Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ለኢንቨስትመንት መሰጠቱ በሌሎች ፓርኮች ላይ ሥጋት መፍጠሩ ተገለጸ

የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ለኢንቨስትመንት መሰጠቱ በሌሎች ፓርኮች ላይ ሥጋት መፍጠሩ ተገለጸ

ቀን:

በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛው ዝርያ መሆናቸው የሚነገርላቸው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያቸው ለኢንቨስትመንት መሰጠቱ፣ ለሌሎች ብሔራዊ ፓርኮች ሥጋት መፍጠሩን  የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ የዱር እንስሳትና መኖሪያ አካባቢያቸው ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሙያ አዲሱ አሰፋ (ዶ/ር)፣ ከስድስት ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር የፓርኩ ይዞታ ውስጥ 200 ሔክታር የሚሆን ቦታ ለኢንቨስትመንት በመሰጠቱ በዝሆኖቹና በሌሎች እንስሳት ህልውና ላይ አደጋ ተጋርጧል ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የእርሻ ኢንቨስትመንቱን ለማስቆም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱን አዲሱ (ዶ/ር) ጠቁመው፣ ይሁን እንጂ ፍርድ ቤት የዕግድ ትዕዛዝ መስጠት ቢኖርበትም ጉዳዩን ዓይቶ ፍርድ ለመስጠት ቀጠሮ ብቻ መያዙን ገልጸዋል፡፡

በመጠለያው እየተከናወነ ያለው ምንጣሮና የእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ መቆም እንደነበረበትና መልሶ መተካት የማይቻለውን የዝሆኖች መጠለያ ያለ ምንም ዕግድ መተው ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ባለሥልጣኑና የመጠለያው ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች የክልሉ፣ የዞንና ከወረዳ አመራሮችን ጨምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ መጠለያውን እንደገና ለማካለል በተደረገው ውይይት አድርገው ከስምምነት መድረሳቸውን አዲሱ (ዶ/ር) አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ በቅርቡ የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ቁልፍ ቦታ ለኢንቨስትመንት በመሰጠቱ፣ የመጠለያው ሠራተኞች ለወረዳና ለዞን አመራሮች ጥያቄ ቢያቀርቡም ምንም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

ከወረዳ እስከ ኦሮሚያ ክልል የተደረገው ሙከራ አለመሳካቱን የገለጹት አዲሱ (ዶ/ር)፣ በግል ከሌሎች ተቆርቋሪ አካላት ጋር በመሆን ጉዳዩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲደርስ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከጥያቄው በኋላ ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ሥራዎች እየተገበረ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ ከእነዚህም ውስጥ 24 ፓርኮች እንዲቋቋሙ ውሳኔ መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ አዳዲስ ፓርኮችን ማቋቋሙ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በአንድ በኩል እያለሙ በሌላ በኩል የሚወድም ከሆነ ችግሩን የጎላ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ኮንቬንሽንን ከተቀበሉ አገሮች አንዷ መሆኗን የገለጹት አዲሱ (ዶ/ር)፣ የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ የመጠበቅና የመንከባከብ ግዴታ እንዳለባት ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የመጠለያው ሁኔታ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ለመጠለያው እንክብካቤና ጥበቃ ተብሎ የሚቀርቡ ድጋፎች ጭምር ሊቋረጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

በመጠለያው እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ አሠራር የሚቀጥል ከሆነ፣ ባለሥልጣኑ ለዓለም የብዝኃ ሕይወት ተቆርቋሪዎች ጉዳዩን ለማድረስ እንደሚገደድ አስረድተዋል፡፡

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም መሐመድ፣ መጠለያው ከተቋቋመ 53 ዓመታት እንዳስቆጠረ ገልጸዋል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የዩኔስኮ ባለሙያዎች በመጋበዝና ጥናት በማድረግ ያሉት ዝሆኖች የተለዩ ዝርያ መሆናቸው እንደታወቀ አስታውሰዋል፡፡

በመጠለያው ያሉት ዝሆኖች ከምሥራቅ አፍሪካ የተለዩ መሆናቸውን፣ ሌሎችም እንስሳት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ጋር ከተጠበቁ አገራዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ መሆኑ ታምኖበት መቋቋሙን ያስታውሳሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞንና በሶማሌ ክልሎች የሚገኘው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ እስካሁን በተደረገው ጥናት፣ ዝሆኖችን ጨምሮ 31 ዓይነት የእንስሳት ዝርያዎች በውስጡ ይገኛሉ፡፡

ለኢንቨስትመንት የተሰጠው ሥፍራና ዝሆኖች ውኃ የሚያገኙበትና የሚራቡበት ኤረር ሸለቆ የሚሰኝ መሆኑን፣ በዚህም ሳቢያ ለዝሆኖችና ለሌሎች እንስሳት የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተናግረዋል፡፡

የመጠለያው የተወሰነ ክፍል ለኢንቨስትመንት ሲሰጥ የአካባቢው ማኅበረሰብና ሠራተኞች ሳያውቁ መሆኑን፣ በዚህም ከወረዳ እስከ ዞን ድረስ ቅሬታቸውን ቢያሳውቁም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አቶ አደም አስረድተዋል፡፡

በተለይም ከመጠለያው በስተሰሜን በኩል 200 ሔክታር መሬት መሰጠቱን ገለጸው፣ ዝሆኖች ከሚኖሩበት ደግሞ ኤረርና ጉብሌ የተሰኙ ሸለቆዎች በመሆናቸው ለእስሳቱ መጥፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ 75 በመቶ ህልውና የተመሠረተው ለኢንቨስትመንት በተሰጠበት ቦታ በመሆኑ፣ ጉዳዩ ያሳስበናል ሲል የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ጋዜጠኞች ማኅበር አስታውቋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛው የዝሆን ዝርያ መገኛ መሆኑን፣ ዝሆኖቹ ከብዙ አካባቢዎች ተሰደው አሁን የደረሱበት ቦታ ላይ ነው ያሉት ሲሉ ያለውን ችግር ማኅበሩ ገልጿል፡፡  

የኤረር ሸለቆ የዝሆኖቹ ዋና መጠለያ መሆኑንና ለእርሻ የተፈለገውም በጣም ለም በመሆኑ ነው ሲል ማኅበሩ አስረድቷል፡፡

እንደ ማኅበሩ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መፈረሟን፣ ከእነዚህም ስምምነቶች መካከል የባቢሌ ዝሆኖችን መጠበቅ ይገኝበታል፡፡

የመጠለያው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም በበኩላቸው በ2015 ዓ.ም. ብቻ በዝሆንና በሰዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰባት ዝሆኖች መገደላቸውን፣ ዘጠኝ ሰዎች በዝሆኖች መገደላቸውንና አምስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...