ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ትልቁን ድርሻ በቋሚነት እያበረከተ የሚገኘው የቡና ኤክስፖርት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ዘርፍ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ከምርቱ ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት አኳያ ሲመዘን ትልቅ ክፍተት መኖሩ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይባስ ብሎ ባለፉት ዓመታት ከቡና ኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ እንዳሽቆለቆለ የኤክስፖርት ዘርፍ አፈጻጸምን የተመለከቱ ዓመታዊ ሪፖርቶች ያረጋግጣሉ፡፡
የ2014 እና 2015 ዓ.ም. ለውጭ ገበያ ከቀረበው ቡና የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ሲነፃፀር ዝቅ ማለቱን ያሳያል፡፡ ገቢው ዝቅ የማለቱ ችግር ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩትም፣ የዓለም አቀፉ የቡና ገበያ መውረድና የአገር ውስጥ ገበያ ከፍ ማለቱ ለኤክስፖርት በሚቀርበው የቡና ምርት መጠንና በውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ላየ ከፍተኛ ጉድለት ማስከተሉ ሲገለጽ ይስተዋላል፡፡ የአገር ውስጥ ፀጥታ ችግርና የቡና ምርትን በሕገወጥ መንገድ ከአገር የማስወጣት የወንጀል ድርጊት መስፋፋት ከሚጠቀሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሰውን ዓለም አቀፍ የቡና ገበያ መቀዛቀዝ የፈጠረውን ችግር በተወሰነ ደረጃ ይቀንሳል የተባለው ‹‹20ኛው የአፍሪካ ፋይን ኮፊ ኤግዚቢሽን›› በመጪው የካቲት ወር 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዝግጅት ተጀምሯል።
የዚህ ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያ መካሄድ አምራቾች ምርታቸውን ከማስተዋወቅና ከማሻሻጥ በዘለለ፣ የዓለም ቡና ገበያ በተቀዛቀዘበትና ዋጋው በወረደበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ የኢትዮጵያ የቡና አምራቾችንና ኤክስፖርተሮችን (ላኪዎችን) ከዓለም የቡና ገበያ ተዋናዮች ጋር የቀጥታ ትውውቅና ግንኙነትን ለመመሥረት ያስችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር ወይም የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ፣ ‹‹የአፍሪካ ፋይን ኮፊስ ኤግዚቢሽን›› በኢትዮጵያ መካሄዱ ያለው ጠቀሜታ የዓለም ቡና ዋጋ በወረደበት ወቅት በመሆኑ ሻጮችና ገዥዎችን የሚገናኙበት መድረክ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ቡና አቅራቢዎች ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የካቲት ወር የኢትዮጵያ ቡና ሽያጭ የሚጀመርበት ወቅት መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛት፣ የዚህ ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያ መካሄድ የተሻለ የቡና ዋጋ የሚገኝበት አጋጣሚ ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ አሁን ባለው የዓለም ቡና ዋጋ የአንድ ፓውንድ ቡና (ከግማሽ ኪሎ ግራም ያነሰ ቡና) 1.50 ፓውንድ መድረሱን ገልጸው፣ ተመሳሳይ መጠን ያለው ቡና ባለፈው ዓመት በ2.60 ፓውንድ ይሸጥ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን የታየው የዓለም ቡና ገበያ መቀዛቀዝ ከዚህ በኋላም የሚቀጥል ከሆነ አሥጊ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የዓረቢካና የሮቡስታ ቡና ዝርያዎች በዓለም የቡና ገበያ ላይ የሚያደርጉት ፉክክር ለቡና ዋጋ መውረድ አንደኛው ምክንያት መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ከ30 ዓመታት በፊት የሮቡስታ ቡና የዓለም ገበያን 30 በመቶ፣ ዓረቢካ ደግሞ የዓለም ገበያን 70 በመቶ ፍላጎት ይሸፍኑ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡
ለዓመታት ኢትዮጵያ የምታቀርበው ቡና 100 እጅ ዓረቢካ በመሆኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ ስታገኝ መቆየቷን ገልጸው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የሮቡስታ ቡና በዓለም ገበያ የነበረው ድርሻ ወደ 46 በመቶ ከፍ ሲል፣ የዓረቢካ ቡና የዓለም ገበያ ድርሻ ደግሞ ወደ 54 በመቶ መውረዱን ተናግረዋል፡፡
የዓለም የሮቡስታ ቡና ዋጋ ዝቅተኛ ወይም ከዓረቢካ ቡና ያነሰ በመሆኑ ለዚህ የገበያ ድርሻ ለውጥ መፈጠር ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በተለይ የዓረቢካ ቡና ምርት በየጊዜው የሚዋዥቅ ወይም ከፍ ዝቅ የሚል መሆኑ ሌላኛው ችግር ነው ያሉት አቶ ግዛት፣ የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ ከፍ ማለቱ ጭምር የውጭ ምንዛሪ ግዥ ላይ ጉድለት ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ቡናን በስፋት የሚሸምቱ አገሮች በጥንቃቄ እንደሚገበያዩ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ አሁን ባለው የዓለም ገበያ ሥርዓት የቡና ዋጋ የሚወስኑ አምራቾችና አቅራቢዎች ሳይሆኑ ገዥዎች መሆናቸውን፣ ይህም ለቡና ዋጋ መዋዥቅ ምክንያት ሊሆን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በየካቲት ወር በሚካሄደው ኤግዚቢሽን የቡና ዋጋ በወረደበት ወቅት የመጣ በመሆኑ አምራቾችና ላኪዎች የሚያቀርቡትን ቡና አንዲሁም እራሳቸውን ለዓለም ገበያ ተዋናዮች ለማስለዋወቅና አዲስ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ከዘርፉ ከሚሊዮን ዶላር ወደ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ወደ ማግኘት መሸጋገሯን ገልጸዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም. 1.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከቡና ኤክስፖርት መገኘቱን፣ በ2015 ዓ.ም. ደግሞ ወደ 1.3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ በመገኘቱን ገልጸው፣ በ2016 በጀት ዓመት 1.75 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማመንጨት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ለማሳካት ደግሞ ግብይቱን የማዘመንና የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ በማስተዋወቅ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝና በዚህም የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማስፋት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ይህንን ዕቅድ ለማሳካት የተለያዩ ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀት ወሳኝነት እንዳለው አቶ ሻፊ ጠቁመው፣ ከእነዚህም ውስጥ የካቲት ወር የሚካሄደው የአፍሪካ ፋይን ኮፍ ኮንፈረንስ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን የቡና ሀብት ለዓለም ገበያ ታቅርብ እንጂ፣ በገበያው ላይ የመደራደር አቅም ውስንነት በመኖሩ ክፍተት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ይህንን በዓለም የቡና ገበያ የመደርደር አቅም ለማጎልበት የአፍሪካ ፋይን ኮፍ አሶሴሽን አዘጋጅነት ‹‹አፍሪካ የቡና ሳምንት›› በሚካሄደው ኤግዚቢሽን የመደራደር አቅምን ለማጎልበት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዚህ ኤግዚቢሽን በዋናነት በዓለም ገበያ የኢትዮጵያን ቡና ከማስተዋወቅ በዘለለ፣ የተለያዩ ጥናቶችና ውይይቶች በማድረግ ተደማጭነትን ለማግኘትና የመደራደር አቅምን ለማግኘት ዕድሉ እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡
ከዓለም ገበያ በተጨማሪ በአፍሪካ የቡና ገበያም በሰፊው ለመግባትና ምርቱን ለማስተዋወቅ ኮንፈረንሱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ፋይን ኮፍ አሶሴሽን ዋና ዳይሬክተር ጊልበርት ጋታሊ፣ የአፍሪካ ፋይን ኮፍ አሶሴሽን ‹‹አፍሪካ የቡና ሳምንት›› የዓረቢካ ቡና መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ መካሄዱ ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በዚህ የአፍሪካ ቡና ሳምንት ከ2,000 የሚበልጡ የቡና ነጋዴዎች፣ ላኪዎችና አምራቾች ተጨማሪ ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ገዥዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ ፋይን ኮፍ አሶሴሽን ከ11 አገሮች በተጨማሪ፣ ዓለም አቀፍ ተገበያዮች የሚገኙበት በመሆኑ ለአፍሪካ ቡና አምራቾች ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
በኤግዚቢሽኑ በሚፈጠረው ስምምነቶችና ትውውቆችና ግብይቶች በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያስገኛል በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በመጪው የካቲት ወር በአዲስ አበባ በሸራተን ሆቴል ይካሄዳል የተባለው የአፍሪካ የቡና ሳምንት፣ ከአዘጋጇ አገር በተጨማሪ የአባል አገሮች ያሏቸው አንጡር የቡና ሀብት ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካ ፋይን ኮፊስ አሶሴሽን ከተመሠረተ 23 ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪካ አባል አገሮች ያሉበት ተቋም ነው፡፡