- ከሁለት ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕጋዊ ባልሆኑ ግለሰቦች መያዛቸው ተነግሯል
በሸገር ከተማ የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ቁልፍ ሰብረው በገቡ ግለሰቦች ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ለባለዕድለኞች የተላለፉ ቤቶችን ሰብረው የገቡ ግለሰቦችን ማስለቀቅ መጀመሩን፣ በሸገር ከተማ የቤቶች ልማት ማስተዳደርና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አበበ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከቤቶቹ ሕጋዊ ባለቤቶች በተገኙ ጥቆማዎች መሠረት ጽሕፈት ቤቱ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር በመሆን የባለዕድለኞቹን ሕጋዊ ሰነዶች በማረጋገጥ፣ በሕገወጥ መንገድ የተያዙት ቤቶች እየተለቀቁ መሆናቸውን ወ/ሮ መሠረት ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት በኮዬ ፈጬ ከሚገኙ 10/90 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 2,236 ቤቶች ሕጋዊ ባልሆኑ ግለሰቦች መያዛቸውን፣ 1,232 ሕገወጥ ግለሰቦችን በማስለቀቅ ቤቶቹ ለባለቤቶቹ እንዲተላለፉ መደረጋቸውን ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
በሕገወጥ መንገድ ወደ ኮንዶሚኒየሞቹ የሚገቡና የሚወጡ ግለሰቦች ሕጋዊ ሰነድ ስለሌላቸው፣ እንዲሁም የግለሰቦቹን ማንነት ማወቅ ባለመቻሉ ነዋሪዎች ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውም ተነግሯል።
‹‹እነዚህ ሰዎች በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ውስጥ ከሦስት ዓመት በላይ ስለኖሩ በሕገወጥ መንገድ የያዙትን ቤት እንደ ራሳቸው አድርገው ነው የሚያዩት፤›› ሲሉ ወ/ሮ መሠረት ተናግረዋል፡፡ አክለውም ችግሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ ስለሆነ፣ በሮቻቸውም ጠንካራ ስላልሆኑ፣ የተሟላ መሠረተ ልማት ስለሌላቸው፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይልና ውኃ ስላልተዳረሰላቸው በሕገወጦች ያላግባብ እየተያዙ መሆናቸውን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ለአካባቢው መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ኮንዶሚኒየሞቹ የተሠሩት ለልማት ተነሽ ለሆኑ በቀበሌ ቤት ለሚኖሩ ሰዎች መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፣ የቤቶቹ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ ስለሆነ ባለዕድለኞች የተረከቡትን ቤታቸውን ቆልፈው እንዳስቀመጡት አክለዋል።
ነገር ግን ተቆልፈው የተቀመጡ ቤቶች ውስጥ የገቡትን ሕገወጦች በማስለቀቅ፣ ለሕጋዊ ባለቤቶች የማስተላለፍ ሥራ እንደሚቀጥልና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተሠራ መሆኑን ወ/ሮ መሠረት ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው መሠረተ ልማት እስኪሟላ ድረስ ተብለው ተዘግተው ከተቀመጡት በተጨማሪ ለባለዕድለኞች ያልተላለፉ በርካታ ቤቶች በመኖራቸው፣ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ወረራውን እንዲፈጽሙ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ነው የተባለው።
የሕግ ማስከበሩ ሥራ የተጀመረው ከአዲስ አበባ ከተማ ወሰን ማካለልና ከሸገር ከተማ ምሥረታ በኋላ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ሥር ይገኙ የነበሩትን ሕጋዊ ሰነዶች በሙሉ ወደ ኦሮሚያ ክልል ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ወ/ሮ መሠረት ገልጸዋል፡፡