Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዓለም ሻምፒዮና የ5000 ሜትር ቁጭቷን በዳይመንድ ሊግ በልዕልና የተወጣችው ጉዳፍ ፀጋይ

በዓለም ሻምፒዮና የ5000 ሜትር ቁጭቷን በዳይመንድ ሊግ በልዕልና የተወጣችው ጉዳፍ ፀጋይ

ቀን:

ከወር በፊት በሃንጋሪ ቡዳፔስት ከተማ ከወቅቱ ስኬታማ አትሌቶች መካከል ተጠባቂዋ ነበረች፡፡ በምትካፈልበት ርቀት ሜዳሊያ ማምጣቷ እንደማይቀር የሁሉም ሰው ግምት ነበር፡፡ በዓለም ሻምፒዮና፣ እንዲሁም በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ሰዓት በማሻሻል ጭምር ማሸነፍ ለለመደ አትሌት፣ ክብረ ወሰን መስበርና አዲስ የትራክ አሻራ ማኖር እንጂ ሜዳሊያ ማምጣት ቀላሉ ነገር ነው፡፡

በዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና በ10 ሺሕ ሜትር ወርቅ ማምጣት የቻለችው የዓምናዋ የዓለም ሻምፒዮና የ5 ሺሕ ሜትር ባለድሏ ጉዳፍ ፀጋይ፣ በሻምፒዮናው ሁለት ወርቅ ለማሳካት ነበር ዝግጅት ስታደርግ የቆየችው፡፡

በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና በሦስት ርቀቶች ማለትም 1500 ሜትር፣ 5000 እና 10,000 ሜትሮች የመካፈል ፍላጎት እንዳላት ስትገልጽ የነበረችው ጉዳፍ፣ በመጨረሻ በሁለት ርቀቶች ተወስና ወደ ሃንጋሪ ማቅናቷ ይታወሳል፡፡

በ10 ሺሕ ሜትር ከለተሰንበት ግደይና እጅጋየሁ ታዬ ጋር ተከታትለው በመግባት የወርቅ ሜዳሊያ ያሳካችው ጉዳፍ፣ በ5 ሺሕ ሜትር ልትደግመው እንደምትችል ከፍተኛ ግምት ሲሰጣት ነበር፡፡

ሆኖም በሁለቱ ርቀት እንደምትካፈል የገለጸችው ጉዳፍ፣ ከ10 ሺሕ ሜትር ድል በኋላ በነበረው ከፍተኛ ሙቀትና በሩጫው ወቅት እግሯ ላይ ጉዳት ገጥሟት ነበር፡፡

ከዚህም በሻገር ጣቶቿ ውኃ ቋጥረው ከሕመሟ ማገገም ባለመቻሏ የመሳተፏ ነገር ጥርጣሬ ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡

በመጨረሻም ጣቶቿን አሽጋ ለሁለተኛ ወርቅ በ5000 ሜትር የተሳተፈችው ጉዳፍ ያሰበችው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በ10 ሺሕ ሜትር የነበረው የቡድን ሥራን በ5000 ሜትር መድገም ባለመቻሉና እንስቶቹ ቀድመው የተነጋገሩትን በውድድሩ ባለመተግበራቸው የጉዳፍ በዓለም ሻምፒዮናው የሁለት ወርቅ ህልም ሳይሳካ ቀረ፡፡

በዚህ ቁጭት ወደ አገር ቤት የተመለሰችው ጉዳፍ፣ በ13 የተለያዩ ከተሞች ተከናውኖ በኦሪጎን ዩጂን ከተማ የሚጠናቀቀውን የዳይመንድ ፍፃሜ ከግምት ውስጥ አስገብታ ነበር፡፡

ከዓለም ሻምፒዮናው መልስ በአገር ቤት ልምምዷን አጥብቃ የቀጠለችው ጉዳፍ የ5000 ሜትር ተሳትፎዋ ተጠባቂ ነበረ፡፡

እሑድ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በዩጂን የ5000 ሜትር ፍፃሜ ጉዳፍ 14፡00፡21 በመግባት በኬንያዋ ፌይዝ ኪፕዬገን ተይዞ የነበረው ክብረ ወሰን ማስመለስ ችላለች፡፡

ይህም ኬንያዊቷ ፌይዝ ከወራት አስቀድሞ በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ 14፡05፡20 በመግባት፣ በለተሰንበት ግደይ ተይዞ የነበረውን በ14፡06፡62 ያሻሻለችውን ነው ጉዳፍ ማስመለስ የቻለችው፡፡ ከሳምንታት በፊት ለተሰንበት ክብረ ወሰኑን ለማስመለስ ጥረት ብታደርግም ሳይሳካላት መቅረቱ ይታወሳል፡፡

በዚህም መሠረት የ5000 ሜትር የምንጊዜም ክብረ ወሰን ከጨበጡ 10 እንስት አትሌቶች ሰባቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሲሆኑ፣ ሁለቱ ኬንያውያንና ለኔዘርላንድ የምትሮጠው ሲፋን ሐሰን ይገኙበታል፡፡

የዳይመንድ ሊግ ድምቀት የነበረችው ጉዳፍ፣ በዓለም ሻምፒዮናው በአምስት ሺሕ ሜትር የጠበቀችውን ማሳካት አለመቻሏ እንዳስቆጫትና ይህም በውድድር የሚያጋጥም መሆኑንም ጠቅሳ፣ በዓለም ሻምፒዮናው ስትጠብቅ የነበረውን በዳይመንድ ሊጉ ማሳካቷ እንዳስደሰታት ለልዩ ስፖርት ተናግራለች፡፡

ለዳይመንድ ሊግና ለዓለም ሻምፒዮና ስትዘጋጅ የሰነበተችው የዓለም ሻምፒናዋ ጉዳፍ፣ ከዚህ በኋላ የዕረፍት ጊዜዋ እንደሆነ ገልጻ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ጠብቁኝ ስትል አስተያየቷን ሰንዝራለች፡፡

ከግንቦት ወር ጀምሮ በተለያዩ ከተሞች ሲከናወን የቆየው የዳይመንድ ሊግ በታሪክ የሚታወቁ ኩነቶችን አስተናግዶ አልፏል፡፡ በዚህም ከየትኛውም ቀድሞ ከተከናወነ የዳይመንድ ሊግ ከፍተኛ ደረጃን ያገኘና ሙገሳ የተቸረው ነው፡፡

በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ የትራክና በሜዳ ተግባር በስምንት አዋቂ አትሌቶች አማካይነት ክብረ ወሰን የተሻሻለበት ነበር፡፡ ኬንያዊቷ ፌይዝ 1500 ሜትር፣ 5000 እንዲሁም በማይል ውድድር፣ ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ በ3000 ሜትር መሰናክል በአሎሎ ውርወራ ሮይን ክሮሰር የራሱን ክብረ ወሰን ያሻሻለበት፣ ስዊድናዊው አርማንድ ዱፕላንቲስ በምርኩዝ ዝላይ 6 ሜትር ከ23 ሳንቲ ሜትር በመዝለል የራሱን ክብረ ወሰን የሰበረበት፣ እንዲሁም የጊዜው ስኬታማ ኖርዌጂያን ጃኮብ ኢንገብሪግሰን በ2000 ሜትር አዲስ ክብረ ወሰን የጨበጠበት ሆኖ አልፏል፡፡   

በዘንድሮ አጠቃላይ የአትሌቲክስ ውድድር የቤት ውስጥ ከ20 በታች፣ እንዲሁም ሪሌይን ጨምሮ 29 የዓለም ክብረ ወሰኖች የተሰበሩ ሲሆን፣ 12 ሪከርዶች በዓለም አትሌቲክስ ፀድቀዋል፡፡ በዳይመንድ ሊግ ብቻ በተለያዩ ርቀቶች፣ እንዲሁም የሜዳ ተግባራት 18 ክብረ ወሰኖች ተሰብረዋል፡፡

በዳይመንድ ሊግ በዓለም ኬንያዊቷ ፌይዝ በ1500 ሜትር፣ 5000 ሜትርና  በማይል ውድድር ሦስት ጊዜ ስድስት ክብረ ወሰኖችን ማሻሻል የቻለች አትሌት ናት፡፡

የዩጂን የዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ ውድድር የወንዶች 5000 ሜትር ፍፃሜ ተጠባቂ ከሆኑት መካከል ቀዳሚ ነበር፡፡ ይህም በርቀቱ በሪሁ አረጋዊ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ጥላሁን ኃይሌና ኖርዌጂያን ጃኮብ እንግሪብሰን መኖራቸው ነበር ትኩረት እንዲስብ ያደረገው፡፡

ሆኖም በቡዳፔስቱ 5000 ሜትር ያሸነፈው ኢንገብሪግሰን በዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ ከዮሚፍ ቀጄልቻ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ አሸንፏል፡፡

በፍፃሜው ሲጠበቅ የነበረው በሪሁ ስድስተኛ ሲወጣ ጥላሁን ኃይሌ አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በዳይመንድ ሊግና በዓለም ሻምፒዮን ሲሳተፉ የከረሙት አትሌቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በላቲቪያ ሪጋ በሚከናወነው የዓለም የግማሽ ማራቶን የማይልና የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ይጠበቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...