Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዳዲስ የወባና ትንኝ ወለድ በሽታዎች የደቀኑት አደጋ

አዳዲስ የወባና ትንኝ ወለድ በሽታዎች የደቀኑት አደጋ

ቀን:

ኢትዮጵያ ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ የወባና ትንኝ ወለድ በሽታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየከሰቱና የሥርጭት አድማሳቸውንም እያስፋፉ መምጣታቸውን አፍሪካ አቀፍ የወባ ትንኝ መቆጣጠሪያ ማኅበር የኢትዮጵያ ቻፕተር አስታውቋል፡፡

እነዚህን የወባና ትንኝ ወለድ በሽታዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የደቀኑትን አደጋ ለመግታት እየተሠራ መሆኑንም ማኅበሩ ገልጿል፡፡

 ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ወደ 1000 የሚጠጉ ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ተሳታፊ የሆኑበትንና በወባ ትንኝና ባክቴሪያ ዙሪያ ትኩረት ያደረገው የአምስት ቀናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲከፈት የኢትዮጵያ ቻፕተር ሊቀመንበር ድልነሳው የኋላው (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ ከተከሰቱትም የወባ በሽታዎች መካከል ዳንጌ የተባለውና በእስያ ብቻ የነበረው በሽታ ይገኝበታል፡፡

ይህ በሽታ በቅድሚያ የገባው በ2013 ዓ.ም. በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ እየተስፋፋ መምጣቱን፣ በአፋር ክልል ብቻ 20,000 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውንና በዚህም የተነሳ የኅብረተሰብ የጤና ሥጋት ሊሆን እንደቻለ ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህም ሌላ በእስያና በገልፍ አካባቢ የሚገኝ አኖፌሌስ ስቴፈንሲ የተባለው የወባ አስተላላፊ ትንኝ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ጂቡቲ ውስጥ እንደተከሰተና በመቀጠልም ከ2016 ጀምሮ በኢትዮጵያ 51 አካባቢዎች ተሠራጭቶ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከምሥራቅ አፍሪካም አልፎ ወደ ምዕራብ አፍሪካ መዛመቱን አመልክተው፣ ወባን ከሚያስተላልፉ ነባር የወባ ትንኞች የሚለየው በአብዛኛው በከተማ መራባቱ ሲሆን፣ ዘወትር የሚጠቀማቸው ከቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ባሉ ቁሶች ላይ መሆኑንና ይህም በራሱ ትልቅ ሥጋት የደቀነ መሆኑን እንደሚያሳይ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ ማብራሪያ፣ ቅልጥም ሰባሪና ቢጫ ወባ የመሳሰሉ የወባ በሽታዎች ለዓመታት በተወሰነ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ የሚገኙ ሲሆን፣ የተጠቂውም ቁጥር ዝቅተኛ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በፍጥነት በመስፋፋት በበሽታው የሚጠቃው የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡

የተጠቀሱትን በሽታዎች አመንጪ የሆኑት ትንኞችም ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት መንስዔ የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ መነሻ ይሆናል፡፡ የሸቀጦችና የሰዎች ዝውውር፣ የሥነ ምኅዳር ለውጥ፣ ግሎባላይዜሽን ወይም ዓለም አቀፋዊ የንግድ ትስስር ሌላው መንስዔ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ የወባ በሽታን የሚያስተላልፉ ትንኞች የሚራቡበት ሥነ ምኅዳር ምን ይመስላል የሚለውን ለመለየትና ባህሪያቸውም አለመታወቁ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ስለሆነም በትንኞቹ ላይ የሚካሄደውን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራን ለማሳለጥ አፍሪካዊ የሆነ አንድ የሙያ ማዳበር መፍጠር ግድ ይላል፡፡

በዚህም የተነሳ በአፍሪካውያን ባለሙያዎች የሚመራ አፍሪካ አቀፍ የወባ ትንኝ ቁጥጥር ማኅበር እ.ኤ.አ. በ2016 እንደተመሠረተ፣ የትኩረት አቅጣጫውም በየአገሮቹ ከሚገኙና ጉዳይ በይበልጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በወባና በትንኝ/ባክቴሪያ ወለድ በሽታዎች ዙሪያ ቅኝት፣ ጥናትና ምርምር ማካሄድ፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊነቱን አንስተዋል፡፡

ለዚህም ዕውን መሆን በየአገሮቹ አፍሪካ አቀፍ የወባ ትንኝ ማኅበር ቻፕተር ማቋቋሙን፣ በኢትዮጵያ ይኸው ቻፕተር በ2011 ዓ.ም. ተቋቁሞ ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘቱንና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን አቅዳ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ችግሩን ለመቅረፍ ጥናቶች እየተካሄዱ መሆኑን፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በኢትዮጵያ ጭምር ምርምር በማድረግ ለፖሊሲ ግብዓት እንዲውል ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ላለፉት ሁለት አሠታት ባደረገው ርብርብ፣ በወባ የሚከሰት ሕመምና ሞትን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ቢቻልም ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ግን የወባ ወረርሽኝ ዳግም ሊከሰት መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፣ ባገረሸውም ወረርሽኝ ሳቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ውስጥ ሚሊዮኖች ለሕመም ብሎም ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ምርታማነትን ቀንሷል፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል አገሮች ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገዋል፡፡

የወረርሽኙ መንስዔዎች እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ በኮቪድ-19 ምክንያት የተፈጠረ የአቅርቦት እጥረት፣ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መዛባትና ግጭቶች መሆኑን ከሊያ (ዶ/ር) ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ወባን ለማጥፋት የሚያስችል የሦስት ዓመት ዕቅድ ነድፏ መተግበር መጀመሯን የጤና ሚኒስትሯ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ወረርሽኙ ዳግም ተከስቶ ጉዳቶች ቢያስከትልም የወባ ወረርሽኝን ከመከላከል በሽታውን እ.ኤ.አ. በ2030 ወደ ማጥፋት ዘመቻ መግባት መቻሉን ጠቁመው፣ በዚህም በወባ የሚያዙ ሰዎችን ከ40 በመቶ በታች ማውረድ ከቻሉ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አስረድተዋል፡፡

‹‹ከበሽታ ተህዋስያን ላይ ከሚታዩት ሥጋቶች አንፃር ክትትልንና ቁጥጥርን ማስተካከል›› በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን ይህንን ዓለም አቀፍ ጉባዔ ኢትዮጵያ ማስተናገዷ፣ ወባን ለመከላከል የሚረዱ ዘመኑ የደረሰበትን የጥናትና ምርምር እንዲሁም የፈጠራ ውጤቶችን ለማግኘት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የወባ በሽታ ከጤና እክልነት ባለፈ የዕድገት ማነቆ መሆኑን ያመለከቱት ስለጉባዔው ሒደት በዋዜማው መግለጫ የሰጡት የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ተገኔ ረጋሳ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ወረርሽኙ በተለይም በመኸር ወቅት የሚከሰት በመሆኑ አምራች የሆነውን ማኅበረሰብ በማጥቃት የምርት መቀነስ ያስከትላል ብለዋል፡፡

ይህን ወረርሽኝ ለመከላከል ባለፉት ዓመታት በተወሰዱ ዕርምጃዎች በወባ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎችን መቀነስ መቻሉን ያስረዱት ሥራ አስፈጻሚው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በዓለም አቀፍ፣ በአኅጉርና በአገር አቀፍ ደረጃ ወረርሽኙ እየጨመረ መሄዱን ተናግረዋል፡፡

አሁን ያለንበት ወቅት የወባ ትንኝ መራቢያ ወቅት በመሆኑ፣ በግለሰብም በማበረሰብም ደረጃ ውኃ ያቆሩ ስፍራዎችን በማፋሰስ፣ በኬሚካል የተነከሩ የአልጋ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀምና ሌሎች የመከላከልና መቆጣጠር ሥራዎችን በመተግበር፣ ወረርሽኙን መከላከል እንደሚያስፈልግና የሚዲያ ተቋማትም በወባ መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥተው መልዕክት እንዲያስተላልፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ጉባዔው ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የሚረዱ አዳዲስ ግኝቶች ይፋ እንደሚደረግ ያስታወቁት፣ የማለሪያ ኮንሰርትየም ካንትሪ ዳይሬክተርና የፓምካ ኮንፍረንስ ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አጎናፍር ተካልኝ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ሚዲያው በጥምረት በመሥራት ኅብረተሰቡን በማንቃትና ግንዛቤ በመፍጠር ወረርሽኙን ለመከላከል የበኩሉን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ የወባ ክትባት በኬንያ፣ ማላዊና ጋና በሙከራ ደረጃ እየተሰጠ እንደሚገኝና በቅርቡም የዓለም ጤና ድርጅት ለክትባቱ ዕውቅና መስጠቱን፣ በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሕይወት ሰሎሞን (ዶ/ር) በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...