Wednesday, June 12, 2024

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምና የሚነሱ ጉዳዮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ፣ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ እንደ አስፈላጊነቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የተተገበሩ አዋጆች ሁለት ናቸው፡፡

የመጀመርያው በሰሜን ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም. ከሕወሓት ጋር ተከስቶ በነበረው ጦርነት ‹‹የአገርን ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ አዋጅ›› ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በ2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል ከፋኖ ጋር ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ‹‹የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ›› ነው፡፡ የመጀመርያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲነሳ ከተደረገ ስምንት ወራትን አስቆጥሯል፡፡

የአሁኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲወጣ ምክንያት የሆነው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ሕገወጥ እንቅስቃሴ፣ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደ የማይቻልበት ደረጃ በመሸጋገሩ እንደሆነ በአዋጁ ማብራሪያ ላይ ተገልጿል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ያፀደቀውን አዋጅ ተመልክቶ ለመወሰን ከክረምት የዕረፍት ጊዜው ለአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. አዋጁንና የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተል መርማሪ ቦርድ ሹመት አፅድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተካሄደው ስምምነት እንዲገታ በመደረጉ፣ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን ወደ መደበኛ የመንግሥት ኃይል የማስገባት ወይም የማሰናበት ሥራ  በሁሉም ክልሎች መካሄዱን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡

ይህን አፍርሶ የመሥራት ሒደት ተከትሎ በአማራ ክልል የልዩ ኃይል መፍረስና በክልሉ ለአርሶ አደሮች የማዳበሪያ አቅርቦት ውስንነት በተገናኘ የጀመረው ውጥረት፣ በአገር መከላከያ ሠራዊትና በፋኖ መካከል ወደ ግጭት ያመራው በሐምሌ 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ነበር፡፡

በተቀሰቀሰው ግጭት በአንዳንድ አካባቢዎች በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙንና የሰላማዊ ሰዎችና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሐምሌ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ አስታውቆ ነበር፡፡

በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በአመዛኙ የሚመራው ኢመደበኛ በሆነውና ፋኖ እየተባለ በሚጠራው አደረጃጀት ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ቀድሞ የክልሉ ልዩ ኃይል እንዲፈርስ ሲወሰን ብዙዎች የኢመደበኛ አደረጃጀቶችን መቀላቀላቸውን የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ተናግረው ነበር፡፡

የሰላም ሚኒስትሩ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር አስመልክቶ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በክልሉ የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች የማስገባት ሥራ ከተጀመረ በኋላ 50 በመቶ የሚሆኑ የልዩ ኃይል አባላት እንደተበተኑ፣ ነገር ግን አብዛኞቹ የቀድሞ የልዩ ኃይል አባላት ታጣቂ ቡድኖችን እንደተቀላቀሉ ገልጸው ነበር፡፡

የቀድሞው አማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በክልሉ ያለው ሁኔታ ከአቅም በላይ መሆኑን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወሳል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት በይፋ ሕግ ማስከበር የጀመረው ከፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ በኋላ ነው ቢባልም፣ ፕሬዚዳንቱ ደብዳቤውን ከመጻፋቸው በፊት በክልሉ ሠራዊቱ ሲያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ የሕጋዊነት ጥያቄም ከማስነሳቱም በላይ የቅራኔ ምንጭም ሆኖ ነበር፡፡ 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በፋኖና የአገር መከላከያ ሠራዊት መካከል የተጀመረው ግጭት እያስከተለ ያለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በመግለጽ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ከኃይል አማራጭ ወጥተው በድርድርና በውይይት እንዲፈቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ጥሪ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአዲስ ዓመት መልዕክታቸው፣ ‹‹ሕዝባችን ካለፈው ሳያገግም አሁንም ከሰላም ዕጦት አላመለጠም፣ ዛሬም በርካታ ዜጎቻችን በእርስ በርስ ውጊያ ውድ ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ እያጡ ነው፣ ቆስለዋል፤ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ አክለውም፣ ‹‹ብዙ ጊዜ እንደምለው በእርስ በርስ ግጭትም ሆነ ውጊያ ወገን ወገኑን እየገደለ ስለሆነ አሸናፊ የለውም፡፡ ችግሩን ከሥር መሠረቱ ዓይቶ ዘላቂ መፍትሔ ከማስገኘት ሌላ የተለየ መንገድ የለንም፤›› በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የሚታዩት ችግሮች በጊዜያዊ ጥገና ሳይሆን ከመሠረቱ ለመፍታት እንቅስቃሴ ይደረግ በሚል ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዚዳንቷ መናገርን፣ ማሳመንን፣ መወያየትንና መደራደርን ማስቀደም ለሰላም ዋስትና በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ አደራ ብለው ነበር፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በፓርላማ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ በሚሰጣቸው መግለጫዎች በታሳሪዎች ላይ የደረሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለመኖሩን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምርያ ዕዝ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል አሉኝ ከሚላቸው አምስት ማቆያ ቦታዎች ውጪ ሌሎች ማቆያ ቦታዎች እንደሌሉ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በሕግ ጥላ ሥር ያሉት ሰዎች በተለይም ቦርዱ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ 764 ብቻ እንደሆኑ፣ በማቆያ ቦታዎች ያለው አያያዝ ሁኔታ ጥሩ የሚባል መሆኑን ገልጿል፡፡

በይፋ ከተቀሰቀሰ ሁለት ወራት ሊሞላው ቀናት የቀሩት ይህ ግጭት እየተባባሰ መምጣቱንና እስካሁን 183 ንፁኃን መገደላቸውንና ከ1,000 በላይ ዜጎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት መታሰራቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ በሕግ ቁጥጥር ሥር ውስጥ ከሚገኙት በርካታዎቹ በብሔር አማራ የሆኑና የ‹‹ፋኖ›› ደጋፊዎች ናችሁ ተብለው መታሰራቸውን፣ ማቆያ ቦታዎቹም በፊት ያልነበሩ በጊዜያዊነት መገንባታቸውን፣ እንዲሁም ለማቆያነት በሚመጥን ደረጃ መቅረብ ያለባቸው መሠረታዊ አቅርቦቶች ያልተሟሉበት ነው ብሏል፡፡

ከሰሞኑ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በርካታ የአማራ ተወላጆች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በቁጥጥር ሥር ውለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አየተፈጸመባቸው ነው ተብሎ ሲሠራጭ የነበረው መረጃ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የማይገናኝና ከእውነታው የራቀ ነው ሲል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ መስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ አዝመራ እንደሞ በሰጡት መግለጫ፣ በአማራ ክልል በተቋቋመው አራት ኮማንድ ፖስቶችና ከዚህ ጉዳይ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ማዕከላት በቁጥጥር ሥር ካሉ ተጠርጣሪዎች ውጪ ሌሎች የማቆያ ቦታዎች የሉም ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የመስክ ምልከታ አካሄድኩ ያለው ቦርዱ በምዕራብ አማራ ኮማንድ ፖስት ባህር ዳር ከተማ ማረሚያ ቤት፣ በምሥራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ኮምቦልቻ ጊዜያዊ ማቆያ ቤት፣ በማዕከላዊ አማራ ኮማንድ ፖስት ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤትና በሰሜን ምዕራብ አማራ ኮማንድ ፖስት ጎንደር ከተማ የቀድሞ ማረሚያ ቤት ነው፡፡

መርማሪ ቦርዱ እንደገለጸው በመስክ ያደረገው ምልከታ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦችን ሰብዓዊ ሁኔታን እንጂ፣ ከዚያ ያለፉ ጉዳዮችን የሚመለከተው አዋጁን እንዲያስፈጽሙ በጠቅላይ መመርያ ዕዝ የተቋቋሙ የመንግሥት አካላት ናቸው ብሏል፡፡

የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢ እንደገለጹት፣ ቦርዱ ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን በግል አነጋግሯል፡፡ በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ አካላት ተጠርጥረው ሲያዙ ከቁጥራቸው በላይ የበዛ የፀጥታ ኃይል ቤታቸው ድረስ መምጣቱ፣ በአዲስ አበባ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች በጥቆማና በዛቻ የተያዙ ስለመኖራቸው እንጂ፣ ከተያዙ በኋላ ማንም ድብደባም ሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልደረሰባቸውና ይልቁንም ‹‹ጠባቂዎቻቸውን ያመሠገኑ አሉ›› ብለዋል፡፡

በምልከታው ወቅት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦቸ ላይ የሚካሄደው የፖሊስ ምርመራ እንዲፋጠን አሳውቄያለሁ ያለው ቦርዱ፣ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ አከናወንኩት ባለው ክትትል በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ 764 ተጠርጣሪዎች ብቻ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ሰዎች በተደጋጋሚ ይታሰራሉ በሚል ለመርማሪ ቦርዱ በመጣለት ጥቆማ መሠረት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዕዝ ጋር መነጋገሩን ጠቅሶ ዕዙ አንድም ሰው በትምህርት ቤቶች እንዳልታሰረ አስታውቋል፡፡ ወደ ትምህርት ቤቶች በመሄድም ክትትል በማድረግ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ ሪፖርተር በቅርቡ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች አሉበት ከተባሉት መካከል፣ በየካ ክፍለ ከተማ ደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ተገኝቶ የታሳሪ ቤተሰቦችን በማነጋገር ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል፡፡

መርማሪ ቦርዱ በሰጠው መግለጫ የፖሊስ ምርመራ ባለሙያዎችን በመጨመርና ምርመራውን በማፋጠን፣ ውጤቱን መሠረት በማድረግ ተገቢነት ያላቸውን የሕግ አማራጮች በመጠቀም፣ በቂ ማስረጃ የማይገኝባቸውን እንዲለቀቁና ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልግባቸውን እንደ ሁኔታው በማስተናገድ የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ወጣት ጥፋተኞችን በመለየት በሕጉ በተቀመጠው አማራጭ የምክርና የፀባይ ማረሚያ አማራጮች እንዲተገበሩ ከዕዙ ጋር መነጋገሩን አስታውቋል፡፡

በምርመራ ሒደት በወንጀል ውስጥ መሳተፋቸው በቂ ማስረጃ ያለባቸውን ተጠርጣሪዎች በቶሎ ክስ በመመሥረት ወደ ፍትሕ ማቅረብና በተቻለ መጠን ተገማች በሆነ ጊዜ በአጭር ጊዜ እንዲተገበር ጥሪ ማቅረቡን የገለጸ ሲሆን፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ጉዳያቸው በምን ያህል ጊዜ መታየት እንዳለበት ግን ቦርዱ ያለው ነገር የለም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚ ከሚሆንባቸው ቦታዎች ውጪ እስራት ተፈጽሞባቸዋል የሚባሉ ቦታዎች በተለይም ገላን፣ ሲዳማ፣ አዋሽና አዋሽ አካባቢ መሆናቸው ለቦርዱ ጥቆማ እንደደረሰው ቦርዱ የገለጸ ቢሆንም፣ አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆንባቸውን ቦታዎች ቅድሚያ መስጠት ያለበት በመሆኑና ከጊዜ ውስንነት አንፃር በቀጣይ የማጣራቸው ናቸው ብሏል፡፡  

መርማሪ ቦርዱ የተቋቋመው በዋነኝነት በዕዙ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦችን የሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታ እንጂ፣ ከዕዝ ውጪ ባይሆንም ሕግ መከበር ያለበት በመሆኑ ዕዙ በአዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በፍጥነት ማጣሪያ አድርጎ በአዋጁ ወይም በዕዝ ስም እስራት የፈጸሙ አካላት ካሉ ዕርምጃዎች እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡ በርካቶች ታስረዋል በሚል በተደጋጋሚ እየተነሳ በመሆኑ፣ በክፍል ሁለት ወደ ማቆያዎች ቦታ ከመሄዱ በፊት ጥቆማ የበዛባቸውን ቦታዎች ሄዶ እንደሚያረጋግጥ አስታውቋል፡፡

በትምህርት ቤቶች የታሰሩ ግለሰቦች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምርያ ዕዝ የታሰሩ አለመሆናቸውን ዕዙ እንዳረጋገጠላቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ገልጸው፣ ‹‹ዕዙ የእኛ ታሳሪዎች ናቸው ቢለን የሪፖርታችን አካል ማድረግ እንችል ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣት በፊትም ሆነ በኋላ በሃይማኖታዊ፣ በባህላዊና በሌሎች ዓለም አቀፍ ኩነቶች ወቅት የወንጀል እንቅስቃሴ ይበዛል በሚል ሰዎችን ሊያቆዩ እንደሚችሉ የቦርዱ ሰብሳቢ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ ትምህርት ቤቶች በሄደበት ወቅት ታሳሪዎችን አላገኘሁም ብሏል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ እንደሚናገሩት የተሰጣቸው ኃላፊነት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  መምርያ ዕዝ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ሰዎች የአያያዝ ሁኔታ እንጂ፣ ዕዙ ከሚያስተዳድራቸው ውጪ ተንቀሳቅሶ ምርመራ ለማድረግ ኃላፊነት የለበትም፡፡ የምርመራ ቦርዱ በአማራ ክልልም ሆነ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች የኃይልና የሞራል ጉዳት ደርሶባቸው አላገኘንም ብሏል፡፡

ከአዲስ አበባ አዋሽ አርባ ተወስደው በጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ታራሚዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ ታሳሪዎች ያሉበት ቦታ ሩቅ መሆኑንና ቤተሰቦች እዚያ ድረስ ሄደው መጠየቅ አለመቻላቸውን በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ከቤተሰብ ጋር በስልክ መነጋገር እንዲችሉ መጠየቃቸውንና ለዚህም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ኢሰመኮ ይህን ይበል እንጂ ቦርዱ ከኢሰመኮ የክትትል ሪፖርት በፊት በቦታው ተገኝቼ አካሄድኩት ባለው ምርመራ በአዋሽ አርባ የነበሩት 34 ሰዎች መሆናቸውን፣ እነዚህ ታሳሪዎች ቤተሰቦቻቸውን በስልክ እንዲያገኙ የሚከለክል ማንም አለመኖሩን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -