ትናንት በቀበና ወንዝ ዳር ስራመድ አንድ ከየካ ተራራ ላይ አቅጣጫ የመጡ ጠቢብ አዛውንት አስቆሙኝ፤ እና የሚከተለውን ለቀቁብኝ፤
‹‹ልዠ ሆይ! መስከረም ማለት ተፈጥሮ ከጸጋዎቹዋ ሁሉ የክት የክቱን መርጣ የምታቀርብበት ወር ነው፡፡ ላይንህ አሪፍ ኅብረቀለም፣ ላፍንጫህ መልካም መዓዛ፣ ለጆሮህ ቆንጆ ጣዕመ ዜማ መርኣ ትለግስሃለች! በዚህች ዓለም ውስጥ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እንድትኖር ስለተፈቀደልህ የምታመሰግንበት ወር መስከረም ነው! ማንነው የማመሰግነው አትበል? አላህን፣ እግዜርን፣ ዋቃዮን፣ እመቤት ተፈጥሮን፣ እናትህን፣ ቆሌህን፣ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ መሬት ታጋሽ፣ እንደ ገበሬ ውለታ አስታዋሽ ሁን! ገበሬ ወረተኛ አይደለም፡፡ ‹አትኩራ ገብስ ጎመን ባወጣው ነፍስ ይላል› ገብስ ስለደረሰለት የጎመንን ውለታ አያጣጥልም፡፡
‹‹መስከረም የፈንጠዝያ ወር ነው፡፡ ሠርተህ ባይሞላልህ ተበድረህ፣ ተመጽውተህ ያቅምህን ያክል ደግስ፣ የቻልከውን ያህል አካፍል! ብላ አብላ! ሕዝብ ለሕዝብ ሳይሆን ብርጭቆን ከብርጭቆን ማጋጨት ተማር! መጠነኛ ስካር በራስህ ላይ አፋፍም! መስከረም የሚለው ቃል ስር ‹መስከርያ› ከሚለው ቃል እንደመነጨ ከቶ አትዘንጋ!
‹‹ፍቅረኛህን ወይም እማወራህን ዓውዳመቱን አስተካከህ የከበረ ስጦታ ስጣት! ቤት ባትገዛላት ቤት የሚመታ ግጥም ጻፍላት! በስስት ሳማት! በልዩ ፈሊጥ እቀፋት! ከምኝታ ፈሊጦች ውስጥ ‹የእንግላል› የተባለው ፈሊጥ ለአዘቦት ቀን ብቻ የሚያገለግል መሆኑን አትርሳ፡፡ በዓውዳመትና ለክብረ በዓለት ቀናት ግን፣ እንደ ‹ወስፌ ጥምዝ› ‹ምሳር ባንገቴ› ‹አሞራ ገፍገፍ፣ ‹ጫንቃ ሰበር› ዓይነት ፐዚኖችን መጠቀም ተፈቅዷል፡፡ ይህንን ሁሌም በልቦናህ መዝገብ አስቀምጠው!
‹‹ምርጥ የምትለውን ስጥ፣ ኮሚክ ከሆንክ ከባለጌ ወንበራችን ላይ ገፍትሮ የሚጥለንን ቀልድ ልቀቅብን! ዘፋኝ ከሆንክ ወፍ ብቻ ሳይሆን ኮከብ እሚያረግፍ ዘፈን ልቀቅብን! የቲክቶ ተሳዳቢ ከሆንክ የቸኩ የተሰለቹ ስድቦችን ትተህ ሌላ አምጣ፡፡ ለምሳሌ ሰገጤ፣ እከካም! ቆማጣ፣ ግማታም፣ ከብት ወዘተረፈ ዓይነት ስድቦች ከበቂ በላይ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ባዲሱ ዓመት ብትደግማቸው ስሜት አይሰጡም! ስድብ ሲደጋገም ቁልምጫ ይመስላል፡፡ ባዲሱ ዓመት አባቶቻችን ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን አንጋፋ ስድቦችን አድሰህ ተጠቀምባቸው! ለምሳሌ ‹ደንደሳም›፣ ‹ቅንዳሻም›፣ ‹ስብድብድ›፣ ‹ዞፍ› እና ‹ኩስለመናም› የመሳሰሉ አጥንት ሰባሪ ስድቦች ከፈለግህ በተመጣጠነ ዋጋ ከኔ መውሰድ ትችላለህ!
በተቻለህ መጠን በጎ አድርግ፣ ተፈለጥ! አልፎ አልፎም አውቀህ ተበለጥ! ያም ሆኖ የሙሉ ጊዜ ጣድቅ ለመሆን አትጋጋጥ! ተሳሳት፡፡ ያነተ መሳሳት ለፕሮፌሽናል መካሪዎች፣ ኑዛዜ ተቀባዮች፣ ንስሀ ሰጪዎች፣ ተቺዎች፣ ከሳሾች፣ አሜተኞች ሥራ እንደሚፈጥርላቸው አትርሳ!
- በዕውቀቱ ሥዩም በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደከተበው