እንዳልተቻለ ሲጠቅሱ ከነበሩ አትሌቶች መካከል ‹‹በጎዳና ውድድሩ እንክሳለን›› በማለት ቃል የገቡ ነበሩ፡፡

በመጀመርያ የጎዳና ዓለም ሻምፒዮና በሴቶች ግማሽ ማራቶን ጽጌ ገብረሰላማ፣ ያለምገነት ያረጋል፣ ፈታው ዘራይና መጻዋት ፍቅር ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ናቸው፡፡

በወንዶች ግማሽ ማራቶን ጀማል ይመር፣ ፀጋዬ ኪዳኔ፣ድንቅ ዓለም አየለና ንብረት መላክ ይጠበቃሉ፡፡

በሻምፒዮናው በዓለም ፈጣን ሰዓት ካላቸው አራት አትሌቶች ሦስቱ በ5 ኪሎ ሜትር ውድድር እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡ እነዚህም የ5 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቱ በሪሁ አረጋዊ፣ዮሚፍ ቀጄልቻና ኬንያዊው ኒኮላስ ኪፕከር ናቸው፡፡

መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሚካሄደው ውድድር ለመዘጋጀት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስድስት አሠልጣኞችን መርጦ ዝግጅቱን ማክሰኞ መስከረም 7 ቀን እንደሚጀምር ገልጿል፡፡

የዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ

የዘንድሮ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ከግንቦት ወር እስከ መስከረም ድረስ 13 ውድድሮች በተለያዩ ከተሞች ሲከናወን ቆይቷል፡፡ የመጨረሻውና የማጠናቀቂያው ውድድር በኦሪጎን ዩጂን ከተማ መስከረም 5 እና 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ይከናወናል፡፡የዓለም ከዋክብት በተሰባሰቡበት በዚህ ውድድር ላሸናፊነት ለሚበቁት የዳይመንድ ሊግ ዋንጫና የ30,000 ዶላር ሽልማት ተዘጋጅቷል።

በአጠቃላይ 32 አትሌቶች በሰበሰቡት ነጥብ ለፍፃሜ የደረሱ ሲሆን፣ 15ቱ መስከረም 5፣ ቀሪዎቹ 17ቱ መስከረም 6 ውድድራቸውን ያደርጋሉ፡፡ አብዛኛዎቹ አትሌቶች ለፍፃሜ የደረሱት በ13 ውድድሮች ላይ ባስመዘገቡት ነጥብ አማካይነት ነው፡፡

በመጀመርያው ቀን ውድድር ለፍፃሜ ከደረሱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ሲምቦ ዓለማየሁና ዘርፌ ወንድማገኝ ይገኙበታል፡፡

በሴቶች 1500 ሜትር ድርቤ ወልተጂ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ሒሩት መሸሻና ወርቅነሽ መለሰ ይጠበቃሉ፡፡ ብርቄ ኃየሎም ሌላዋ በርቀቱ ነጥብ ሰብስባ ለፍፃሜ መድረስ የቻለች አትሌት ናት፡፡

በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ሳሙኤል ፍሬው፣ አብርሃም ስሜና ጌትነት ዋለ ይሳተፋሉ፡፡ በርቀቱ የቡዳፔስት ሻምፒዮኑ ሞሮካዊው ሶፍያን ኤል ባካሊና የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቱ ኢትዮጵያዊ ለሜቻ ግርማ አለመኖራቸው ለሌሎች ዕድል ከፍቷል፡፡

በመጨረሻው ቀን መርሐ ግብር መሠረት በሴቶች 5000 ሜትር መዲና ኢሳ፣ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ለምለም ኃይሉ፣ ብርቄ ኃየሎም፣ጉዳፍ ፀጋይና እጅጋየሁ ታዬ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብለው ይጠበቃሉ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...