Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉሕዝባችን ውስጥ የጥርጣሬና የጥላቻ ስሜት እንዳይፈጠር እንጠንቀቅ

ሕዝባችን ውስጥ የጥርጣሬና የጥላቻ ስሜት እንዳይፈጠር እንጠንቀቅ

ቀን:

በመክብብ ንጋቱ

ለመላ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ እያልኩ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና ከማንኛውም ዓይነት ክፋትና ጠብ የምንርቅበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ አገራችንም ኢትዮጵያ ከገባችበት የግጭት አዙሪት ተላቃ ሁላችንም በእኩልነት የምንኖርባት፣ የምንሠራባት፣ ሀብት የምናፈራባትና የአፍሪካ ተምሳሌት እንድትሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከእነ መላ ሕዝቧ ሰላም ሆና ምኞታችን እንዲሰምር በተለይ መንግሥት፣ በሁሉም ጎራዎች ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞችና የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው በሙሉ በአዲስ ተስፋና በቅንነት መንፈስ እንዲነሱም አሳስባለሁ፡፡

ሁላችንም እንደምንረዳው ምትክ ከማይገኝላቸው የተወሰኑ ነገሮች ውስጥ አገርና እናት ይገኙባቸዋል፡፡ ስለዚህም እኛ አገርን እንደ እናት ስለምንቆጥር ኢትዮጵያን እናት አገሬ ብለን እንጠራታለን፡፡ እነዚህን ሁለቱን በሌላ ለመተካት እንኳን ብንሞክር በእንጀራ እናትና በሌላ በምንኖርበት አገር ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ እናትም አይደሉም፣ አገርም አይደሉም፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁለቱም የሚከበሩትና የሚታፈሩት በልጆቻቸው ነው፡፡ የልጆቻቸው ማንነት ህልውናቸውን ይወስነዋል፡፡

አገራችን ህልውናዋ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ለረዥም ዘመናት ልጆቿ እየተሰው እናታቸውን በክብር እዚህ አድርሰዋታል፡፡ ይህች አገር እዚህ ለመድረስ የተከፈለላትን መስዋዕትነት ለመግለጽ መሞከር ከንቱ ልፋት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ከእነ ክብሯ ባለችበት ለመቀጠል ተመሳሳይ ለመስዋዕትነት ዝግጁ የሆነ ትውልድ ያስፈልጋታል፡፡ ይህችን አገር ለዚህ ያበቋት ልጆቿ የተማሩ፣ ዴሞክራቶች፣ ፈላስፎች፣ ሀብታሞች፣ ባለዘመናዊ መሣሪያ ወይም ከአንድ ብሔር የተገኙ ብቻ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ዜጎች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር እኛ በሕይወት እያለን አገራችንን ጠላት አይደፍራትም፣ ድንበራችን አይቆረስም የሚል ፅኑ እምነት ነው፡፡

ያለፉት መንግሥታትም ቢሆኑ ይኼንን የፀና የሕዝብ አቋም ስለሚያውቁ፣ ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገው የጨቆኑትንና የገፉትን ሕዝብ ጭምር በማስተባበር ነው እዚህ ያደረሱት፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ኢትዮጵያዊነት ለግፉአን ሕዝቦች ጭምር ገዥ ሐሳብ ሆኖ ኖሯል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሰላም ጊዜ እየተናቆሩ፣ የውጭ ወራሪ ሲመጣ በአንድነት የመከላከልና የማጥቃት ኃይል አላቸው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ይኼ ስሜት የተፈጠረው ደግሞ ከማኅበራዊ ትስስራችን፣ ከዕድገታችንና ከታሪካችን ነው፡፡

አሁን አሁን ግን ነገሮች ተሻሽለው ይሁን ተበላሽተው ባይታወቅም፣ ይኼ ነባር የኢትዮጵያዊነት ስሜት የመቀዛቀዝ ባህሪ በበርካቶች ዘንድ አምጥቷል፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ አመራር ዘመን አገሪቱ በፌዴራል ሥርዓት በመዋቀር ክልሎች የየራሳቸውን መንግሥት መሥርተዋል፡፡ በየደረጃው የተዋቀሩት የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮች ደግሞ በሚያካሂዱት ሕዝባዊም ሆነ ሌሎች መድረኮች በሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ ለማስረፅ የሚጥሩት የክልላቸውን ልማት፣ የክልላቸው ሕዝብ እስከ ዛሬ ሲደርስበት ስለነበረው ጭቆና፣ ጭቆናውንም ያደረሰው ክፍል ሌላው ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ለዚህ ትኩረት ሰጥተው በጥንቃቄና በጥርጣሬ እንዲከታተሉ የሚያደርግ ጽንሰ ሐሳብ ያለው ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ቢሆን በአገራዊ የመንግሥት በጀት ድልድልና አልፎ አልፎ በሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላት ካልሆነ በስተቀር፣ አጠቃላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ የጋራ ሥነ ልቦና የመፍጠር ተነሳሽነቱ በእጅጉ የደከመ ነው፡፡ አሁን ያሉት ወጣቶችም ቢሆኑ ያደጉት በዚህ ሥርዓት ውስጥ በመሆኑ፣ ስለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ግንዛቤ የወቅቱን ሁኔታ እንዲያንፀባርቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለጋራ አገራችን፣ ስለሥነ ልቦናዊ ትስስራችንና ስለጋራ ድንበራችን ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንዲያገኙ አልተደረገም፡፡ ከአገራዊው ፍቅር ይልቅ ስለብሔራቸው፣ ስለክልላቸው፣ ስለቋንቋቸውና ስለባህላቸው ብዙ እንዲጨነቁ ሆነው ነው የተቃኙት፡፡ መደበኛም ሆነ ኢመደበኛ ትምህርታቸውን በሚመለከት የተቀረፀው ካሪኩለምም ይኼንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ ለአደባባይ ዲስኩር ማሳመሪያ ካልሆነ በስተቀር የአገራዊ አንድነት ጉዳይ ልብ ውስጥ ያለም አይመስልም፡፡

ብዙዎቹ የአዲሱ ትውልድ አባላት ትምህርታቸው፣ ኑሮአቸው፣ ዕድገታቸው፣ ሥራቸው፣ ጋብቻቸውና አካባቢያዊ ዕውቀታቸው በአብዛኛው በራሳቸው ክልል ውስጥ የታጠረ ነው፡፡ ስለጋራ አገራቸው ስለኢትዮጵያ ያላቸው ዕውቀት ግን የተወሰነ ነው ብል ያጋነንኩ ይመስለኛል፡፡ ባዶ ነው ለማለት ከብዶኝ ነው፡፡ ወቅቱ ለታሪክ ቦታ የማይሰጥና ታሪኩም ችግር ያለበት በመሆኑ ስለአገሪቱ የቀድሞ ታሪክ፣ ስለአንድነትና የኢትዮጵያዊነት መሠረተ ሐሳብ ለማስረፅ ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ትውልዱ በብዙ አካባቢዎች በኪሱ ይዞት በሚዞረው መታወቂያ ላይ እንኳ ብሔሩን እንጂ ኢትዮጵያዊነቱን አልተገለጸለትም፡፡ ብሔራዊ መዝሙሩን እንዲያውቅ አላደረግንም፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተቀላቅለው በአንድነት እንዲኖሩ ምቹ ሁኔታ ያልፈጠርንለት ትውልድ ነው ያለን፡፡ ይኼ ጉዳይ ሄዶ ሄዶ እኔ ለብሔሬ እንጂ ለኢትዮጵያዊነት አልታገልም ያሰኛል፡፡

ኢትዮጵያ ከሁሉም ክልሎችና ሕዝቦች የተፈጠረች ውሁድ አካል ናት፡፡ ለሁሉም ሕዝቦች ደግሞ ከየክልላቸው ይልቅ ይህች ውሁድ አካል ናት የምትጠቅማቸው፡፡ የሁሉም ኃይል አንድ ላይ ሲዋሀድ አገር ጠንካራ የሆነ መከላከያ ተፈጥሮ ትጠበቃለች፣ ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›› እንደሚባለው፡፡ የሁሉንም ሀብት አንድ ላይ ደምራ ብዙ ሀብት ስለሚኖራት በፍጥነት ኢኮኖሚያችን እንዲያድግ ታደርጋለች፡፡ አንዱ ጋ የሌለውን ካለው ዘንድ አምጥታ ታቀምሳለች፡፡ ሁሉም ገበያዎቿ ስለሆኑ ሁሉም ሸማቾቿ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ስትሆን ሁሉም ለየራሱ እየሆነ ነው የተቸገርነው፡፡ ይኼ አባባል ምናልባት አንዳንዶች እንደሚገምቱት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት አሳንሶ፣ በኢትዮጵያዊነት ላይ ብቻ እንድናተኩር የሚደረግ ጥረት መስሎ እንዳይታይ እሠጋለሁ፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር በአሁኑ ጊዜ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የብሔር ብሔረሰብን መብት ሙሉ በሙሉ ሳይሸራረፍ መጠበቅ የማይችል ማንኛውም አካል፣ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ ያለንበት ጊዜ እዚህ መደምደሚያ ላይ አድርሶናል፡፡

ብሔረሰባችንን ወደን ሳይሆን በተፈጥሮ አስገዳጅነት ያገኘነው ስለሆነ የትም አይሄድብንም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ግን በጊዜ ብዛትና በሒደት፣ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ወይም በስምምነት የፈጠርነው ስለሆነ፣ በተንኮለኞች ሴራ ወይም በሌላ ምክንያት የማንስማማ ከሆነ በቀላሉ የምናጣውና የሚቀርብን ነው፡፡ ስለዚህ ነው ጠላቶቻችን ለስላሳ ብልታችንን ፈልገው ሊለወጥ የማይችለውን የብሔረሰብ ማንነታችንን ምክንያት አድርገው፣ ለአደጋ ተጋልጧል ብለው ያሰቡትን የጋራ ማንነታችንን በየጊዜው ለመናድ የሚጥሩት፡፡ ከእነዚህ ሴረኞች በፍጥነት ሮጠን ማምለጥ አለብን፡፡ ሕይወትን ለማትረፍ ከሚያባርረው ሰው ይልቅ የሚሸሸው መፍጠን አለበት፡፡ ክልላችንን ይዘን ኢትዮጵያን ብናጣ ኪሳራ እንጂ ምን ትርፍ አለው?

አሁን አስፈላጊው ነገር ለልጆቻችን የምናወርሰው ኢትዮጵያዊነት ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት እናስብ፡፡ ወላጆች ሁሉንም ዓይነት ባህሪ ነው ለልጆቻቸው የሚያወርሱት፡፡ አንድ ልጅ ጠንካራ ወላጆቹ ያቆዩትን ሀብት ይወርሳል፡፡ የሚገርመው ነገር ልጁ ከወላጆቹ የሚወርሰው ሀብታቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ከወላጆች በሽታና ባህሪም ይወርሳል፡፡ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ ግላኮማና የመሳሰሉ በርካታ በሽታዎች ከወላጆች ሊተላለፉ የሚችሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ታዲያ እኛ በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች ለልጆቻችን የምናወርሰው ምን መሆን አለበት? በሽታችንን ጭምር ለልጆቻችን እንዳናወርሳቸው ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ለትውልድ የሚተላለፉ በሽታዎች በውስጣችን እንዳይቀሩ በቅድሚያ እኛ ታክመን መዳን አለብን፡፡ አሁን ያለነው የዘመኑ ትውልድ አባላት በፅኑ ታመናል፡፡ ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ቂመኝነት፣ ማናለብኝነት፣ ስግብግብነት፣ ኢትዮጵያን ያለ ማስቀደም፣ እንዲሁም የተዛባ የፈጠራ ታሪክ ሰለባ መሆንና የመሳሰሉት በሽታዎች በግልጽ ይታዩብናል፡፡ እነዚህን ሁሉ አሁኑኑ ታክመን ካልዳንን ቀጣዩን ትውልድ ተስፋ ቢስና አገር አልባ እናደርገዋለን፡፡

እኛ ከእነዚህ በሽታዎች ነፃ ሆነን በፍቅር ስንሞላ ጤነኛ፣ የሚዋደድና የሚከባበር ባለራዕይ ትውልድ እንተካለን፡፡ ይኼ ተተኪ ትውልድ ደፋሪ የለውም፡፡ በብሔሩ የሚኮራ፣ በኢትዮጵያዊነቱ የሚመካና የሚታፈር ይሆናል፡፡ ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን አዋህደን በልዩነታችንም ሆነ በአንድነታችን ተስማምተን እንኖራለን፡፡ የሁለቱንም ይዘት አጣጥመን አንዱን በማራቅ ወደ ሌላው ስንጠጋ፣ ሁለቱንም በእኩልነት አስተናግደን የተሟላች አገር ማቆየት እንችላለን፡፡ አንዱን ትታችሁ አንዱን ምረጡ ለማለት የሚያበቃ ምክንያት የለም፡፡ ለመሆኑ አሁን ያለውን ብሔረሰባዊ አከላለልና በተግባር እየታየ ያለውን ክልላዊና ፖለቲካዊ ይዘቶችን ወደ ጎን በመተው፣ ዘላቂ መፍትሔ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል? ምናልባት ከሃያ ዓመታት በፊት ቢሆን በወቅቱ ያስኬድ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ነው የወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ካለፈው ታሪካችን በላይ ወሳኝ የሚሆነው፡፡ ካለፈው እንማራለን፡፡ አሁን ላይ ሆነን የወደፊቱን እንተልማለን፡፡ የስልሳዎቹን የፖለቲካ ዘይቤ በአሁኑ ዘመን ውስጥ ለመተግበር አንሞክር፡፡

አንድ ሰው ትልቅ ቪላ ገንብቶ በውስጡ ያሉትን ክፍሎች እጅግ ቢያስውባቸውና የቤቱን ጣሪያ ባይከድነው ቤቱ በውስጡ ሰው ሊያኖር አይችልም፡፡ ይኼ ውብ ክፍሎች ያሉት ቤት ከዝናብ፣ ከፀሐይ፣ ከብርድና ከአደጋ የማያድን በመሆኑ፣ ሁሉም ክፍሎች መኖሪያ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች በክፍሉ ውስጥ ተከፋፍለው እንደሚኖሩ ሰዎች አድርገን ብንወስዳቸው ሁላቸውንም በሰላም፣ በምቾትና በመልካም ቤተሰብነት ሊያኖራቸው የሚችለው የጋራ የሆነውን ቤት በኢትዮጵያዊነት ጣሪያ ስንከድነው ነው፡፡ ጣሪያው የሁሉም ሀብትና ተስፋ ስለሆነ በየክፍሉ ያሉት ሁሉ እኩል ሊንከባከቡት ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ዝናብ ሲዘንብ እኩል ይበሰብሳሉ፡፡ ፀሐይ ሲከር እኩል ይቃጠላሉ፡፡ ብርድ ሲሆን እኩል ይንቀጠቀጣሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ቤቱ ፈራሽ ነው፡፡ ለአንዱ ክፍል ብቻ በተለይ የሚመጣ ምቾትም ሆነ መከራ የለም፡፡

ኢትዮጵያዊነት በፅኑ መሠረት ላይ እንዲቆም የምንፈልገው ባለፈው የልጅነት ትዝታችን ወይም ገናና ታሪክ ስላለን ብቻ አይደለም፡፡ አሁን ያለውን ትውልድና የወደፊቱን ልጆቻችንን በሰላምና በምቾት ያኖራቸዋል ከሚል መነሻ ነው፡፡ ይኼንን ማድረግ በዋናነት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥት ካለበት ኃላፊነቱና ለራሱም ህልውና ሲል መፈጸም የሚገባውን ይህንን ቅድሚያ መሠረታዊ ኃላፊነት ለመወጣት የሚቀረው ነገር አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ መንግሥት ያለው አብዛኛው የሰው ኃይል ለዚህ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ መሠረታዊ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ያለው ልምድና ብቃት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ አገርን ለማስተዳደርና ሕዝብን ለመምራት ስለክልላችንና ስለብሔራችን ብቻ መጨነቅ ግማሽ ዕውቀት ነው፡፡ አጠቃላይ የአገሪቱን የቀድሞ ታሪክ፣ ስለደረሰባት ችግርና እንዴት እንደ ተቋቋመችው፣ እንዲሁም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተለይተን በነፃነት የመኖር ሚስጥርን ትውልዱ ሊያውቀው ይገባል፡፡ አገሪቱን በማንኛውም እርከን ላይ ኃላፊነት ወስዶ የሚያስተዳድር አመራር የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪክ እንዲያውቅ ማድረግ ተገቢና ግዴታ ነው፡፡

በዕድሜ መብሰል፣ የአገሪቱን ታሪክ በስፋት ማወቅ፣ ብዙ አገራዊና ማኅበራዊ ንቃትን ሊያላብሰው በሚችል ሁኔታ ውስጥ ማለፉ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ አስተዋይና የተረጋጋ ሆኖ የነገሮችን አመጣጥና የወደፊት አቅጣጫን መተለም መቻል አገር ለማስተዳደር ከዋናዎቹ መመዘኛዎች ውስጥ ስለሆኑ ነው፡፡ የዲግሪ ብዛትና ዓይነት፣ እንዲሁም ወጣትነትና ካድሬነት ብቻቸውን ለዚህ ዘርፍ ብቁ ስለማያደርጉ ዋና መመዘኛ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

መንግሥት የአገሪቱን ቁሳዊ ልማት በከፍተኛ ሁኔታ እያካሄደ በመሆኑ ሊመሠገን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን በዚያው ልክ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ አብሮ ካላደገ ልማቱ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ልማቱ አንድነት ባለው ጠንካራ ሕዝብ መጠበቅ አለበት፡፡ በመንፈስ የተለያየ ሕዝብ ልማቱን ቀርቶ ራሱን ለመጠበቅ ይከብደዋል፡፡ የብዙ ሺሕ ዘመን ልማትና ዕድገት በሐሳብና በፖለቲካ በተለያዩ ክፍሎች ምክንያት ትልልቅ አገሮች ሳይቀሩ ፈርሰዋል፡፡ የእኛንም ልማት ለማስቆምና ለማውደም የሚጥሩ ክፍሎች፣ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ ለመኖራቸው ፍንጭ ታይቷል፡፡

ለዚህ ችግር ዋና መፍትሔ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ተጠናክሮ አገራዊ ጥበቃ ሁሉም ሲያደርግ ነው፡፡ ይኼን ለመፍጠር ደግሞ ብቁና ዝግጁ የሆኑ የመንግሥት አካላት ያስፈልጉናል፡፡ ይኼን ማድረግ የሚችሉ በርካታ ዜጎች አገሪቱ አሏት፡፡ ነገር ግን መንገዱ ሁሉ ለአገሪቱ ህልውና ምንም በማይፈይዱ፣ ነገር ግን በመለማመጥና በማስመሰል ከሥልጣን ጣሪያ ለመድረስ በሚጥሩ አሜኬላዎች ስለታጠረ ዋና ጉዳያችን ወደ ጎን ተገፍቷል፡፡

የፌዴራል ሥርዓታችን ክልሎች ሊኖራቸው የሚገባቸውን አገራዊ የሆነ ፕሮግራምና ራዕይ ማስቀመጥ አለበት፡፡ በየብሔረሰቡ ቋንቋ ሕዝቡን እንዲያገለግሉ የተቋቋሙት የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መገምገም አለባቸው፡፡ በርካታ የፌዴራልም ሆኑ የክልል ባለሥልጣናት የሚያስተላልፉት መልዕክት ቀድሞ ስለነበረው ቁርሾ ነው፡፡ ግማሹ የራሱን ክልል ዕድገት የማይፈልጉ ጠላቶች በሌላው ክልል ውስጥ እንዳሉ በድፍረት ይናገራል፡፡ ግማሹ ሀብትህንና ንብረትህን ሌሎች እንዳይዘርፉህ እያለ ሕዝቡ ውስጥ የጥላቻ ስሜት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ በጠቅላላው ለሁላችንም የምትበቃንን ሰፊ ዓለም ያጠባታል፡፡ ግማሹ አገሪቱ የቆመችው በተወሰነ ክፍል መስዋዕትነት አስመስሎ ሕዝቡ ውስጥ የሌለ ጥርጣሬ ያጭራል፡፡

በጠቅላላው የብሔረሰብ መብትን ከሚገባው በላይ ስናጠብቀው ኢትዮጵያዊ መንፈስ ይላላል፡፡ ዕንቁላልን ከሚገባው በላይ መቀቀል ምንም ጥቅም የለውም፡፡ የተባሉት ችግሮች አልፎ አልፎ ቢታዩም በግለሰቦች ደረጃ እንጂ፣ እንደ ክልል ወስደን የጥላቻ መንፈስን የሚያባብስ ነገር አናውራ፡፡ አገር የምትለማውና የምትገነባው በረዥም ጊዜ ሒደት ነው፡፡ አገር የምትፈርሰው ግን በአጭር ጊዜ ክስተት ነው፡፡ የጥላቻና የጥርጣሬ ስሜትን በሕዝብ ውስጥ መፍጠር አፍራሽ ክስተትን እንዳያስከትል እንጠንቀቅ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...