Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለወላጆች ቀንበር የሆነው የትምህርት ግብዓት ዋጋ

ለወላጆች ቀንበር የሆነው የትምህርት ግብዓት ዋጋ

ቀን:

ኢትዮጵያውያን አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ዓመት ለመቀበል ሲሰናዱ በርካታ ወጪ ያወጣሉ፡፡ በተለይ ከምግብና ከመጠጥ ወጪ ባለፈ ወቅቱ ትምህርት ቤት የሚከፈትበት መሆኑ፣ አብዛኛዎቹን ወላጆች ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፡፡

ምንም እንኳን በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሆነውን የትምህርት ግብዓት መንግሥት መሸፈኑ ዕፎይ ቢያስብላቸውም፣ ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ የትሩፋቱ ተቋዳሽ ባለመሆናቸው ችግሩን የበለጠ አጉልቶታል፡፡  

ከሁሉም በላይ የብዙኃኑ ገቢ ባልጨመረበት በዚህ ወቅት በአብዛኛዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የሚባል ጭማሪ መደረጉ ወላጆችን ፈተና ውስጥ ከቷል፡፡ በተለይ በመካከለኛ ገቢ ላይ ሆነው ልጆቻቸውን የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች ዩኒፎርም፣ ደብተር፣ ቦርሳ፣ ምሳ ዕቃና ሌሎች መሰል ግብዓቶች ገዝተው ለማስተማር አቅም አጥተዋል፡፡ አቅም ካጡት መካከል ወ/ሮ ፍሬወይኒ ደስታ ይገኙበታል፡፡

ወ/ሮ ፍሬወይኒ የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ ሁለቱንም ልጆቻቸውን በሳውዝ ዌስት አካዴሚ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እንደሚያስተምሩ ነግረውናል፡፡ የመጀመርያ ልጃቸው አምስተኛ ክፍል፣ ሁለተኛ ሴት ልጃቸው ደግሞ ሁለተኛ ክፍል እንደሆነች የሚናገሩት እኚህ እናት ባለቤታቸውም ሆኑ እሳቸው ከሚያገኙት ገቢ አንፃር ሁለቱንም ልጆቻቸውን ለማስተማር እንደከበዳቸው አስረድተዋል፡፡

የኑሮ ውድነትም ሆነ የቤት ኪራይ ክፍያ አቅም በሚፈትንበት በዚህ ወቅት፣ ሁለት ልጅ የግል ትምህርት ቤት ማስተማር ከባድ ነው የሚሉት እኚህ እናት፣ ለ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ክፍያ ከፍተኛ የሆነ ወጪ ማውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ለትምህርት ቤት ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶች መወደድ ችግሩን ይበልጥ እንዳጎላው ገልጸው፣ በቀጣይ ችግሩ በዚያው ከቀጠለ ሁለቱንም ልጆቻቸውን ከግል ትምህርት ቤት አውጥተው የመንግሥት ትምህርት ቤት ለማስተማር እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡

በየጊዜው በዩኒፎርም፣ በደብተር፣ በቦርሳ፣ በምሳ ዕቃና በሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ላይ የሚደረገው ጭማሪ ለወላጆች ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥት መሠረታዊ የሆኑ ግብዓቶች ላይ የሚደረገውን ጭማሪ በፍጥነት መቆጣጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡  

ከሁሉም በላይ አብዛኛዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች የ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመንን ተከትሎ ክፍያን መጨመራቸው፣ በዚህም የተነሳ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን ከግል ትምህርት ቤት አስወጥተው የመንግሥት ትምህርት ቤት እንዲገቡ ማድረግ መቻላቸውን ወ/ሮ ፍሬወይኒ ገልጸዋል፡፡

ባለቤታቸውም ሆኑ እሳቸው በሚያገኙት ገቢ ሁለት ልጆቻቸውን የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩበት ምክንያት፣ ልጆቻቸው ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ በማሰብ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

‹‹በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን መፈተኑ ቀጥሏል፤›› የሚሉት እኚህ እናት፣ ለትምህርት የሚያስፈልገው ግብዓት ዋጋው በየጊዜው በመጨመሩ ወላጆችን ፈተና ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት ለሁለቱም ልጆቻቸው የሚሆነውን የትምህርት ግብዓት ሲሸምቱ የተሻለ እንደነበር፣ በሒደት ግን የተማሪዎች የትምህርት ግብዓት ዋጋ ሊቀመስ አለመቻሉን አክለው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙና በመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚማሩ ተማሪዎች፣ መንግሥት የግብዓት ድጋፍ ማድረጉ የሚያስደስት መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ለትምህርት ግብዓት የሚሆን ለሁለቱም ልጆቻቸው ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ የገለጹት እኚህ እናት፣ ከአነስተኛ ክፍያ ከፍ ጀምሮ እስከሚለው የሚያስከፍሉ የግል ትምህርት ቤቶች ወላጆች ለልጆቻቸው ሶፍት፣ ልሙጥ ሉክ ወረቀት፣ ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶች እንዲገዙ ይገደዳሉ ብለዋል፡፡

ለ2016 ዓ.ም. ትምህርት ዘመን ለሁለቱም ልጆቻቸው ቦርሳ፣ ደብተር፣ የምሳ ዕቃና ዩኒፎርም መግዛታቸውን ገልጸው፣ ለእነዚህም ግብዓት ከ10 ሺሕ ብር በላይ ማውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በሜትሮ አካዴሚ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ልጁን እያስተማረ ያለና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አባት እንደገለጸው፣ ከነርሰሪ ጀምሮ አሁን እስካለችበት የትምህርት ደረጃ ድረስ ለትምህርት የሚያወጣው ወጪ ከፍተኛ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት አንድ ልጁን አስተምሮ ለቁም ነገር ለማብቃት ላይ ታች እያለ እየሠራ መሆኑን የሚናገረው ይህ አባት፣ ለ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ልጁ ምንም ሳይጎድልባት ትምህርቷን እንድትከታተል ደብተር፣ ዩኒፎም፣ የምሳ ዕቃና ሌሎች የትምህርት መሣሪያዎችን ማሟላት መቻሉን ያስረዳል፡፡

ለዘንድሮ የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቱ በአንድ ተማሪ ላይ ከፍተኛ የሆነ የክፍያ ጭማሪ ማድረጉን የሚያስታውሰው ይህ አባት፣ የቤት ኪራይ፣ የምግብ ፍጆታና ሌሎች ግብዓቶች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ተደምሮ በርካታ ወላጆችን እየፈተነ ይገኛል ብሏል፡፡

ከዚህ በፊት አንድ ልጁን ሲያስተምር ያን ያህል ወጪ እንደማያወጣ፣ ልጁም በአሁኑ ወቅት የሦስተኛ ክፍል ተማሪ መሆኗን ይናገራል፡፡

በተለይ መሠረታዊ ፍጆታ የሚባሉ ጤፍ፣ ስንዴ፣ አልባሳትና ሌሎች ግብዓቶች ላይ በየጊዜው የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ በርካታ ወላጆችን መፈተኑን ገልጾ፣ አሁን ላይ ይህም ችግር በየትምህርት ቤቱ መታየቱ ወደፊት የትምህርት አሰጣጡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ያስረዳል፡፡

መንግሥት ትምህርት መሠረታዊ ነገር መሆኑን ተረድቶ ለትምህርት የሚሆኑ ግብዓቶች ላይ የዋጋ ማረጋጋት ካልፈጠረ፣ በርካታ ወላጆች የማይወጡት ማጥ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ያብራራል፡፡

በተለይ ብዙ ልጆች ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን የግል ትምህርት ቤት ለማስተማር ቢፈልጉም እንኳን፣ ለትምህርት የሚሆኑ ግብዓቶች ወጪ ከፍተኛ ስለሚሆንባቸው ልጆቻቸውን የግድ በመንግሥት ትምህርት ቤት ለማስተማር ይገደዳሉ ብሏል፡፡   

እስካሁን ለአንድ ልጁ የትምህርት ቤት ወጪ ከአምስት ሺሕ ብር በላይ ማውጣቱን የሚናገረው ይህ አባት፣ የዘመን መለወጫ በዓልም ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ችግር ውስጥ መውደቁን ይናገራል፡፡

በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ወላጅ ልጁን ከግል ትምህርት ቤት አስወጥቶ ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት እያስገባ መሆኑን፣ እሱም በቀጣይ ይህ ዓይነት ዕጣ ፈንታ እንደሚገጥመው አስታውሷል፡፡

ሪፖርተር በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ የትምህርት ግብዓት ዋጋ እንደተመለከተው ከሆነ፣ የምሳ ዕቃ ከ1,200 እስከ 2,000 ብርና ዩኒፎርም ከ800 እስከ 1,500 እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ሲነር ላይን 50 ገጽ ደብተር በደርዘን ከ680 እስከ 800 ብር፣ ራዲካል ደግሞ ከ800 ብር እስከ 900 ብር፣ ቦርሳ ከ1,500 እስከ 3,000 ብር እየወጣባቸው ነው፡፡ ግብዓት ላይ ከዓምናው አንፃር ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡

እስኪርቢቶና እርሳስ በነጠላ ከ15 እስከ 20 ብር እየተሸጠ መሆኑን፣ ቅናሽ የሚባለው ደብተር ደርዘኑ ከ600 ብር ጀምሮ እየተሸጠ እንደሆነ ሪፖርተር በቦታው ሆኖ ለመመልከት ችሏል፡፡

ነጋዴዎች የትምህርት ግብዓቶች ዋጋ ከዓምናው አንፃር ዘንድሮ ጭማሪ ማሳየቱን ነጋዴዎቹ ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...