Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየህዋ ሳይንስን የቀሰሙት ታዳጊዎች

የህዋ ሳይንስን የቀሰሙት ታዳጊዎች

ቀን:

ገና የማንበብን ጥቅምንም ሆነ ፊደላትን አገጣጥሞ የመጻፍ ችሎታ ባልነበረው በሕፃንነት ዘመኑ፣ በየመጻሕፍት ማስቀመጫ የሚያገኛቸውን የትኞቹንም መጻሕፍት በማገላበጥ ማንበብ ባይችል እንኳ ሥዕሎቹን ይመለከት ነበር፡፡

ነገር ግን ከተወሰነ ዓመታት በኋላ ማንበብና መረዳት ሲችል ቤተሰቦቹ ይሆነዋል፣ ይጠቅመዋል የሚሉትን መጻሕፍት በመግዛት፣ እንዲሁም ራሱ የሚፈልገውን በማስገዛትና በማንበብ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ እንደበቃ የተናገረው ታዳጊው ድሜጥሮስ ዘሪሁን ነው፡፡

ታዳጊው የቤተሰቦቹ ዕገዛ ተጨምሮበት በነበረው የትምህርት ተነሳሽነት በኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ሥር በነበረው የሕፃናት ፕሮግራም ለሦስት ዓመታት የመማር ዕድል እንዳገኘ ተናግሯል፡፡

ድሜጥሮስ ለሦስት ዓመታት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ‹‹ኪውኤፍኤች›› (QFH) የተሰኘ ፕሮጀክት በመሥራት ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡

‹‹ኪውኤፍኤች አንቴና›› ማለት የዲሽ አንቴና መሳይ ሆኖ፣ ነገር ግን ከዚህ ለየት የሚያደርገው እንደ ዲሽ አንቴናው ቲቪ ለማየት ሳይሆን፣ በህዋ ላይ ለሚገኙ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት የሚጠቅሙ ናቸው ሲል ያስረዳል፡፡

አንቴናው ዳታዎችን ከሳተላይት በመቀበልና ወደ ምሥል ለመቀየር የሚያገለግል መሣሪያ ነው ብሏል፡፡

የዚህ አንቴና አገልግሎት ደግሞ በአብዛኛው ለግብርና ሥራዎች ጠቀሜታ ሲኖረው፣ የእርጥበት መጠንን ከሳተላይት በመሰብሰብ እንዴት ማየት እንደሚቻል፣ እንዲሁም ስለ ሞቃታማ አካባቢዎች፣ ስለ ድርቅና ስለ ደመና ሽፋንና ትንበያዎች ለማወቅ ያገለግላል ሲል ታዳጊው ያስረዳል፡፡

አሁን ላይ ምንም እንኳን በትንሽ አንቴና ደረጃ ቢሆንም፣ በጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ሥር ስላለ፣ ከሌሎች ትልልቅ ባለሙያዎች ጋር በመሆንና በማስፋፋት በቀጣይ በተለይ ለግብርናው መስክ መረጃዎችን በማሰባሰብ በስፋት እንደሚሠራበት ተስፋ አደርጋለሁ ሲል ተናግሯል፡፡

ታዳጊው በአሁኑ ወቅት ትልቅ ተሳትፎ እያደረገበት ባለው የሙያ ዘርፍ፣ ዕውቀቱንና ሐሳቡን በማሳደግ በቀጣይ በፊዚክስ ዘርፍ ለአገሩ ትልቅ አስተዋጽኦ የማድረግ ህልም እንዳለው አክሏል፡፡

በሌላ በኩል በኢንጂነሪነግ ዘርፉ የስፔስ ኢንጂነሪንግ በማጥናት በዘርፉ የራሱን አሻራ የማስቀመጥ ረዥም ህልም እንዳለው ጠቅሷል፡፡

ሌላው ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ውጪ በስፔስ ሳይንስ (ህዋ ሳይንስ) ወይም በአስትኖሮሚ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ተቋም ባለመኖሩ ትልቅ ፀፀት ያደረበት ደግሞ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሚካኤል አሸናፊ ነው፡፡

ይህንን ችግር ደግሞ በመፀፀት ከማለፍ ይልቅ፣ እንደ ናሳ ባሉ ትልልቅ ተቋማት በመግባትና ዕውቀትን በመሸመት በአገሩ ላይ በርካታ የስፔስ ሳይንስ ምርምሮች የሚሠሩበት ተቋም የመክፈት ትልቅ ህልም እንዳለው ተናግሯል፡፡

ሚካኤል ገና የስምንት ዓመት ታዳጊ እያለ አምስት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስን የተቀላቀለው፡፡

በወቅቱ ‹‹ፍላጎቱ እንጂ ዕውቀቱ አልነበረኝም፤›› የሚለው ታዳጊ፣ ነገር ግን ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡን ያስታውሳል፡፡

በዚህ ውጤቱም ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት የመማር ዕድል ተፈጥሮለት ለመመረቅ መብቃቱን ተናግሯል፡፡ ሚካኤል ባገኘው ትምህርት የሠራውን ፕሮጀክት በማቅረብ ከሌሎች ከአርባ በላይ ከሚሆኑ ጓደኞቹ ጋር ከቡራዩ የልዩ ተሰጥዖ ማሠልጠኛ ተቋም ተመርቋል፡፡

ሚካኤል ከሌሎቹ ጓደኞቹ ጋር በመሆን የፀሐይን አቅጣጫ መከተል የሚችል ሶላር ፓናል በመሥራት አሳይቷል፡፡

ፀሐይ ወጥታ እስክትገባ አቅጣጫዋን እየተከታተለ ኃይልን የሚሰበሰብ ሶላር ፓናል ሲሆን፣ አገልግሎቱም ከፀሐይ የሚገኘውን ኃይል በሁለትና በሦስት እጥፍ ለማሳደግ ያገለግላል ሲል ታዳጊው ተናግሯል፡፡

‹‹ልጆች ገና ከሕፃንነታቸው ጀምረው የቴክኖሎጂን ትምህርት መቅሰም አለባቸው፤›› ያሉት ደግሞ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ የሆኑት ወ/ሮ ሁሪያ አሊ ናቸው፡፡

‹‹ሁላችንም በልጅነታችን ብዙ ሐሳብ በውስጣችን እንይዛለን፤›› ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የልጆችን ልዩ ተሰጥዖ ማውጣት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ሰው የየራሱ ልዩ ችሎታና ተሰጥዖ ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህንን ልዩ ተሰጥዖ እንዲያወጣ ለማድረግ መንግሥት በዋናነት ማመቻቸት ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...