- በጂቡቲ መንገድ አውራ ጎዳና ከተማ ግጭት መከሰቱ ታውቋል
የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎችን በሚያዋስነው ባቢሌ አካባቢ ግጭት ማጋጠሙ ተሰማ፡፡ ከእሑድ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ግጭቱ መከሰቱን የጠቀሱ የአካባቢው ምንጮች፣ በሁለቱ ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡
ከገለልተኛ ወገን በአካባቢው በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት ባይቻልም፣ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የነበረው በተኩስ የታገዘ ግጭት ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በረድ ማለቱን የአካባቢው ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
የባቢሌ ወረዳ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በግጭቱ ሳቢያ መንገድ በመዘጋቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ነበር ብለዋል፡፡ ግጭቱ ያጋጠመው የሱማሌ ክልል ፀጥታ ኃይሎች ወሰን ተሻግረው የፍተሻ ኬላ በመፍጠር ጫት ካልቀረጥን በማለታቸው ነው ሲሉም የፀጥታ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ከሶማሌ ክልል የተነሱ የልዩ ኃይል ደንብ ልብስ የለበሱ ኃይሎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ድንበር ገብተው ጥቃት አድርሰዋል የሚሉት አቶ ሙሳ፣ ግጭቱ በከተሞች አካባቢ ሙሉ ለሙሉ ረገብ ቢልም በገጠር አካባቢዎች ግን አሁንም እንዳለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ግጭቱ ያጋጠመው የሶማሌ ክልል የታጠቁ ኃይሎች በባቢሌ ከተማ ኬላ ካልፈጠርን በማለታቸው አንደሆነ የተናገሩት አቶ ሙሳ፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው ፈጥነው በመድረሳቸው ኬላው ላይ የተፈጠረው ግጭት ቆሟል ብለዋል፡፡ ከዚያ ውጪ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ግን የተኩስ ልውውጡ መቀጠሉን አክለዋል፡፡ ከአዲስ ኬላ የመፍጠር ጥረት በተጨማሪ የእርሻ መሬትንም ካልወሰድን የሚል ጥረት አለ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ባቢሌ አቅራቢያ ቆሎጂ በተባለው ቦታ የሠፈሩ ተፈናቃዮችን ወደ ባቢሌ እንዲገቡ እየገፉ ነው በማለት የሶማሌ ክልል ታጣቂዎችን ወንጅለዋል፡፡
ጉዳዩን በሚመለከት ከሶማሌ ክልል በኩል ለማጣራት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል ወደተባሉት የሰማሌ ክልል የፀጥታና የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮዎች የሥራ ኃላፊዎች በእጅ ስልካቸው በተደጋጋሚ ቢደወልም፣ ምላሽ ሊሰጡ ባለመቻላቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡
ለሶማሌ ክልል ቅርብ የሆኑ የመረጃ ምንጮች በማኅበራዊ የትስስር ገጾችና በተለያዩ መንገዶች ባጋሩት መረጃ ግን፣ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ባቢሌ ከተማ አቅራቢያ ባለው ቆሎጂ መጠለያ ጣቢያ በሠፈሩ ተፈናቃዮች ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጥቃትም በመጠለያ ጣቢያ የነበሩ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ነው እነዚሁ ምንጮች የገለጹት፡፡ ይህንን መረጃ ማጣራት አልተቻለም፡፡
የቆሎጂ የተፈናቃዮች መጠለያ ከሐረር ወደ ጅግጅጋ በሚያልፈው ዋና አስፋልት መንገድ ላይ በባቢሌና በቦምበስ ከተሞች መካከል የሚገኝ ሰፊ ካምፕ ነው፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት በነበረው የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ግጭት ሳቢያ ከኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከ16 ሺሕ ያላነሱ ሰዎች፣ በሁለት መንደሮች በተሠሩ ችምችም ባሉ የፕላስቲክ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩበት ቦታ መሆኑ ይነገራል፡፡
እነዚህን ከኦሮሚያ ክልል በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ሌላ አካባቢ ለማስፈር ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) እና በሶማሌ ክልል መንግሥት በኩል ጥረት መጀመሩን አይኦኤም አስታውቆ ነበር፡፡ በመጠለያው ካሉ መካከል 700 ቤተሰቦችን አናገርኩ የሚለው አይኦኤም 44 በመቶዎቹ በሶማሌ ክልል ሌላ ቦታ በመደበኛነት ቢሰፍሩ እንደሚመርጡ ማረጋገጣቸውን፣ ሌሎች 44 በመቶዎች ደግሞ በዚያው በመጠለያው መኖር እንደሚፈልጉ መናገራቸውን፣ ቀሪዎቹ ሁለት በመቶዎቹ ግን ወደ ተፈናቀልንበት ኦሮሚያ ክልል እንመለስ ማለታቸውን በጥናት ማረጋገጡን ይፋ አድርጎም ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ ከስድስት ወራት በፊት 1,200 አባወራ ቤተሰቦችን ከቆሎጂ የተፈናቃዮች መጠለያ በማንሳት ከጅግጅጋ አልፋ በምትገኘው ቀብሪ በያህ ከተማ አቅራቢያ፣ በመጀመሪያ ዙር መርሐ ግብር በዘላቂነት ማስፈሩን አይኦኤም በመረጃው አስታውቆም ነበር፡፡ ይህ የቆሎጂ መጠለያ ተፈናቃዮችን ቀስ በቀስ በዘላቂነት የማስፈር መርሐ ግብር እንደሚቀጥልም አክሎ ገልጾ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በዚህ መጠለያ አቅራቢያ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎችን የሚያጋጭ ችግር መፈጠሩ የተነገረ ሲሆን፣ ግጭቱ በከፊል የቆሎጂ ተፈናቃዮች ካምፕን የሚነካ መሆኑ እየተነገረም ነው፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በዋናው የጂቡቲ መንገድ ላይ በምትገኘዋ አውራ ጎዳና ከተማ የአማራና የኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች መጋጨታቸው ተሰምቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ፣ እንዲሁም የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ አዋሳኝ የሆነችውና በአማራ ክልል የምትገኘው አውራ ጎዳና ከተማ ከዚህ ቀደምም የሁለቱ ክልል ኃይሎች ሲጋጩባት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የጂቡቲ መንገድ በሚያልፍበት አስፋልት መንገድ በወለንጪቲና በመተሐራ ከተሞች መካከል የምትገኘዋ ትንሽ ከተማ ከእሑድ መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የደረሰው ግጭት የትራንስፖረርት እንቅስቃሴን ማስተጓጎሉም ተነግሯል፡፡ ስለዚሁ ግጭት ከመንግሥትም ሆነ ከገለልተኛ ምንጮች ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡